በወፍ ጉንፋን የተያዘ የመጀመሪያው በግ መገኘት እና ቫይረሱ ወደ ሰው እየተጠጋ ይሆን የሚለው ስጋት

በጎች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በወፍ ጉንፋን የተያዘው የመጀመርያው በግ በእንግሊዝ ተገኝቷል

በሰሜናዊ እንግሊዝ ለመጀመርያ ጊዜ በወፍ ጉንፋን (በርድ ፍሉ) የተያዘ በግ መገኘቱን ተከትሎ፣ ቫይረሱ በአጥቢ እንስሳት መካከል የሚዛመት መሆኑ ከጊዜ ወደ ጊዜ አሳሳቢ እየሆነ መጥቷል ።

ይህ በሌላ ስሙ ኤች5ኤን1 በመባልም የሚታወቀው ቫይረስ ቀደም ሲል ከብቶችንና የዱር አጥቢ እንስሳትን አጥቅቶ ያውቃል።

በተጨማሪም ከሁለት አሥርተ ዓመታት በፊት ይህ የወፍ ጉንፋን በሽታ በወረርሽኝ መልክ ተከስቶ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተይዘው የነበረ ሲሆን ከእነዚህ መካከል ግማሽ የሚያህሉ ሕይወታቸውን አጥተዋል።

ይኹን እንጂ በአሁኑ ጊዜ ቫይረሱ ከሰው ወደ ሰው ሊተላለፍ እንደማይችል ሳይንቲስቶች ይናገራሉ።

በዶሮ እርባታ ጣብያ ውስጥ የሚገኙ እንቁላል ጣይ ዶሮዎች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ኤች5ኤን1 ቫይረስ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገኘው እአአ በ1996 በደቡባዊ ቻይና እና በሆንግ ኮንግ ነው።

የወፍ ጉንፋን ምንድን ነው? እንዴትስ ይሰራጫል?

የወፍ ጉንፋን (በርድ ፍሉ) ለ100 ዓመታት ያህል በዶሮዎች እና በዱር አእዋፋት ዘንድ የኖረ ተላላፊ በሽታ ነው።

በአሁኑ ጊዜ እንደ ቀበሮ፣ ሲል እና ኦተር ያሉ የዱር አጥቢ እንስሳት እንዲሁም በግና ላሞች በበሽታው እየተያዙ ነው።

በአሁኑ ጊዜ በጣም ተስፋፍቶ የሚገኘው ኤች5ኤን1 ቫይረስ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገኘው እአአ በ1996 በደቡባዊ ቻይና እና በሆንግ ኮንግ ነው።

በጥቂት ቀናት ውስጥ፣ ከአካላቸው በሚወጡ ፈሳሾች፣ በምራቅ አሊያም በተበከለ ምግብና ውኃ አማካኝነት በሁሉም ለማዳ ወፎች ዘንድ ሊሰራጭ ይችላል።

ቫይረሱ ወደ ላሞችም ተሻግሯል።

በዩናይትድ ስቴትስ እስከ መጋቢት 16/2017 ዓ.ም. ድረስ በ17 ግዛቶች ውስጥ 989 ከብቶች በቫይረሱ ተጠቅተዋል።

ይኹን እንጂ ቫይረሱ አየር ወለድ በሽታ እንደመሆኑ ከላም ወደ ላም አይተላለፍም፤ ከዚህ ይልቅ የወተት አመንጪ እጢዎቻቸውን አጥቅቷል።

ሳይንቲስቶች ቫይረሱ ወደ ላሞቹ የተላለፈው በወተታቸው በኩል መሆኑን ይናገራሉ ።

በዩናይትድ ስቴትስ የእንስሳት ሳይንስ ምርምር ማዕከል ባልደረባ ዶክተር ቶማስ ፒኮክ "በተበከለ የወተት ማሽን አማካኝነት የተላለፈ ይመስላል" ብለዋል።

የወፍ ጉንፋን ለ100 ዓመታት ያህል የቆየ የዶሮ እና የዱር አእዋፋት ተላላፊ በሽታ ነው።

በመጋቢት 2025 መገባደጃ ላይ፣ በሰሜን እንግሊዝ ውስጥ በዮርክሻየር በሚገኝ አነስተኛ እርሻ አንዲት በግ የወፍ ጉንፋን እንዳለባት ታወቀ።

እርሻው አንድ ላይ ተቀላቅለው የሚውሉ የበግ እና የዶሮ እርባታ ነበረው።

የዓለም ጤና ድርጅት በ24 አገራት ቢያንስ 954 ሰዎች በኤች5ኤን1 አቪያን ፍሉ ሲያዙ ከእነዚህም ውስጥ 464 ያህሉ ሞተዋል ሲል አስታውቋል።

በበሽታው የተያዙት ሰዎች በቫይረሱ ከተጠቁ ወፎች እና ሌሎች ፍጥረታት ጋር የቅርብ ግንኙነት ነበራቸው ተብሏል።

የዓለም ጤና ድርጅት ሪፖርት አብዛኛዎቹ እነዚህ ጉዳዮች የተከሰቱት በእስያ ውስጥ ባሉ አገሮች ሲሆን ሌሎች ደግሞ በአፍሪካ፣ አውሮፓ እና አሜሪካም ናቸው ይላል።

በ2024 ከሰሜን አሜሪካ በተጨማሪ በካምቦዲያ፣ ቬትናም፣ አውስትራሊያ እና ካናዳ በቫይረሱ የተጠቁ ሰዎች ተመዝግበዋል።

በሰኔ ወር መጀመሪያ ላይ በሜክሲኮ ውስጥ የ59 ዓመት እድሜ ያለው ጎልማሳ ከዚህ በፊት በሰዎች ላይ ተመዝግቦ በማያውቅ ሌላ ዓይነት የወፍ ጉንፋን (ኤች 5ኤን2) ተጠቅቶ ሞቷል።

በሜክሲኮ ውስጥ በአንዳንድ የዶሮ እርባታዎች ላይ ወረርሽኞች ቢኖሩም ግለሰቡ ግን እንዴት እንደያዘው ግልጽ መረጃ የለም።

የዓለም ጤና ድርጅት የሰው ልጅ በበሽታው ከተያዙ እንስሳት ጋር በእርባታ እና በእርድ ወቅት የሚኖረው ንክኪ ወይም በበሽታው በተያዙ እንስሳት የሰውነት ፈሳሽ የተበከሉ ነገሮችን በመንካት ለወፍ ጉንፋን ሊጋለጥ እንደሚችል ገልጿል።

እንደ የአሜሪካ የበሽታ መቆጣጠሪያ እና መከላከያ ማእከል (ሲዲሲ) ቫይረሱ መለስተኛ ጉንፋን መሰል ምልክቶችን የሚያስከትል ሲሆን፣ ለሞት የሚያጋልጡ እንደ ሳምባ ምች ያሉ ከባድ ሕመሞችንም ሊያመጣ ይችላል።

በወተት ላሞች እርባታ ጣብያ ላሞች እና ባለሙያዎች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ባለፉት 20 ዓመታት ብቻ በ23 አገራት በኤች5ኤን1 ቫይረስ የተያዙ ሰዎች ተገኝተዋል

ወተትን መጠጣት ደህንነቱ የተጠበቀ ነው?

የአሜሪካ የምግብ እና የመድሀኒት ቁጥጥር ኤጀንሲ (ኤፍዲኤ) እና ሌሎች የፌደራል ኤጀንሲዎች በወተት ውስጥ የሚገኙ ጎጂ ባክቴሪያዎችን ለመግደል እና ረዘም ላለጊዜ እንዲቆይ ፓስቸራይዝድ ( pasteurized) የሆነ ወተትን መጠጣት ደህንነቱ የተጠበቀ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

የአሜሪካ የምግብ ደህንነት እና ቁጥጥር ባለስልጣን ሰዎች ፓስቸራይዝድ ያልሆነ ወተት እንዳይጠጡ ይመክራል።

ኤች5ኤን1 (H5N1) እንዳይስፋፋ እንዴት መከላከል ይቻላል?

የአሜሪካ የምግብ እና የመድሀኒት ቁጥጥር ኤጀንሲ (ኤፍዲኤ) እንደገለጸው የመጀመርያዋ ላም በቫይረሱ መያዝዋ ከታወቀ ጀምሮ በመላ አገሪቱ በሚገኙ የወተት ላሞች እንዲሁም የስጋ እና የወተት ተዋጽኦዎች ላይ ክትትል እየተደረገ ነው።

ዩናይትድ ኪንግደም በእርባታ ጣብያዎች የሚገኙ እንስሳት ላይ ክትትል እያደረገች ሲሆን፣ ይህም በዮርክሻየር ውስጥ በበሽታው የተጠቃ በግ ለመገኘቱ አስተዋጽኦ አድርጓል።

እንደ ካናዳ ያሉ አንዳንድ አገራት ደግሞ ከአሜሪካ እንዲሁም ኮሎምቢያ እንስሳትን እና የእንስሳት ተዋጽኦዎችን በሚያስገቡ ድርጅቶች ላይ ጥብቅ የቁጥጥር መስፈርት አስቀምጠዋል።

የወፍ ጉንፋንን ለመከላከል ምንም ዓይነት ክትባት የሌለ ሲሆን፣ ነገር ግን አንዳንድ አገሮች ክትባቱን ለመስራት እየተነጋገሩ ነው።

በዩናይትድ ኪንግደም ሮያል የእንስሳት ሕክምና ኮሌጅ የስነ ሕይወት ባለሙያ የሆኑት ዶክተር ጄይና ራግዋኒ ይህ በአንፃራዊነት በፍጥነት ሊከናወን ይችላል ሲሉ ተስፋቸውን ገልጸዋል።

"በኢንፍሉዌንዛ ቫይረስ ከባዶ መጀመር የለብንም" ይላሉ ምሁሯ። "ነባር የጉንፋን ክትባቶችን የበሽታ መከላከል ምላሽን ከፍ ለማድረግ እና መከላከያዎቹ እንዴት እንደሚሠሩ ጥሩ ግንዛቤ አለን።"

ክትባቶቹ በመጀመሪያ የዶሮ እርባታ ውስጥ ለሚሰሩ፣ ለእንስሳት ሐኪሞች፣ በእንስሳት ጸጉር ምርት ላይ ለተሰማሩ እና በሽታውን ለሚመራመሩ ሳይንቲስቶች ይሰራጫሉ።

ከቦታ ወደ ቦታ እየተንቀሳቀሱ ሕይወታቸውን የሚመሩ አእዋፋት በቻይና በሚገኝ ሐይቅ ላይ ሲበሩ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የወፍ ጉንፋን በዶሮ እርባታ ውስጥ እና በዱር አእዋፋት ላይ የሚገኝ ተላላፊ በሽታ ነው

ቫይረሱ ባህሪውን ሊቀይር ይችል ይሆን?

ተመራማሪዎች ኤች5ኤን1 ቫይረስ ከሰው ወደ ሰው አይተላለፍም ሲሉ ይናገራሉ። ነገር ግን ቫይረሱ ባህሪውን ሊለውጥ ይችል ይሆናል የሚል ስጋት አላቸው።

በዩናይትድ ኪንግደም በሚገኘው የግላስጎው ዩኒቨርሲቲ የኤምአርሲ ዩኒቨርስቲ የቫይረስ ምርምር ማዕከል ዶክተር ኢድ ሃቺንሰን " ቫይረሱ በግስጋሴ ላይ ያለ ነው፤ ለዚያም ነው በንቃት እና በስጋት ስንከታተለው የነበረው " ብለዋል ።

የዓለም ጤና ድርጅት የዓለም አቀፍ የኢንፍሉዌንዛ ፕሮግራም ኃላፊ የሆኑት ዶክተር ዌንኪንግ ዣንግ በበኩላቸው "በሰዎች ላይ የሚደርሰው እያንዳንዱ ኢንፌክሽን ቫይረሱ በሰው ልጅ ውስጥ ራሱን ለማቆየት የሚያደረገው ሙከራ ነው" ብለዋል።

"ምንም እንኳ እስካሁን ያለው ዕድል ጠባብ ቢሆንም፣ አንድ ጊዜ፣ አንድ ጊዜ ብቻ ከተሳካለት፣ ያ የኢንፍሉዌንዛ ወረርሽኝ መጀመሪያ ይሆናል" ሲሉም ያክላሉ።

ባለሙያዎች በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት የተገኘው ልምድ እና የመከላከያ እርምጃዎች ቫይረሱ ወደ ሰዎች እንዳይተላለፍ ለመከላከል እንደሚረዳ ተስፋ ያደርጋሉ።

የወፍ ጉንፋን በሽታ ባለባቸው አገራት የሚኖሩ ሰዎች ምግብን ከመንካታቸው በፊት እና በኋላ እጃቸውን በሞቀ ውሃ እና በሳሙና መታጠብ እንዳለባቸው ይመክራሉ።

በተለይም በዶሮ እርባታ ውስጥ የሚሰሩ እና ሕይወት ካላቸው አእዋፋት ጋር ቅርበት ያላቸው ንክኪያቸውን አጥብቀው እንዲቀንሱ ይመክራሉ።