ሱዳን ዘግታው የነበረውን ከኢትዮጵያ ጋር የሚያዋስናትን ድንበር ከፈተች

ሱዳን ከኢትዮጵያ ጋር በሚያዋስናት ድንበር አካባቢ ከሳምንታት በፊት ተከስቶ የነበረውን ግጭት ተከትሎ ዘግታው የነበረውን ቁልፍ የድንበር መተላለፊያ በር ከፈተች።
ሱዳን የገላባት የድንበር መተላለፊያን የተከፈተችው ከኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ጋር ገንቢ ውይይት ከተደረገ በኋላ ነው ብላለች።
ከሳምንታት በፊት ሱዳን ከኢትዮጵያ ጋር በምትዋሰንበት አካባቢ ተፈጸመ ባለችው ጥቃት የጦር አባላቶቼ ተገድለውበኛል ስትል ክስ ማሰማቷ ይታወሳል።
ሱዳን በኢትዮጵያ ጦር ሠራዊት ተፈጽሟል ባለችው ጥቃት 6 ወታደሮቿ እና አንድ ሲቪል መገደላቸውን ገልጻ ነበር።
የኢትዮጵያ መንግሥት በበኩሉ በዚህ ግጭት የአገር መከላከያ ሠራዊት ተሳትፎ እንዳልነበረው እና ጉዳቱ ያጋጠመው የሱዳን ኃይሎች የኢትዮጵያን ድንበር አልፈው ከገቡ በኋላ ከአካባቢው ሚሊሻ ጋር ባጋጠመ ግጭት ነው ብሏል።
የሱዳን መንግሥታዊው የዜና ወኪል ሱና፤ ገላባት የተባለው የድንበር በር እንዲከፈት የተወሰነው ድንበር ላይ ያጋጠመውን ችግር የሁለቱ አገራት መሪዎች ለመፍታት ከተስማሙ በኋላ ነው ሲል፣ የአገሪቱን ደኅንነት እና መከላከያ ምክር ቤት ቴክኒክ ኮሚቴን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል።
በድንበር አካባቢ የታጠቁ ኃይሎችን ለመቆጣጠር “በኢትዮጵያ በኩል የታየው በጎ ፍቃድ” የድንበር በሩ እንዲከፈት ምክንያት ከሆኑት መካከል አንዱ መሆኑም ተመላክቷል።
ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ እና የሱዳኑ መሪ ጄኔራል አብደል ፋታህ አል ቡርሐን በኬንያ ተገናኝተው መነጋገራቸው ይታወሳል።
ሁለቱ መሪዎች ሰኔ 28/2014 ዓ.ም. ናይሮቢ ላይ የተገኛኙት የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት (ኢጋድ) ልዩ የመሪዎች ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ ኬንያ ከገቡ በኋላ ነበር።
የሁለቱን መሪዎች ውይይት ተከትሎ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው፤ “ከጄኔራል አብዱል ፋታህ አል ቡርሐን ጋር ባደረግኩት ውይይት ሁለቱ አገራት በሰላማዊ መንገድ ለመስራት በርካታ ጉዳዮች እንዳሉ ስምምነት ላይ ደርሰናል” ብለው ነበር።
የሱዳን ደኅንነት እና መከላከያ ምክር ቤት ቴክኒክ ኮሚቴ ድንበሩ ከትናንት ዕሁድ ጀምሮ በይፋ መከፈቱን ይፋ ሲያደርግ የሱዳን ኃይሎች በአካባቢው ላይ የተጠናከረ ጥበቃ ያደርጋሉ ብሏል።

የፎቶው ባለመብት, ETH PM Office
ጋላባት ሁለቱ አገራት በድንበር ይገባኛል በሚወዛገቡበት አል-ፋሽካ አካባቢ የሚገኝ የድንበር በር ነው።
ሱዳን የኢትዮጵያን መከላከያ ሠራዊት ተጠያቂ ካደረገችበት ክስተት በኋላ የድንበር በሩ ዝግ ሆኖ ቆይቶ ነበር።
አል-ፋሽካ ተብሎ የሚጠራውን ሰፊ ለም የእርሻ አካባቢ በኢትዮጵያውያ ቁጥጥር ስር ቆይቶ የትግራይ ጦርነት መቀስቀሱን ተከትሎ ኢትዮጵያ ጦሯን ስታንቀሳቅስ የሱዳን ኃይሎች ቦታውን ይዘው ይገኛሉ።
በድንበር ይገባኛል ጥያቄ ምክንያት እየተወዛገቡ ያሉት ኢትዮጵያና ሱዳን፣ በአባይ ወንዝ ላይ በሚገነባው የሕዳሴው ግድብ ምክንያት ግንኙነታቸው ሻክሮ ቆይቷል።












