የሕገ መንግሥት ጥያቄ የቀረበበት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት ወንበር ድልድል "ያለ አዋጅ ማሻሻያ" ተቀየረ

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ አሻድሊ ሀሰን፣ የምክር ቤት አፈ ጉባኤ አስካለች አልቦሮ እና ምክትል አፈ ጉባኤ መለሰ ኪዊ

የፎቶው ባለመብት, Ashadeli Hassen

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት፤ ለሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ አቤቱታ የቀረበበትን የምርጫ ክልሎችን በአዲስ መልኩ የሚያዋቅር አዋጅ "ለማሻሻል" የሚያስችል ውሳኔ ማጽደቁን ሦስት ተወካዮች ለቢቢሲ ተናገሩ።

በአዲሱ ውሳኔ መሠረት ከ99 ወደ 165 ያደገው የክልሉ ምክር ቤት መቀመጫ እንደ አዲስ ለተዋቀሩት የምርጫ ክልሎች መደልደሉ ቀርቶ ለነባሮቹ ምርጫ ክልሎች እንዲከፋፈል ተደርጓል።

የክልሉ ምክር ቤት ከዚህ ቀደም በአዋጅ ያጸደቀውን የምርጫ ክልል አወቃቀር የሚያስቀረውን ይህንን ውሳኔ ያሳለፈው፤ "የአዋጅ ማሻሻያ ሳይቀርብ በቃል በቀረበ ገለጻ" ላይ ተመሥርቶ መሆኑን የምክር ቤቱ አባላት ገልጸዋል።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት፤ ምርጫ ክልሎች የሚኖራቸውን የሕዝብ ተወካዮች ብዛት ያሳደገውን ይህንን ውሳኔ ያጸደቀው ባለፈው ሳምንት እሁድ ሐምሌ 20/2017 ዓ.ም. ባደረገው መደበኛ ጉባኤ ላይ ነው። ውሳኔው ለምክር ቤት አባላት የተገለጸው ለሁለት ቀናት በቆየው ጉባኤ ማጠናቀቂያ ላይ እንደሆነ ቢቢሲ ያነጋገራቸው የምክር ቤቱ አባላት ገልጸዋል።

በጉባኤው ላይ የሌሎች አራት አዋጆች ረቂቅ ለምክር ቤት አባላት ከተሠራጨ በኋላ መጽደቃቸውን የሚናገሩት የምክር ቤት አባላቱ፤ ሌላኛው ውሳኔ ግን በስብሰባው አጀንዳ ላይ በግልጽ አለመጠቀሱን አስረድተዋል።

የተቃዋሚው የቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ቦዴፓ) ተመራጭ የሆኑት የምክር ቤት አባሉ አቶ ተስፋሁን እንደሚናገሩት፤ ይህ ጉዳይ በምክር ቤቱ አጀንዳ ላይ የተጠቀሰው "ውሳኔ የሚፈልጉ ጉዳዮችን መርምሮ ማጽደቅ" በሚል ነበር።

ይህ የአዋጅ ማሻሻያ የውሳኔ ሀሳብ ሲቀርብ ለምክር ቤቱ አባላት በጽሁፍ የደረሰ ረቂቅም እንዳልነበረ አቶ ተስፋሁን እንዲሁም የጉሙዝ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄን (ጉሕዴን) ተመራጭ የሆኑት የምክር ቤት ተወካዮች አቶ ግራኝ ጉደታ እና አቶ ለሜሳ ናኖ ገልጸዋል።

የውሳኔው ይዘት ለምክር ቤት አባላቱ የተገለጸው በክልሉ የአስተዳደር ምክር ቤት የሕግ አማካሪ አማካኝነት እንደሆነ ተነግሯል። በዚህ መልኩ የውሳኔ ሀሳብ የቀረበበት አወዛጋቢ አዋጅ የጸደቀው የካቲት ላይ ነበር።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ምክር ቤቱ በወቅቱ ባደረገው ጉባኤ ከዚህ አዋጅ በተጨማሪ፤ የክልሉን ምክር ቤት ወንበር ብዛት ከ99 ወደ 165 ያሳደገውን አዋጅም አጽድቆ ነበር። ብዛቱ ያደገው የምክር ቤቱ ወንበር እንዴት እንደሚደለደል የተወሰነው ደግሞ "የየእርከኑ ምክር ቤት ተወካዮች ብዛት ለመወሰን" በሚል በጸደቀው አዋጅ ነው።

ይህ አዋጅ ከዚህ ቀደም ከአራት እስከ ስድስት የነበረውን ከአንድ ምርጫ ክልል የሚመረጡ ተወካዮች ብዛት ከአምስት እስከ 11 አድርሷል። በተጨማሪም አዋጁ በአሶሳ ዞን የነበሩ ሦስት ነባር የምርጫ ክልሎችን እንደ አዲስ በማዋቀር ወደ አምስት ቀይሯቸዋል።

አዲስ የተቋቋሙት የምርጫ ክልሎች አብራሞ፣ ኡራ፣ ኡንዱሉ፣ አሶሳ ከተማ ወረዳ አንድ እና አሶሳ ከተማ ወረዳ ሁለት ናቸው።

በሕገ መንግሥት ማሻሻያው እና በአዋጁ ላይ የጸደቁ እነዚህ አሠራሮች ግን የተቃዋሚው የቦሮ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ተመራጭ በሆኑ ሦስት የክልሉ ምክር ቤት አባላት ተቃውሞ ገጥሞታል።

የምክር ቤት አባላቱ በፌደራል ደረጃ ላለው የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ ባቀረቡት አቤቱታ፤ ሁለት አዋጆች "ኢ-ሕገ መንግሥታዊ፣ ያልነበሩ፣ ያልተደነገጉ እንዲባሉ" እና "ተፈጻሚ እንዳይሆኑ" ተብሎ እንዲወሰን ጠይቀዋል።

ሦስቱ ተመራጮች ለዚህ ጥያቄያቸው በምክንያትነት የጠቀሱት አንዱ ምክንያት የምክር ቤቱ ወንበር ከ99 ወደ 165 ያደገበት መንገድ "የሕዝብ ብዛትን ያላማከለ" ነው የሚል ነው።

"ነባር ምርጫ ክልሎች የፈረሱበት እና አዳዲስ ምርጫ ክልሎች የተቋቋሙበት ሂደትም ሕገ መንግሥቱን የጣሰ" እንደሆነም በአቤቱታቸው ላይ ገልጸዋል። በተጨማሪም የምርጫ ክልሎችን የማዋቀር ሥልጣን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እንጂ የክልሉ ምክር ቤት አለመሆኑን በመጥቀስ ተችተዋል።

ይህ አቤቱታ በሂደት ላይ ነው። አቤቱታውን ካቀረቡት የምክር ቤት አባላት መካከል አንዱ የሆኑት አቶ ዮሐንስ ተሰማ ጥያቄው ከቀረበ ከቀናት በኋላ በቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆን ላለፉት አምስት ወራት በእስር ላይ ናቸው።

በእሁድ ዕለቱ የክልሉ ምክር ቤት ጉባኤ ላይ አዲሱ ውሳኔ ለመቅረቡ ከተጠቀሱ ምክንያቶች መካከል አንዱ፤ የምርጫ ክልሎች እንደ አዲስ መዋቀሩ በምርጫ ቦርድ ተቀባይነት አለማግኘቱ እንደሆነ አቶ ተስፋሁን ገልጸዋል።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ አሻድሊ ሀሰን

የፎቶው ባለመብት, Benishangul Gumuz Region Communication

"ምርጫ ቦርድ [በአዋጁ መሠረት] አዳዲስ የምርጫ ክልሎችን እንዲያካልልን ጠይቀን ነበር። ምርጫ ቦርድ ግን የእናንተ ጥያቄ ብቻ አይደለም፤ የሌሎች ክልሎችም ጥያቄ ስላለ ይህንን ጥያቄ አሁን አናስተናግድም ብለው [ተግባብተናል]" የሚል ማብራሪያ መሰጠቱን የምክር ቤት አባሉ አስረድተዋል።

አቶ ተስፋሁን፤ በአዲስ ለተዋቀሩት የምርጫ ክልሎች የተሰጡት መቀመጫዎች "ተነስተው ለሌሎች ወረዳዎች እንዲሸነሸን በተሰጠን አቅጣጫ መሠረት ሸንሽነናል። ይህንን አውቃችሁ፤ ያንን ተቀብላችሁ እንድታጸድቁ" መባሉንም አስታውሰዋል።

ይህ የክልሉ መንግሥት የውሳኔ ሀሳብ እና ውሳኔው የቀረበበት መንገድ ግን እንደ አቶ ለሜሳ ካሉ የምክር ቤት አባላት ተቃውሞ ተነስቶበታል። እንደ አቶ ለሜሳ ገለጻ በአንድ ምርጫ ክልል ውስጥ የሚገኝ ሕዝብ ምን ያህል ተወካዮች እንደሚያስፈልጉት መወሰን የነበረበት በክልሉ የሕዝብ እና ቤት ቆጠራ ከተካሄደ በኋላ በሚደረግ የክፍፍል ስሌት ነበር።

አቶ ለሜሳ፤ "[የወንበር ቁጥር] የጨመረበት መንገድ ፍትሐዊ አይደለም። የሕዝብ እና ቤት ቆጠራ ሳይካሄድ ይሄንን መጨመር ፍትሐዊነቱ የጎደለ ይሆናል። [...] ለተወሰነ ሕዝብ የሚያስፈልገው ውክልና ስንት ነው? የሚለውን የሚመልሰው የሕዝብ እና ቤት ቆጠራ ነው" በማለት በምክር ቤት ተቃውሟቸውን ማሰማታቸውን ተናግረዋል።

የቀድሞው ማሻሻያ ላይ አቤቱታ ካቀረቡት የምክር ቤት አባት አንዱ የሆኑት አቶ ተስፋሁንም ይህንን ሀሳብ ይስማሙበታል። መጋቢት ላይ ለሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባኤ በቀረበው አቤቱታ ላይም ይህ ጉዳይ ተጠቅሶ ነበር።

አቶ ተስፋሁን፤ የሕዝብ እና ቤት ቆጠራ ካለመካሄዱም በተጨማሪ አሁን የወንበር ክፍፍል የተካሄደበት መንገድም ቢሆን የክልሉ መንግሥት "ለበጀት እና ሌሎች ጉዳዮች እየተጠቀመ ያለበትን 1.2 ሚሊዮን የሕዝብ ብዛት ትንበያ" መሠረት ያደረገ አይደለም።

ይህ የውሳኔ ሀሳብ ለምክር ቤቱ የቀረበበት መንገድም ቢሆን ጥያቄ እንደተነሳበት አቶ ተስፋሁን ተናግረዋል። የአዋጅ ማሻሻያ ረቂቅ ባልቀረበበት ሁኔታ በበፊቱ አዋጅ ላይ የተደነገጉ ጉዳዮችን የሚቀይር የውሳኔ ሀሳብ መቅረቡን የተቃወሙ የምክር ቤት አባላት አጀንዳው ወደ ሌላ ቀን እንዲዘዋወር ጠይቀው እንደበረም አስታውሰዋል።

የክልሉ መንግሥት በበኩሉ፤ የመቀመጫዎች ብዛትን ያሳደገው አዋጅ "ከዚህ በፊት የጸደቀ ስለሆነ፤ አሁን አዲስ ምርጫ ክልል ማቋቋም ስለማይቻል ትርፍ [ወንበሮችን] ለወረዳዎች በሙሉ የተሸነሸነው ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ነው። የጸደቀ አዋጅ ስለሆነ አሁን በድጋሚ ማጽደቅ አያስፈልግም" የሚል ማብራሪያ መስጠቱን ገልጸዋል።

በመጨረሻው የውሳኔ ሀሳቡ በአብላጫ ድምጽ መጽደቁን ሦስቱ የምክር ቤት አባላት ተናግረዋል።

ቢቢሲ በጉዳዩ ላይ ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት እና የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ማብራሪያ ለማግኘት ያደረጋቸው ጥረቶች አልተሳኩም።