የኬንያ የፓርላማ አባል በዋና ከተማዋ ናይሮቢ በታጣቂዎች ተገደሉ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
አንድ የኬንያ ፓርላማ አባል የታቀደ ነው በተባለ ጥቃት በዋና ከተማዋ ናይሮቢ ጎዳና ላይ በሞተር ሳይክል በሚጓዙ ታጣቂዎች በተተኮሰባቸው ጥይት ተገደሉ።
ፖሊስ እንዳለው ጥቃት ፈጻሚዎቹ የምክር ቤት አባል የሆኑትን ቻርለስ ኦንጎንዶ ዌሬን መኪና ከፊት ሆነው ሲከታተሉ ቆይተው ከሞተር ሳይክሉ ላይ በመውረድ ከቅርብ ርቀት ተኩሰው ገድለዋቸዋል።
"የዚህ ወንጀል ባህሪይ ዒላማውን የለየ እና ቀድሞ የታቀደ ነው" በማለት የፖሊስ ቃል አቀባይ ሙቺሪ ኒያጋ ግድያውን በተመለከተ በሰጡት መግለጫ ላይ ተናግረዋል።
የኬንያ መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት የተቃዋሚ ፓርቲ አባል እና የምክር ቤት እንደራሴ የሆኑት ቻርለስ ከሁለት ወራት በፊት ለሕይወታቸው ስጋት እንዳላቸው ገልጸው ነበር ተብሏል።
ረቡዕ ምሽት ላይ በተፈጸመው ጥቃት የፓርላማ አባሉ ጠባቂ እና ሹፌር ጉዳት ስላልደረሰባቸው ግለሰቡን በፍጥነት ወደ ሆስፒታል ቢወስዷቸውም ሆስፒታል እንደደረሱ ሕይወታቸው ማለፉ ተገልጿል።

የፎቶው ባለመብት, Kenyan parliament
ጥቃቱ የተፈጸመው ንጎንግ በተባለ ጎዳና ላይ በሚገኝ ተሽከርካሪዎች በሚበዙበት አደባባይ እና በአብዛኛው ትራፊክ ፖሊሶች እንዲሁም የደኅንነት ካሜራዎች ባሉበት ስፍራ ነው።
ግድያው ከተፈጸመ በኋላ ወዲያውኑ ከፍተኛ የፖሊስ አዛዦች እና መርማሪዎች ከስፍራው የደረሱ ሲሆን፣ በክስተቱ ዙሪያ ምርመራ እየተካሄደ መሆኑን ፖሊስ አሳውቋል።
ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ በጥቃቱ ላይ ፖሊስ ጥልቅ ምርመራ እንዲያካሂድ እና "ግድያውን የፈጸሙትም ተጠያቂ እንዲሆኑ" ትዕዛዝ ሰጥተዋል።
ከጥቃቱ በኋላ ግድያው በተፈጸመበት ቦታ የተገኙ የምክር ቤት አባላት ድንጋጤ እና ቁጣቸውን በመግለጽ ፈጣን ምርመራ ተደርጎ ገዳዮች ለፍርድ እንዲቀርቡ ጠይቀዋል።
የኬንያ ፓርላማ አፈ ጉባኤ ሞሰስ ዌታንጉላ የተገደሉትን የፓርላማ አባል "የማይፈሩ እና የተከበሩ" የሕዝብ እንደራሴ እንደነበሩ በመግለጽ ግድያውን "አሳዛኝ" ብለውታል።
ሟች የምክር ቤት አባል ቻርለስ በአንጋፋው ፖለቲከኛ ራይላ ኦዲንጋ የሚመራው የኦሬንጅ ዴሞክራቲክ ሙቭመንት ፓርቲ አባል እና ከምዕራብ ኬንያ የተመረጡ የሕዝብ እንደራሴ ነበሩ።
የፓርቲው መሪ ኦዲንጋ በታጣቂዎች የተፈጸመውን ግድያ "ጭካኔ የተሞላበት" በማለት ባወጡት መግለጫ አውግዘውታል።
አክለውም በግድያው "የአገራችንን ጀግና አጥተናል!" ብለዋል ኦዲንጋ።












