እስራኤል 37 ዓለም አቀፍ የረድኤት ድርጅቶችን ከጋዛ ልታባርር ነው

በጡጦ ውስጥ ውሃ የምትሞላ ሴት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

እስራኤል አዲስ ያወጣችውን ሕግ አላሟሉም ያለቻቸውን በጋዛ እና በወረራ በያዘችው ዌስት ባንክ የሚሰሩ 37 የረድኤት ድርጅቶችን ፈቃድ ልትሰርዝ ነው።

እንደ አክሽን ኤድ፣ ዓለም አቀፉ የነፍስ አድን ድርጅት እና የኖርዌይ የስደተኞች ድርጅት የመሳሰሉ ታዋቂ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ከአውሮፓውያኑ አዲስ ዓመት የመጀመሪያ ቀን ጀምሮ ፈቃዳቸውን ከሚነጠቁት ውስጥ ናቸው።

ይህንን ውሳኔ ተከትሎ ድርጅቶቹ ሥራቸውን በ60 ቀናት ውስጥ ያቆማሉ ተብሏል።

እስራኤል ከሌሎች ጉዳዮች በተጨማሪ የረድኤት ድርጅቶቹ የሠራተኞቻቸውን "ሙሉ" ዝርዝር ማቅረብ አልቻሉም ብላለች።

እርምጃውን የዩናይትድ ኪንግደም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርን ጨምሮ የ10 አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ክፉኛ ተችተውታል።

የዩኬ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አዲሱን ሕግ "አፋኝ" እና "ቅቡልነት የሌለው" ብለውታል።

ዩኬ፣ ፈረንሳይ፣ ዴንማርክ፣ ፊንላንድ፣ አይስላንድ፣ ጃፓን፣ ኖርዌይ እና ስዊዘርላንድ በጋራ መግለጫቸው ዓለም አቀፍ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን በግዴታ መዝጋት "የጤና አገልግሎቶችን ጨምሮ መሠረታዊ አገልግሎቶች ላይ ትልቅ ተፅዕኖ ይኖረዋል" ብለዋል።

በጋዛ የሰብዓዊ ሁኔታ ቀውሱ "አስከፊ" ሆኖ መቀጠሉን የጠቀሱት አገራቱ፤ የእስራኤል መንግሥት የረድኤት ድርጅቶቹ "ዘላቂ እና ተገማች በሆነ መንገድ" እንዲሰሩ ሊያደርግ ይገባል ብለዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የረድኤት ድርጅቶች ምዝገባ ኃላፊነት ያለበት የእስራኤል የዲያስፖራ ጉዳዮች ሚኒስቴር አዲሱ እርምጃ ለጋዛ በሚቀርበው የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት ላይ ተፅዕኖ እንደማይኖረው ገልጿል።

የሰብዓዊ እርዳታ "በተፈቀደ እና ምርመራ በተካሄደባቸው መንገዶች" በመንግሥታቱ ድርጅት ኤጄንሲዎች፣ በአጋሮች እና በረድኤት ድርጅቶች መቅረቡን ቀጥሏል ብሏል።

የረድኤት ድርጅቶቹ ፈቃድ የሚሰረዝበት ዋነኛው ምክንያት ሙሉ ለሙሉ እና መረጋገጥ የሚችል የሠራተኞቻቸውን መረጃ ለማቅረብ አሻፈረኝ በማለታቸው" እንደሆነ ገልፆ፤ መረጃው በሰብዓዊ እርዳታ መዋቅር ውስጥ አሸባሪዎች ሰርገው እንዳይገቡ" ለመከላከል ወሳኝ ነው ብሏል።

በቅርቡ የመንግሥታቱ ድርጅቶች ባለሙያዎች በእስራኤል እና በሀማስ መካከል የተኩስ አቁም ስምምነት ከተደረሰ ወዲህ በጋዛ የሚቀርበው የሰብዓዊ ምግብ አቅርቦት መሻሻሉን አስታውቀዋል።

ይሁን እንጂ በአሁኑ ወቅት 100 ሺህ ሰዎች "በአሳሳቢ ሁኔታ" ውስጥ ይገኛሉ።

ወደ ጋዛ የሚያስገባውን መንገድ የሚቆጣጠር የእስራኤል ጦር አካል 'ካጎት' የሚሰረዙት የረድኤት ድርጅቶች አሁን ባለው የተኩስ አቁም ወደ ጋዛ እርዳታ አላስገቡም ብሏል።

"ከዚህ ቀደም እንኳ ከአጠቃላይ የእርዳታ አቅርቦቱ አንድ በመቶ የሚሆነውን የሚሸፍኑ አይደሉም" ሲል አክሏል።

የእስራኤል ዲያስፖራ ጉዳዮች ሚኒስቴር እንዳለው ለጋዛ የሰብዓዊ እርዳታ ከሚያቀርቡ የረድኤት ድርጅቶች ውስጥ 15 በመቶ የሚሆኑት አዲሱን ሕግ ጥሰው ተገኝተዋል።

በአዲሱ ሕግ ከተዘረዘሩት ውስጥ እሰራኤል አይሁድ እና ዲሞክራሲያዊት አገር ህልውናዋን መካድ፣ የጥቅምት ሰባቱን ሀማስ መር ጥቃት አሊያም የአይሁዳዊያን ጭፍቸፋን መካድ፣ በጠላት አገራት አሊያም በአሸባሪዎች የሚደረግን የትጥቅ ትልግ መደገፍ፣ የእስራኤልን ቅቡልነት ለማሳጣት በዘመቻ መሳተፍ እና የእስራኤል የፀጥታ ኃይል በውጭ ወይም በዓለም አቀፍ ፍርድ ቤቶች እንዲከሰስ መደገፍ የሚሉት ይገኙበታል።

የተመድ ኤጄንሲዎችን ጨምሮ 200 የአገር ውስጥ እና ዓለም አቀፍ የረድኤት ድርጅቶችን ያቀፈው 'የፍልስጤም የሰብዓዊ ቡድን' ከዚህ ቀደም በሰጠው አስተያየት አዲሱን ሕግ በጋዛ እና በዌስት ባንክ የረድኤት ድርጅቶችን ሥራ "በመሠረታዊነት አደጋ ላይ የሚጥል" ብሎታል።