ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ውጊያው በቀጠለባት ሱዳን አገራት ዲፕሎማቶቻቸውን እያስወጡ ነው
በሱዳኗ ዋና ከተማ በተቀናቃኝ ኃይሎች መካከል የሚካሄደው ውጊያ በቀጠለበት በአሁኑ ጊዜ በርካታ አገራት ዜጎቻቸውን ከካርቱም ማስወጣታቸውን ቀጥለዋል።
አሜሪካ እና ዩናይትድ ኪንግደም እሁድ ዕለት ዲፕሎማቶቻቸውን በአውሮፕላን ከአገሪቱ አስወጥተዋል።
ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ጣሊያን እና ስፔን በበኩላቸው ዲፕሎማቶቻቸውን እና ሌሎች ዜጎቻቸውን በማስወጣት ላይ ናቸው።
ከአንድ ሳምንት በፊት ተጀምሮ አገሪቱን ቀውስ ውስጥ የከተተው ግጭት፣ በዋነኞቹ ጄኔራሎች በሚመሩት በሱዳን ሠራዊት እና በፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች መካከል እየተካሄደ ነው።
የአሜሪካ ባለሥልጣናት እሁድ ጠዋት ከ100 ያነሱ ሰዎችን ቺኒክ በተባሉ ሦስት ሄሊኮፕተሮች “በፍጥነት ያለምንም ችግር” ማስወጣት መቻላቸውን አሳውቀዋል።
በካርቱም የሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ አሁን የተዘጋ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ሌሎች የአሜሪካ ዜጎችን ከሱዳን ለማስወጣት አስተማማኝ ሁኔታ እንደሌለ በትዊተር ገጹ ላይ ኤምባሲው አመልክቷል።
የዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) “ውስብስብ እና ፈጣን” በሆነ ሁኔታ ዲፕሎማቶቿን እና ቤተሰቦቻቸውን ማስወጣት እንደቻለች ገልጻለች። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጄምስ ክሌቨርሊ እንዳሉት የቀሩ የብሪታኒያ ዜጎችን ከሱዳን ለማስወጣት “በጣም ውስን” ሁኔታ እንዳለ አመልክተዋል።
የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኢማኑአኤል ማክሮን ከሱዳን ፈረንሳይ ዜጎችን ይዞ የወጣ አውሮፕላን እሁድ ዕለት ጂቡቲ መድተረሱን ገልጸው፣ ይኸው ተግባር ሰኞ ቀጥሎ በአጠቃላይ አስካሁን 388 ሰዎች እንደወጡ ተናግረዋል።
በተጨማሪም የተወሰኑ የኔዘርላንድስ ዜጎች በፈረንሳይ አውሮፕላን የወጡ ሲሆን፣ የጀርመን ሠራዊት ደግሞ 101 ሰዎችን ያሳፈሩ ሦስት አውሮፕላኖች ከካርቱም በመውጣት ወደ ዮርዳኖስ ተጉዘዋል።
የጣሊያን፣ የስፔን፣ የአርጀንቲና፣ የፖርቱጋል፣ የፖላንድ፣ የሜክሲኮ፣ የቬንዙዌላ፣ የካናዳ፣ የቱርክ፣ ግብፅ፣ ፓኪስታን፣ ሳዑዲ አረቢያ እና የሌሎችም አገራት ዲፕሎማቶች ከካርቱም በተለያዩ አገራት አውሮፕላኖች እንዲወጡ ተደርገዋል።
ነገር ግን ስድስት ሚሊዮን ነዋሪ ባለበት ካርቱም ውስጥ የሚገኙ ከተለያዩ የአፍሪካ፣ የመካከለኛው መሥራቅ እና የእስያ አገራት የመጡ ተማሪዎች ለመውጣት እየጠየቁ ነው።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በሱዳን ውስጥ የኢንተርኔት አገልግሎት መቋረጡን ኔተብሎክስ የተባለው ተቋም ገልጿል። ሁለት በመቶ ብቻ የኢንተርኔት ትስስር ባላት ሱዳን ውስጥ የአገልግሎቱ መቋረጥ፣ ከካርቱም እና ከሌሎች አካባቢዎች መውጣት የሚፈልጉ ሰዎችን ለመርዳት አዳጋች ያደርገዋል ተብሏል።
በሁለቱ ኃይሎች መካከል የበላይነትን ለማግኘት በሚካሄደው ፍልሚያ በዋና ከተማዋ ውስጥ የአየር ድብደባ ጭምር እንዲካሄድ አድርጓል። አስካሁን በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የተገደሉ ሲሆን፣ በርካታ ሺዎች ደግሞ ጉዳት ደርሶባቸዋል።
በካርቱም እና በሌሎችም ከተሞች ውስጥ እየተካሄደ ባለው ወታደራዊ ግጭት እና የአየር ድብደባ የኤሌክትሪክ አገልግሎት የተቋረጠ ሲሆን፣ አብዛኛው ነዋሪ የምግብ እና የውሃ አቅርቦት ችግር አጋጥሞታል።
የኢድ በዓልን ጨምሮ በተደጋጋሚ ተፋላሚ ኃይሎቹ የተኩስ አቁም ለማድረግ ቢስማሙም ውጤታማ ሳይሆን ውጊያው ቀጥሏል።