ከሜኒሶታ ግዛት የሕዝብ ገንዘብ ለአል ሻባብ ይተላለፋል በሚል የአሜሪካ መንግሥት ምርመራ ጀመረ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአሜሪካ መንግሥት፤ የሜኒሶታ ግዛት የሕዝብ ገንዘብ ለሶማሊያው ታጣቂ ቡድን አልሻባብ ይሸጋገራል በሚል በቀረበው ክስ ላይ ምርመራ መጀመሩን አስታወቀ።
የአሜሪካ ግምጃ ቤት እንዳስታወቀው፤ ከአሜሪካዋ ግዛት የሚላከው የሕዝብ ገንዘብ ወደ ታጣቂው ቡድን መሻገሩን በተመለከተ ምርመራ ከፍቷል።
ግምጃ ቤቱ በኤክስ ገጹ ላይ ባወጣው ጽሑፍ እንዳመለከተው ምርመራው የተጀመረው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በሰጡት ትዕዛዝ ነው።
የቀድሞው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደንን እና አገረ ገዢው ቲም ዋልዝን "የአሠራር ክፍተት" በመፍጠር ከስሷል።
ግምጃ ቤት ብሎ የሚታወቀው የአሜሪካ የገንዘብ ሚኒስቴር ምርመራውን ሲያጠናቅቅ ግኝቶቹን ይፋ እንደሚያደርግም አስታውቋል።
ትራምፕ ከሁለት ቀናት በፊት የአሜሪካው ወግ አጥባቂ ሚዲያ 'ጀስት ዘ ኒውስ' ያወጣውን ዘገባ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው አጋርተዋል።
ዘገባው "ሊበራል ፕሮግራሞችን ለማስተግበር በሜኒሶታ በሶማሌ ስደተኞች የተፈጸመ ትልቅ ምዝበራ በዴሞክራት ፓርቲ ከሽፏል" ይላል።
የተመዘበረው ገንዝብ ወደ ኬንያ እና ሶማሊያ እንደተላከ እና ይህም ከአል ቃይዳ ጋር ትስስር ወዳለው አል ሸባብ እንደደረሰ ዘገባው ይጠቁማል።
ዘገባው ስማቸው ያልተጠቀሰ ባለሥልጣናት ለኮንግረስ ቃላቸውን መስጠታቸውንም ጠቅሷል።
የትራምፕ አስተዳደር ኤርትራ፣ ሶማሊያ እና ሱዳንን ጨምሮ የ19 አገራት ዜጎችን የመኖሪያ እና የሥራ ፈቃድ ሊመረምር እንደሆነ ከቀናት በፊት ማስታወቁ ይታወሳል።
የአገሪቱ የዜግነት እና የኢሚግሬሽን አገልግሎት ኃላፊ ጆሴፍ ኤድሎው እንዳሉት ፕሬዝዳንት ትራምፕ "አሳሳቢ ከሆኑ አገራት የመጡ ስደተኞች በሙሉ የመኖሪያ እና የሥራ ፈቃዳቸው፣ በጥብቅ እንደገና እንዲመረምር" መመሪያ ሰጥተዋል።
ኤርትራ፣ ሶማሊያ፣ ሱዳን፣ ሊቢያ፣ ዴሞክራቲክ ኮንጎ፣ አፍጋኒስታን፣ የመን፣ ኩባ፣ ሄይቲ፣ ኢራን እና ቬንዙዌላን በዝርዝሩ ተካትተዋል።
ይህ ትዕዛዝ የተላለፈው አንድ አፍጋኒስታናዊ ባለፈው ሳምንት በዋሽንግተን ዲሲ ሁለት የብሔራዊ ዘብ አባላት ላይ ተኩሶ ከባድ ጉዳት ካደረሰባቸው በኋላ ነው።
ዘገባው ገንዘቡ ወደ አልሻባብ መተለለፉን በተመለከተ ላነሳው ክስ ከገለልተኛ ወገን ማስረጃ አላቀረበም። የአሜሪካ መንግሥትም የክሱን ትክክለኛነት አላረጋገጠም።
የሶማሊያ መንግሥት እስካሁን ድረስ ለትራምፕ ንግግር በይፋ ምላሽ አልሰጠም።
አል ሻባብ ባለፈው ሳምንት ባወጣው መግለጫ የአሜሪካን ክስ አስተባብሏል። የቡድኑን አስተያየት በተመለከተ ቢቢሲ በገለልተኛ ወገን አላጣራም።
በአሜሪካ ያሉ ሲቪል ማኅበራት የትራምፕ አስተያየት ሶማሌ-አሜሪካዊ ማኅበረሰቦች ላይ ጉዳት እንደሚያደርስ ገልጸዋል።
ባለንበት 2025 'ካውንስል ኦን አሜሪካን ኢስላሚክ ሪሌሽንስ' የተባለው የመብት ተሟጋች በማኅበረሰቡ አባላት ላይ መገለል መድረሱን አስታውቋል።















