ሴቶች ከወንዶች የተሻለ ብቃት የሚያሳዩባቸው ስፖርቶች የትኞቹ ናቸው? ምክንያቱስ?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ረዥም ርቀት እና ብዙ ቀናት ከሚፈጀው አልትራ-ራኒንግ ከተሰኘው የሩጫ ውድድር ጀምሮ እስከ የዒላማ ተኩስ ውድድር ባሉ ስፖርቶች ሴቶች የተሻለ ውጤት ያስመዘግባሉ።
ምንም እንኳ ጊዜው 40 ዓመት ቢያልፈውም ፔኒ ሊ ዲን በወቅቱ የነበረው ብርድ አሁንም ያንዘፈዝፋታል።
ልምምድ በጣም ከባድ ነበር። በ1978 (እአአ) በእንግሊዝ ቻነል ላይ በሚካሄደው ፆታ የማይገድበው የዋና ውድድር ላይ ለመሳተፍ ብዙ ለፍታለች።
“እግሬን ማንቀሳቀስ፤ እጆቼን መዘርጋት አቅቶኝ ነበር” ትላለች ያን ጊዜ እያስታወሰች። ለሕዝብ ክፍት የሆነ ቦታ ሄዳ ልምምድ አድርጋ ስትመለስ ሙቀት እስኪሰማት ድረስ ሰዓታት ሊቆጠሩ ይችላሉ።
ለ20 ደቂቃ ሙቅ “ሻወር” ብትገባም ሰውነቷ በረዶ እንደሆነ ይቆያል። ሞቅ ያለ ውሃ የሞላው ገንዳ ውስጥ መግባትም መፍትሔ አይሆንም። ሻይ በኩባያ በላይ በላዩ ትጠጣለች።
ብርዱ አጥንት ሰርስሮ የሚገባ ቢሆንም ክብረ-ወሰን ሰባሪ ዋናተኛ ለመሆን የሚያስፈልገውን መስዋዕትነት ሁሉ ከፍላለች።
በዚህ ስፖርት ሴቶች የተሻለ ውጤት ያላቸው ብርድን የመቋቋም ኃይላቸው የላቀ ስለሆነ ነው። ሰውነታቸው ውስጥ ያለው ስብ የሚሰራጭበት መንገድ ወደ ቀዝቃዛ ውሃ ውስጥ ሲገቡ ሙቀታቸውን ለማመጠን ይረዳል።
ዲን፤ ሴቶች ምቹ ባለሆነ ሁኔታ ውስጥ ቢሆኑ እንኳ የመቋቋም አቅማቸው ሌላኛው ጥቅም ነው ብላ ታምናለች።
እርግጥ ነው ሴቶች ከአልትራ-ራኒንግ እና የዒላማ ተኩስ ባለፈ በሌሎች የስፖርት መስኮች ከወንዶች በላይ አሊያም ዕኩል የመወዳደር ብቃት አላቸው።
ነገር ግን በስፖርት ውድድሮች ለመሳተፍ የተራመዱት መንገድ ቀላል የሚባል አይደለም። አሁንም ቢሆን ፆታ በአትሌቲክስ ብቃት ላይ ያለው ተፅዕኖ ምን ያክል ነው የሚለው ጥያቄ ሙሉ በሙሉ ምላሽ አላገኘም።
አሳሳች ንፅፅር
አይቪንድ ሳንባክ የኖርዌይ አርቲክ ዩኒቨርሲቲ የስፖርት ሳይንስ ፕሮፌሰር ናቸው። ከሙያ አጋሮቻቸው ጋር ሆነው በሠሩት ጥናት መሠረት የዓለምን ክብረ ወሰን በጨበጡ ሴት እና ወንደ አትሌቶች መካከል ያለው ልዩነት ከ8 አስከ 12 በመቶ ሲሆን ወንዶች የበላይነቱን ይይዛሉ።
ጥናቱ አክሎ እንደሚጠቁመው በጣም ጥንካሬ በሚጠይቁ እንደ ውሃ ዋና ባሉ እና የላይኛው የሰውነት አካልን ጥንካሬ በሚጠይቁ ስፖርቶች በወንዶች በሴቶች መካከል ያለው ልዩነት ጠባብ ነው።
የፆታ መድልዎ ደግሞ የራሱን ሚና ይጫወታል። አንዳንድ ስፖርቶች “የሴቶች” ተደርገው ይቆጠራሉ። ሌሎች እንደ ቡጢ እና ማርሻል አርት ያሉ ስፖርቶች በአንዳንድ ባህሎች ዘንድ ሴቶች እንዲሳተፉበት አይፈለግም። ለምሳሌ በፓሪስ ኦሊምፒክ አርቲስቲክ ዋና በተሰኘው ስፖርት ወንዶች እየተሳተፉ አይደለም።
ሳንዳባክ እንደሚሉት በስፖርቱ ዘርፍ በሴቶች እና ወንዶች መካከል ያለውን ባዮሎጂካዊ እና ማኅበረሰባዊ ልዩነት ማወቅ ቀላል አይደለም። ለምሳሌ ወንዶች እና ሴቶች ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችን ለማድረግ ያላቸው ዕድል የተለያየ ነው።
ረዥም ርቀት በሚባሉት ስፖርቶች ደግሞ አትሌቶች መጀመሪያ ላይ ያላቸው ፍጥነት እና የሚጓዙበት ፍጥነት ወሳኝ ናቸው።
“ሴቶች በጠቅላላው የተጓዙበት ፍጥነት የተሻለ ነው። የማራቶን ሩጫን በምሳሌነት ማንሳት ይቻላል” ይላሉ ሳንድባክ። ውድድር ማለት የሰውነት አቅም ብቻ ሳይሆን ማኅበረሰባዊ ሁኔታዎች እና ሥነ-ልቦናንም የሚካተተቡት ነው።
አብዛኛዎቹ የሕፃናት አትሌቲካዊ ብቃት ላይ ያተኮሩ ጥናቶች እንደሚጠቁሙት ማኅበረሰባዊ ተፅዕኖዎች ከወንዶች በላይ ሴቶች ላይ ይበረታሉ።
የአሜሪካው ስፖርት ሜዲሲን ኮሌጅ በአውሮፓውያኑ 2023 ባወጣው ጥናት መሠረት ሴቶችና ወንዶች ወደ ታዳጊነት ከመሸጋገራቸው በፊት ያላቸው የአትሌቲክስ አቅም ውሱን ቢሆንም ከታዳጊነት በኋላ ግን እየተለያየ ይመጣል።
ነገር ግን ሕፃናት ወደ ታዳጊነት ከመቀየራቸው በፊት የተሠሩ ጥናቶች የተለያየ ውጤት ነው ያላቸው። ለምሳሌ አንዳንድ ጥናቶች ታዳጊ ወንዶች በመም ስፖርት የተሻለ አቅም እንዳላቸው ያሳያሉ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በሰውነት ውስጥ ያለ ቴስቴስትሮን የተባለው ንጥረ ነገር መጠን ከጡንቻ እና ጥንካሬ ጋር የሚያያዝ ነው። ከፍተኛ ሄሞግሎቢን ክምችት ያላቸው ደግሞ የተሻለ ኦክሲጅን የመሳብ አቅም አላቸው።
ቴስቴስትሮን የተባለው ኬሚካል በስፖርትም ሆነ በሌሎች እንቅስቃሴዎች ወንዶች ከሴቶች የተሻለ ድፍረት እንዲኖራቸው ያደርጋል።
ቴስቴስትሮን ሴቶች ላይ ምን ያክል ተፅዕኖ ሊኖረው እንደሚችል የሚያሳይ ብዙ ጥናት የለም። በተመሳሳይ ኦስትሮጂን ወንዶች ላይ ምን ያክል ተፅዕኖ እንዳለውም በልኩ አልተጠናም።
ስፖርት እና ፆታ ላይ በማተኮር የሚፅፉት የስፖርት ጋዜጠኛዋ ማጊ ሜርቴንስ በቴስቴስትሮን መጠን እና በስፖርታዊ እንቅስቃሴ መካከል ስላው ግንኙነት የሚያስረዳ ግለፅ ጥናት የለም ይላሉ።
“እንደውም በርካታ ጉምቱ የሚባሉ ወንድ አትሌቶች የቴስቴስትሮን መጠናቸው በአማካይ አነስተኛ የሚባል ነው” ይላሉ። ማጊ እንደሚሉት ከወንዶች ጋር የሚመጣጠን የቴስቴስትሮን መጠን ያላቸው ሴት አትሌቶች እንኳ ከወንዶች የሚተካከል የአትሌቲክስ ብቃት የላቸውም።
የከባድ ስፖርቶች ብቃት
ዲን በእንግሊዝ ቻነል የዋና ውድድር ክብረ-ወሰን ከመስበሯ በፊት ሎስ አንጀለስ በሚገኘው ካታሊና ቻነል አዲስ ክብረ-ወሰን አስመዝግባ ነበር። ይህን 32.5 ኪሎ ሜትር የሚፈጀውን የውሃ አካል ከ7 ሰዓት 16 ደቂቃ በታች ነው የገባችው። ዲን ይህ ክብረ-ወሰን እስካሁን እንዴት እንዳልተሰበረ ይገርማታል።
ከዋና ውድድር ራሷን ካገለለች በኋላ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ መምህርት ሆና ያገለገለች ሲሆን፣ የውሃ ስፖርት አሠልጣኝም ናት። የዋና ማራቶን ውድድር አቀንቃኝ የሆነችው ዲን ረዥም ርቀት የሚጓዙ ውድድሮች ይማርኳታል። የስፖርቱ መገለጫም ነው ብላ ታስባለች።
“32 ኪሎ ሜትር እና ከዚያ በላይ ባለው ርቀት ሴቶች ከወንዶች የተሻሉ ናቸው ብዬ አስባለሁ” የምትለው ዲን ሴቶችን ቀዝቃዛ ውሃ የመቋቋም ልዩ ችሎታ እንዳላቸው ትናገራለች።
ወንድ የዋና ተወዳዳሪዎች ብዙውን ጊዜ ረዥም እና ቀጠን ያለ ሰውነት ያላቸው ናቸው። ረዥም ርቀት በሚሸፍኑ የዋና ውድድሮች ከአየር ፀባይ ጀምሮ ስቃይ እስከ መቋቋም ያሉ ጉዳዮች ተፅዕኖ አላቸው። በእነዚህ ውድድሮች ላይ በወንዶች እና በሴቶች መካከል ያለው ልዩነት ጠባብ ነው።
በ2020 የተሠራ አንድ ጥናት 195 ኪሎ ሜትር እና ከዚያ በላይ በሚሸፍኑ ውድድሮች ሴቶች ከወንዶች 0.6 በመቶ ብልጫ አላቸው።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አእምራዊ ጥንካሬ
በፓሪስ ኦሊምፒክ በሴቶች እና በድብልቅ ፆታ የዒላማ ተኩስ የተሳተፈችው ደቡብ ኮሪያዊቷ ኪም የጂ ከዲን ጋር ትስማማለች።
በያዝነው ዓመት መጀመሪያ በዓለም አቀፉ የዒላማ ተኩስ ስፖርት ፌዴሬሽን ዓመታዊ ውድድር ላይ ተሳትፋ በ25 ሜትር የዒላማ ተኩስ አዲስ ክብረ-ወሰን ያስመዘገበችው ኪም በፓሪሱ ኦሊምፒክ ክብረ-ወሰን ልትሰብር ተቃርባ ነበር።
“የተኩስ ውድድር ከአካላዊ ብቃት በላይ አእምሯዊ ጥንካሬን ነው የሚጠይቀው ብዬ አምናለሁ” ትላለች ኪም። አትሌቷ እንደምትለው ሴቶች ከፍተኛ ጫና ባለበት ሁኔታ ተቋቁመው የማለፍ ጥንካሬያቸው በዒላማ ውድድር የተሻሉ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል።
በኦሊምፒክ ውድድር የ25 ሜትር የዒላማ ተኩስ ውድድር ወንዶች ከሴቶች በፈጠነ ሰዓት ውድድሩን ያጠናቅቃሉ።
በ2020 የቶኪዮ ኦሊምፒክ ወንዶች የሚንቀሳቀስ ዒላማን በመምታት ከሴቶች የተሻሉ ሆነው ሲገኙ፤ ቋሚ ዒላማን በመምታት ግን ሁለቱ ፆታዎች ተመጣጣኝ ብቃት አሳይተዋል።
የፓሪስ ኦሊምፒክ ዕኩል ቁጥር ያላቸው ሴት እና ወንድ አትሌቶች የተሳተፉበት የመጀመሪያው ውድድር ሆኗል። ሳንድባክ ይህን ቢያበረታቱም በዘርፉ በርካታ ጥናቶች ሊሠሩ ይገባል የሚል ሐሳብ አላቸው።












