ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ፍልስጤማዊ ታሪክን የሚያሳይ ፊልምን የሸለመው የእስራኤል ሽልማት ድርጅት ከሀገሪቱ መንግስት ማስጠንቀቂያ ተሰጠው
'ዘ ሲ' ለተባለ እና ስለ 12 ዓመት ፍልስጤማዊ ልጅ የሚተርክ ፊልም የእስራኤልን ብሔራዊ የፊልም ሽልማትን ማሸነፉን ተከትሎ የሀገሪቱ የባህል ሚኒስትር ለሸላሚው ድርጅት የሚሰጠውን የገንዘብ ድጋፍ ለማቋረጥ ዛቱ።
እስራኤል ውስጥ የኦስካር አቻ ተደርጎ የሚቆጠረውን "ኦፈር አዋርድስ" በተባለው ዝግጅት ላይ በምርጥ ፊልም ዘርፍ ያሸነፈው ይህ ስራ በተወረረው ዌስት ባንክ የሚኖር እና ለመጀመሪያ ጊዜ ባህር ለመመልከት ወደ ቴል አቪቭ መጓዝ የሚፈልግ ታዳጊ ዙሪያ የሚያጠነጥን ነው።
የባህል ሚኒስትሩ ሚኪ ዞሃር በኤክስ ገጻቸው ባወጡት መግለጫ፤ "ከአሳፋሪው እና ከተገለለው ዓመታዊ የኦፈር አዋርድስ ስነ ስርዓት በበለጠ የእስራኤል ዜጎችን ፊት በጥፊ የመታ የለም" ብለዋል።
'ዘ ሲ' የተባለው ፊልም የኦፈር አዋርድስ የምርጥ ፊልም ዘርፍ አሸናፊ መሆኑን ተከትሎ በሚቀጥለው የአውሮፓውያን ዓመት በሚካሄደው የኦስካር ሽልማት ላይ በዓለም አቀፍ ፊልም ዘርፍ በእስራኤል በእጩነት የሚቀርብ ስራ ሆኗል።
ይሁን እንጂ ሚኒስትሩ ለሽልማት ስነ ስርዓቱ የሚሰጥ የገንዘብ ድጋፍን የማቋረጥ ስልጣን ይኖራቸው እንደሆነ ግልጽ አለመሆኑን የሀገሪቱ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
በ13 ዓመቱ የምርጥ ወንድ ተዋናይነት ሽልማትን በማሸነፍ በእድሜ ትንሹ ተሸላሚ የሆነውን ሙሀመድ ጋዛዊን ጨምሮ 'ዘ ሲ' ፊልም ላይ የተሳተፉ ተዋናዮች የስነ ስርዓቱን ዋነኛ ሽልማቶች አግኝተዋል።
ጋዛዊ በፊልሙ ላይ፤ ወደ ቴል አቪቭ በሚደረግ የተማሪዎች ጉዞ ወቅት በእስራኤል መከላከያ ሰራዊት ፍተሻ ቦታ ላይ ወደ እስራኤል መግቢያ ቪዛ የተከለከለውን ካህሊድ የተባለ የ12 ዓመት ልጅ ታዳጊ ገጸ ባህሪን ተጫውቷል።
ከዚያም ካህሊድ ተደብቆ ወደ እስራኤል በመግባት ባህሩን ለማየት የሚሞክር ሲሆን እስራኤል ውስጥ ሰነድ አልባ ሰራተኛ የሆነው አባቱ ደግሞ ሊያገኘው የሚያደርገው ጥረት በፊልሙ ይታያል።
በሽልማት ስነ ስርዓቱ ላይ ንግግር ያደረገው የፊልሙ ፕሮዲዩሰር ባኸር አግባሪያ፤ ፊልሙ "ሁሉም ሕፃናት በሰላም የመኖር እና መሰረታዊ መብት ስለሆነው ተስፋ አለመቁረጥ" የሚተርክ እንደሆነ ገልጿል።
የእስራኤል አካዳሚ ኦፍ ፊልም ኤንድ ቴሌቪዥን ሊቀ መንበር አሳፍ አሚር ለባህል ሚኒስትሩ መግለጫ በሰጠው ምላሽ፤ "ማለቂያ አልባ የሆነው የጋዛ ጦርነት ያስከተለው የሞት ቁጥር እና ውድመት አስከፊ በሆነበት [ወቅት] 'ሌላውን' መመልከት መቻል... ትንሽ ተስፋን ይሰጣል" ብሏል።
አሚር አክሎም፤ "የእስራኤል መንግስት በእስራኤል ሲኒማ እና ባህል ላይ ጥቃት እያደረሰ ባለበት እና ዓለም አቀፉ የፊልም ማህበረሰብ እኛ ጋ እንዳይሳተፍ ጥሪ እየተደረገ ባለበት ጊዜ ዘ ሲ መመረጡ ኃይለኛ እና ከፍተኛ ምላሽ ነው" ሲል ምላሽ ሰጥቷል።
ይህ አስተያየት የተሰጠው በሺዎች የሚቆጠሩ የሆሊውድ ባለሙያዎች "ከዘር ማጥፋት ጋር ተያይዘዋል" ካሏቸው የእስራኤል የፊልም ተቋማት ጋር ላለመስራት መፈረማቸውን ተከትሎ ነው።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መርማሪ ኮሚሽን ማክሰኞ ዕለት በሰጠው መግለጫ እስራኤል ጋዛ ውስጥ ባሉ ፍልስጤማውያን ላይ ዘር ማጥፋት መፈጸሟን ገልጿል። ይህንን ሪፖርት የተቃወመው የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ውንጀላውን "የተዛባ እና ሐሰተኛ" ሲል ጠርቶታል።