ታዋቂው የአልባሳት አምራች ዛራ ማስታወቂያዎቹ በጣም የከሱ ሞዴሎችን በመጠቀሙ ታገዱ

ከተከለከሉት ማስታወቂያዎች አንዱ

የፎቶው ባለመብት, Zara

በፋሽን ኢንዱስትሪው ስመ ጥር የሚባለው ታዋቂው የአልባሳት አምራች ዛራ ሁለት ማስታወቂያዎች "ጤናማ የማይመስሉ የከሱ" ሞዴሎችን በመጠቀሙ ታገዱ።

የዩናይትድ ኪንግደም የማስታወቂያ ደረጃዎች ባለስልጣን የአንደኛዋ ሞዴል የጸጉር ስታይል በጣም የከሳች አድርጎ ያሳያት ሲሆን የሌላኛዋ ሞዴል አቋቋሟ እንዲሁም የተጋለጠው ቲሸርት የሞዴሏን የገጠጠ አጥንት እንዲወጣ አድርጎታል ብሏል።

ባለስልጣኑ እነዚህ "ኃላፊነት የጎደላቸው ማስታወቂያዎች በአሁኑ ወቅት ለዕይታ እንዳይቀርቡ እንዲሁም ዛራ ከዚህ በኋላ ለሚያወጣው የማስታወቂያ ምስሎች "በኃላፊነት መዘጋጀታቸውን" ማረጋገጥ እንዳለበት ውሳኔውን አስተላልፏል።

የባለስልጣኑን ውሳኔ ተከትሎ ዛራ ማስታወቂያዎቹን ያስወገደ ሲሆን እነዚህ ጥያቄ የሚነሳባቸው ሞዴሎች ፎቶዎቹን በሚነሱበት ወቅት በጥሩ ጤንነት ላይ መሆናቸውን የሚያረጋግጥ የህክምና የምስክር ወረቀት እንደነበራቸው ገልጿል።

እነዚህ ሁለት የተከለከሉ ማስታወቂያዎች በአልባሳት አምራቹ መተግበሪያዎች እና ድረገጾችን ላይ ተለጥፈው ነበር።

አንደኛው ማስታወቂያ ለአጭር ቀሚስ ሲሆን ፎቶው ላይ ያለው የካሜራ የጥላ አጠቃቀም የሞዴሏ እግሮች በጣም የቀጨጨ እንዲሆን ለማድረግ ጥቅም ላይ ውሏል ሲል ባለስልጣኑ ወቅሷል።

በተጨማሪም ፎቶው ላይ የሚታየው የላይኛው እጆቿ እና የክርን መገጣጠሚያዎቿ የተመጣጠነ ሰውነት አቀማመጥ የሌላት አድርጓታል ብሏል።

ሌላኛው የተከለከለው ማስታወቂያ የቲሸርት ሲሆን የሞዴሏ የአንገት አጥንት ትኩረት ያደረገ መሆኑ ተገልጿል። ባለስልጣኑ ሌሎች ሁለት የዛራ ማስተዋወቂያዎችን ቢመረምርም እገዳ አልተጣለባቸውም።

ዛራ ባለስልጣኑ የከለከላቸውን ምስሎች ያስወገደ ሲሆን ከሌሎች አካላት ምንም አይነት ቅሬታ አልደረሰኝም ብሏል።

አምራቹ እነዚህ የማስታወቂያ ምስሎች በጣም አነስተኛ ከሆኑ የብርሃን እና የቀለም አርትኦቶች በሰተቀር ምንም አይነት ማሻሻያ እንዳልተደረገባቸው ለባለስልጣኑ ተናግሯል።

ኩባንያው አክሎም የሞዴሎችን ጤና ማዕከል ባደረገው በዩኬ ሞዴል ኸልዝ ኢንኳየሪ በተሰኘውና በአውሮፓውያኑ 2007 የወጣው ሪፖርት ምክረ ሃሳቦችን በተከተለ መልኩ እንደሚሰራ አስታውቋል።

ዛራ በሪፖርቱ ከተካተቱት ውስጥ ሶስቱን ምክረ ሃሳቦች እንዳሟላ ገልጾ ፤ይህም ሞዴሎች "የአመጋገብ መዛባትን በማወቅ ረገድ ልምድ ካላቸው ዶክተሮች ጤናቸውን የሚያረጋግጥ የህክምና የምስክር ወረቀት ማቅረብ አለባቸው" ይላል።

ከጥቂት ወራት በፊትም ሌሎች የአልባሳት አምሯቾች የተጠቀሟቸው ሞዴሎች የመነመኑ ናቸው በሚል ማስታወቂያዎቻቸው ታግደዋል።

በሐምሌ ወር ማርክስ ኤንድ ስፔንሰር የተባለው ታዋቂው የአልባሳት አምራች ኩባንያ የተጠቀማት ሞዴል "ጤናማ ባልሆነ መልኩ የከሳች" ነች በሚል ማስታወቂያው ታግዶ ነበር።

ባለስልጣኑ የሞዴሏ አቋቋም እንዲሁም የአለባበስ ምርጫ የእግሮቿን ቅጥነት እንዲያጎላ በመደረጉ ማስታወቂያው "ኃላፊነት የጎደለው ነው" ብሏል።

ከዚያ ቀደም ብሎም ኔክስት የተባለው አምራች የጂንስ ማስታወቂያው ታግዷል።

ለዚህም ባለስልጣኑ አንደ ምክንያት የጠቀሰው ማስታወቂያው የሞዴሏን የእግር ቅጥነት ለማጉላት ሲል በካሜራ የተለያዩ እንግሎችን መጠቀሙ ኃላፊነት እንደጎደለው አትቷል።