ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኔታንያሁ አይሲሲ ያወጣባቸውን የጦር ወንጀሎች የእስር ማዘዣ አወገዙ
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ የዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት በእርሳቸው እና በቀድሞው የመከላከያ ሚኒስትር ዮአቭ ጋላንት ላይ የጦር ወንጀሎች የእስር ማዘዣ እንዲወጣ ያስተላለፈውን ውሳኔ “ፀረ-ሴማዊ” ሲሉ አውግዘዋል።
“በሲቪሎች ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለማስወገድ የምንችለውን ሁሉ እያደረግንም ነው” አይሲሲ “በውሸት ሰላማዊ ሰዎች ላይ አነጣጥረዋል” በሚል እየከሰሳቸው መሆኑን ተናግረዋል።
አይሲሲ ለሐማሱ አዛዥ መሐመድ ዴይፍም የእስር ማዘዣ አውጥቷል። እስራኤል ግን አዛዡ በጋዛ ውስጥ በሐምሌ ወር መገደሉን ተናግራለች።
የአይሲሲ ዳኞች ሦስቱ ሰዎች በእስራኤል እና በሐማስ መካከል እየተደረገ በሚገኘው ጦርነት ለፈጸሙት ጥፋት “የወንጀል ተጠያቂነት” መኖሩን ለማመን “በቂ ምክንያቶች” እንዳሉ ተናግረዋል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በእስራኤል ባለሥልጣናት ላይ የአይሲሲ ያስተላለፈውን ውሳኔ “አሳፋሪ” ብለውታል።
“አይሲሲ ምንም ይሁን ምን በእስራኤል እና በሐማስ መካከል ምንም ዓይነት እኩልነት በጭራሽ የለም። በደኅንነቷ ላይ የሚደርሱ ስጋቶችን ለመከላከል ሁሌም ከእስራኤል ከጎኑ እንቆማለን” ሲሉ ባይደን ባወጡት መግለጫ ተናግረዋል።
እስራኤልም ሆነች ሐማስ አይሲሲ ያቀረበውን ውንጀላ አይቀበሉም።
ኔታንያሁ ሐሙስ ዕለት በሰጡት መግለጫ “በሄግ የሚገኘው ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት ያሳለፈው ፀረ-ሴማዊ ውሳኔ ዘመናዊ የድሬይፉስ ችሎት ነው። በተመሳሳይ መንገድም ይጠናቀቃል” ብለዋል።
ይህም ከአንድ መቶ ዓመት በፊት በፈረንሳይ በከፍተኛ ደረጃ የነበረውን የፀረ-ሴማዊነት ጉዳይ በማጣቀስ ነበር።
“በሄግ የሚገኘው ፍርድ ቤት ሆን ብለን የረሃብ ፖሊሲ እንደምናካሄድ ጠቅሶ ከሶናል” በማለት ጠቅላይ ሚንስትር አስታውቀዋል።
“ይህ የሆነው የጋዛን ሕዝብ ለመመገብ 700 ሺህ ቶን ምግብ አቅርበን ነው። የጋዛ ዜጎችን ከጉዳት ለመከላከል በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የጽሑፍ መልዕክቶችን፣ የስልክ ጥሪዎችን፣ በራሪ ወረቀቶችን እናደርሳለን። የሐማስ አሸባሪዎች ግን እነርሱን በጥይት ከመምታት ጀምሮ እንደ ሰብዓዊ ጋሻ በመጠቀም ጉዳት እንዲደርስባቸው ሁሉንም ነገር ያደርጋሉ።”
እስራኤል የአይሲሲን “ውሳኔ ትክክለኛነት እንደማትቀበል” ኔታንያሁ ተናግረዋል።
የተባበሩት መንግሥታት በዚህ ሳምንት እንዳስታወቀው በእስራኤል ጦር ከበባ ውስጥ በሚገኘው በሰሜን ጋዛ ባለፉት 40 ቀናት ውስጥ ምንም ዓይነት ዕርዳታ ባለመድረሱ ነዋሪዎች “ከፍተኛ አደጋ እያጋጠሟቸው ነው” ሲል አስጠንቅቋል።
ጋላንት በበኩላቸው አይሲሲ “የእስራኤልን መንግሥት እና የሐማስ ገዳይ መሪዎችን በእኩል አስቀምጦ ህጻናት መግደልን፣ የሴቶች መደፈርን እና የአዛውንቶች ከአልጋቸው ላይ መታፈንን ሕጋዊ አድርጓል”ብሏል።
የቀድሞ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ኢሁድ ኦልመርት ለቢቢሲ እንደተናገሩት ከሆነ ኔታንያሁ ከሐማስ ጋር ያለውን ግጭት የሚያስኬዱበትን መንገድ ቢተቹም በአይሲሲ ውሳኔ ግን አይስማሙም።
“እስራኤል በጠቅላይ ሚኒስትሩ እና በመከላከያ ሚኒስትሩ ላይ ክስ ሊያስመሰርትባቸው የሚገባ የዘር ማጥፋት ወይም የጦር ወንጀል አልፈጸመችም” ሲሉ ኦልመርት ለሬዲዮ 4 ዎርልድ ቱናይት ፕሮግራም ተናግረዋል።
ሐማስ ስለዲይፍ ማዘዣ ምንም አስተያየት ሳይሰጥ በኔታንያሁ እና በጋላንት ላይ የተወሰደው እርምጃ “ታሪካዊ ምሳሌ እና በሕዝባችን ላይ ላለው ረዥም ታሪካዊ ኢፍትሃዊ መንገድ እርማት የሚሰጥ ነው” ብሏል።
በጋዛ የሚኖሩ ፍልስጤማውያን የእስራኤል መሪዎች ለፍርድ እንደሚቀርቡ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።
እስራኤል ጦሯ በጋዛ የዘር ማጥፋት ወንጀል እየፈፀመ ነው የሚለውን ውንጀላ ውድቅ አድርጋለች። ይህ ጉዳይ በዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት ለብቻው እየታየ ያለ ጉዳይ ነው።
በአይሲሲ የወጣው የእስር ማዘዣ የሚወሰነው እስራኤልን ወይም አጋሯን አሜሪካን ያላካተቱት የፍርድ ቤቱ 124 አባል አገራት ተፈጻሚ እንዲሆን በሚሰጡት ውሳኔ ላይ ነው።
በርካታ የአውሮፓ አገራት የአይሲሲን ውሳኔዎች እንደሚያከብሩ ተናግረዋል። የብሪታንያ መንግሥትም የአይሲሲን ነጻነት እንደሚያከበር አስታውቋል።
ዐቃቤ ሕግ በሦስቱ ሰዎች ላይ ያቀረበው ክስ የሐማስ ታጣቂዎች እስራኤልን በማጥቃት 1200 የሚደርሱ ሰዎችን ከገደሉበት እና ሌሎች 251 ሰዎችን አግተው ወደ ጋዛ ከወሰዱበት ከመስከረም 26/2016 ዓ.ም. በኋላ ያለውን የሚመለከት ነው።
እስራኤል ሐማስን ለማጥፋት ወታደራዊ ዘመቻ በመክፈት በሰጠችው ምላሽም ቢያንስ 44 ሺህ ሰዎች ጋዛ ውስጥ መሞታቸውን በሐማስ የሚመራው የግዛቲቱ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አስታውቋል።
ዴይፍን በተመለከተ ደግሞ የአይሲሲ ቅድመ ችሎት “በሰብዓዊነት ላይ ለሚፈጸሙ ወንጀሎች፣ ማጥፋት፣ ማሰቃየት፣ አስገድዶ መድፈር እና ሌሎች ፆታዊ ጥቃቶች፣ እንዲሁም የግድያ ወንጀል፣ ማሰቃየት እና ጭካኔ ለተሞላበት አያያዝ ተጠያቂ ነው ብሎ ለማመን ምክንያቶችን አግኝቷል።”
በሰብዓዊነት ላይ የተፈጸሙት ወንጀሎች በሐማስ እና በሌሎች የታጠቁ ቡድኖች “በእስራኤል ሲቪል ሕዝብ ላይ ያደረሱት ሰፊ እና ስልታዊ ጥቃት አካል ነው ብሎ ለማመን ምክንያቶች እንዳሉም” ገልጿል።
በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ ከመከላከያ ሚኒስትርነት የተነሱት ጋላንት እና ኔታንያሁ ደግሞ “እያንዳንዳቸው ከሌሎች ጋር በጋራ በመሆን ለሚከተሉት ጉዳዮች የወንጀል ኃላፊነት ይወስዳሉ፡ ረሃብን እንደጦር መሣሪያ መጠቀም እና በሰብአዊነት ላይ የሚፈጸሙ ግድያ፣ ስደት እና ሌሎች ኢሰብአዊ ድርጊቶች” ብሏል።
“በሲቪል ሕዝብ ላይ ሆን ተብሎ የሚሰነዘረውን ጥቃት በመምራት ረገድም እንደ ሲቪል የበላይ ኃላፊ የወንጀል ኃላፊነት አለባቸው” ብሎ ለማመን አሳማኝ ምክንያቶች አግኝቷል።