ከኢትዮጵያ ድንበር አቅራቢያ ደቡብ ሱዳን ውስጥ በሆስፒታል ላይ የአየር ጥቃት ተፈጸመ

በአየር ጥቃት የወደመው ስፍራ

የፎቶው ባለመብት, MSF

የምስሉ መግለጫ, በአየር ጥቃት የወደመው ሥፍራ
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

ደቡብ ሱዳን ከኢትዮጵያ ጋር ከምትዋሰንበት ድንበር አቅራቢያ በሚገኝ ግዛት ውስጥ የአየር ጥቃት ከተፈጸመ በኋላ ቁጥራቸው በውል ያልታወቀ የእርዳታ ሠራተኞች የደረሱበት እንዳልታወቀ ኤምኤስኤፍ አስታወቀ።

በደቡብ ሱዳን ጆንግሌ ግዛት ውስጥ በሚገኘው በድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን (ኤምኤስኤፍ) የሚመራው ሆስፒታል ማክሰኞ ምሽት ላይ "በደቡብ ሱዳን መንግሥት ኃይሎች የአየር ጥቃት ተፈጽሞበታል" ሲል የእርዳታ ድርጅቱ ገልጿል። የደቡብ ሱዳን መንግሥት ግን እስካሁን ምንም ዓይነት አስተያየት አልሰጠም።

እዚያው ጆንግሌ ግዛት ውስጥ ፔሪ በተባለ ሥፍራ በሚገኝ የጤና ተቋም ላይ በተመሳሳይ ቀን ማንነታቸው ባልታወቁ ታጣቂዎች በተፈጸመ ሌላ ጥቃት ዝርፊያ ተፈጽሞ ተቋሙ "ለአካባቢው ማኅበረሰብ ጥቅም የማይሰጥ" እንዲሆን ተደርጓል ሲል ኤምኤስኤፍ ገልጿል።

"ባልደረቦቻችን ጥቃቱን በመፍራት ከማኅበረሰቡ ጋር አካባቢውን ለቅቀው በመሸሻቸው ምን እንዳጋጣቸው እና የት እንዳሉ እስካሁን አይታወቅም" ሲል የሕክምና ተራድኦ ድርጅቱ አስታውቋል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በመንግሥት ኃይሎች እና ፕሬዝዳንት ሳልፋ ኪርን ለመገልበጥ በማሴር ከሥልጣናቸው ለተነሱት ለምክትል ፕሬዝዳንትን ሪክ ማቻር ታማኝ በሆኑ ኃይሎች መካከል በጆንግሌ ግዛት ውስጥ ውጊያዎች እየተካሄዱ ነው።

እነዚህም ግጭቶች ከሱዳን ተለይታ አዲስ አገር በሆችው ደቡብ ሱዳን ውስጥ የእርስ በርስ ጦርነት መልሶ እንዲያገረሽ ያደርጋል የሚል ስጋት ፈጥሯል።

ከፍተኛ የምግብ እጥረት ካላባቸው የደቡብ ሱዳን ክፍሎች መካከል አንዱ በሆነው ጆንግሌ ውስጥ ከፍተኛ የጤና አገለግሎት ፍላጎት ያለ ሲሆን፣ ካለፈው ታኅሣሥ ወር ወዲህ በተካሄዱ ውጊያዎች እና የአየር ድብደባዎች 280 ሺህ የሚገመቱ ሰዎች መፈናቃላቸውን የተበባሩት መንግሥታት ድርጅት ገልጿል።

ኤምኤስኤፍ እንዳስታወቀው ማክሰኞ ዕለት ከተፈጸመው የመጀመሪያው ጥቃት ቀደም ብሎ ጥቃት ሊፈጸም እንደሚችል መረጃ ደርሶት ነበረ፤ በዚህም ምክንያት "ከጥቃቱ ከሰዓታት በፊት ሕመምተኞች እና ሠራተኞች ለቅቀው እንዲወጡ ተደርጓል።"

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

"አንድ የሆስፒታሉ ሠራተኛ ቆስሏል እንዲሁም የሆስፒታሉ ዋነኛ መጋዘን በውስጡ ከነበሩ የሕክምና አቅርቦቶች ጋር ወድመወል" ሲል ድርጅቱ ባወጣው መለግጫ ላይ አመልክቷል።

ጥቃቱ የተፈጸመበት ጆንግሌ ውስጥ የሚገኘው ላንኪን የተባለው አካባቢ በመንግሥት እና በተቃዋሚዎች መካከል አዲስ የተቀሰቀሰው ውጊያ ማዕከል ነው።

"በጥቃቱ ወቅት የሆስፒታሉ ዋነኛ መጋዘን በመውደሙ የሕክምና አገልግሎት ለመስጠት የሚያስፈልጉን በጣም ወሳኝ የሆኑ ነገሮችን አጥተናል" ሲል ኤምኤስኤፍ ጨምሮ ገልጿል።

ከጥቃቱ ጀርባ ማን እንዳለ ወዲያውኑ የታወቀ ባይሆንም ኤምኤስኤፍ ግን "በአገሪቱ ውስጥ የአየር ጥቃት የመፈጸም አቅም ያለው የደቡብ ሱዳን ጦር ኃይል ብቻ ነው" ሲል የአገሪቱን ሠራዊት ከስሷል።

የሕክምና እርዳታ ድርጅቱ እንደሚለው ጥቃቶቹ በተፈጸመባቸው ላንኪን እና ፔሪ በተባሉት ሥፍራዎች ለ250 ሺህ ሰዎችን የጤና አገለግሎት በመስጠት ብቸኛው በመሆኑ ተቋሞቹን ማጥቃት ማለት "የአካባቢው ማኅበረሰብን ያለ ምንም ጤና አገለግሎት የሚያስቀር ነው" በማለት አስጠንቅቋል።

"ለጤና አገልግሎት ሰፊ ፍላጎት ባለበት በአገሪቱ ውስጥ የጥቃት ዒላማ መሆን ተቀባይነት የሌለው ነው" ሲሉ የድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን ኦፕሬሽን ማኔጀር ጉል ባድሻህ ተናግረዋል።

ባለፈው የአውሮፓውያን ዓመት ስምንት ጥቃቶች እንደተፈጸሙበት እና በዚህም ምክንያት በግሬተር አፐር ናይል ግዛት ውስጥ ሁለት ሆስፒታሎች ሲዘጉ፤ በጆንግሌ፣ በአፐር ናይል እና ሴንትራል ኢኳቶሪያል ግዛቶች ውስጥ ደግሞ አጠቃላይ የጤና አገልግሎቶች ተቋርጠዋል።

በታኅሣሥ ወር የደቡብ ሱዳን መንግሥት በተቃዋሚዎች ቁጥጥር ሥር በሚገኙ ጆገግሌ ግዛት ውስጥ የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት ላይ እቀባ ጥሏል። ይህም የኤምኤስኤፍን አስፈላጊ የጤና አገልግሎት የመስጠት አቅም ውስን አድርጎታል።

ደቡብ ሱዳን ነጻ አገር ከሆነች ከሁለት ዓመት በኋላ በማቻር እና በኪር ታማኝ ተዋጊዎች መካከል የመጀመሪያው የእርስ በርስ ጦርነት በአውሮፓውያኑ 2013 ተቀስቅሶ ነበር።

የእርስ በርስ ጦርነቱ 400,000 የሚሆኑ ሰዎችን ለሞት ከዳረገ በኋላ በ2018 በሁለቱ መሪዎች መካከል በተደረሰ የሰላም ስምምነት ቢቆምም፤ በተቀናቃኝ ፖለቲከኞቹ መከካል ያለው ግንኙነት ሳይሻሻል በጎሳዎች መካከል ውጥረት እና ግጭቶችን እየፈጠረ እስካሁን ቆይቷል።