የኳታር አየር መንገድ ከጥንድ ተጓዦች አጠገብ ሬሳ በማስቀመጡ ይቅርታ ጠየቀ

የካታር ኤርዌይስ አውሮፕላን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

አውስትራሊያዊያኑ ጥንዶች በኳታር አየር መንገድ አውሮፕላን እየተጓዙ ሳለ አጠገባቸው ሬሳ በመቀመጡ "እጅግ መደናገጣቸውን" ተናገሩ።

ሚቼል ሪንግ እና ጄኒፈር ኮሊን ለሽርሽር በሚል ነው ወደ ጣሊያኗ ቬኒስ ከተማ ለማቅናት የተነሱት።

ነገር ግን ከሜልበርን ወደ ዶሀ በነበረው ጉዞ አንዲት መንገደኛ መሞቷን ተከትሎ ሬሳዋ አጠገባቸው እንዲቀመጥ ተደርጓል።

በወቅቱ ያደረባቸውን ድንጋጤና ፍርሀት ቻነል 9 ለተሰኘው የአውስትራሊያ ቴሌቪዥን ጣቢያ ያጋሩት ጥንዶቹ የአውሮፕላኑ ሠራተኞች የሟቿን ሬሳ በአንሶላ ሸፍነው ከሚቼል ሪንግ አጠገብ ካለው ወንበር ማስቀመጣቸውን ተናግረዋል።

ጥንዶቹ እንደሚሉት ምንም እንኳ ከእነሱ ወንበር ተሻግሮ ባለው ክፍል ክፍት ወንበር ቢኖርም የበረራ አስተናጋጆች ሬሳውን ያስቀመጡት አጠገባቸው ነው።

ኳታር ኤርዌይስ "ለተፈጠረው ችግር እና መንገዶቹ ለደረሰባቸው ድንጋጤ" ይቅርታ ጠይቆ መንገደኞችን በማፈላለግ ላይ እንደሆነ አስታውቋል።

ጥንዶቹ እንደሚሉት ኳታር ኤርዌይስም ሆነ ካንታስ የተባለው ቲኬት የቆረጠቡት ኩባንያ ሊያገኟቸው አሊያም ድጋፍ ሊያደርጉላቸው አልሞከሩም።

ሚቼል ሪንግ እንደሚለው ምንም እንኳ የበረራ አስተናጋጆቹ የሟቹን ሕይወት ለማትረፍ ደፋ ቀና ቡሉም "ሊያተርፏት አልቻሉም።"

ሪንግ፤ ግለሰቧ ስትሞት በረራ ላይ በነበረው አውሮፕላን ውስጥ የነበረው ሁኔታ "በጣም ልብ የሚነካ ነበር" ይላል።

አክሎ የበረራ አስተናጋጆች ሬሳዋን ወደ 'ቢዝነስ ክላስ' ሊወስዱት ቢሞክሩም "በጣም ከባድ ከመሆኗ የተነሳ ሊያጓጉዟት አልቻሉም።"

"ከዚያ «ጠጋ ትልልናለህ?» ሲሉኝ በድንጋጤ እሺ ችግር የለም አልኳቸው" ሲል ታሪኩን ይናገራል።

ጥንዶቹ እንደሚሉት ከቆይታ በኋላ ባደረባቸው ድንጋጤ ምክንያት ክፍት የሆነ መቀመጫ ፈልገው ከሬሳው ራቅ ብለው ተቀምጠዋል።

አውስትራሊያዊያኑ የበረራ አስተናጋጆች ለምን ሬሳውን ክፍት መቀመጫ ላይ አላደረጉትም አሊያም እኛን ወደ ሌላ ወንበር አላዛወሩንም ሲሉ ይወቅሳሉ።

ጄኒፈር ኮሊን በበኩሏ "አየር መንገዱ በግለሰቧ ሞት ተጠያቂ ባይሆን መሰል ሁኔታዎች ሲከሰቱ መንገደኞችን እንዴት መንከባከብ እንዳለበት አሠራር ሊኖረው ይገባል" ስትል ወቅሳለች።

ካታር ኤርዌይስ በለቀቀው መግለጫ በረራ ላይ ሳለች ሕይወቷ ላለፈው ግለሰብ ቤተሰቦች መፅናናትን ተመኝቶ "በሁኔታው ምክንያት ድንጋጤ ውስጥ ለገቡ መንገደኞች ይቅርታ እንጠይቃለን" ብሏል።

አየር መንገዱ አክሎ በረራው ላይ የነበሩ መንገደኞችን ለማግኘት ሙከራ እያደረገ እንደሆነ አስታውቋል።