ለኢትዮጵያውን ዶሮ አርደው 12 ብልቶችን በማውጣት የተካኑት ኬንያውያን
በዓላት ከአገር ውጭ በስደት ለሚገኙ ኢትዮጵያውያን በርካታ ትዝታዎችን የሚያጭሩ ናቸው። እንደ አገር ቤት ባይደምቅም የቻሉትን አድርገው በዓላትን በማክበር ቤተሰባቸውን እና አገራቸውን ያስታውሳሉ።
ከእነዚህም መካከል ለበዓላት የሚዘጋጀው ዶሮ ወጥ አብዛኞቹ የሚናፍቁት እና ባሉበት አገርም ሆነው ቢያገኙት የሚመኙት ነው። ነገር ግን ረጅም ጊዜ እና ከባድ ሥራ የሚጠይቀውን ዶሮ ወጥ ማዘጋጀቱ በስደት ላይ ለሚገኙ ኢትዮጵያውያን አመቺ አይደለም።
በጎረቤት አገር ኬንያ ናይሮቢ ውስጥ በርከት ያሉ ኢትዮጵያውያን ከመኖራቸው የተነሳ የዶሮ ነጋዴዎች ፍላጎታቸውን በመረዳት 'የሐበሻ' ዶሮዎችን እና እንቁላልን ያቀርባሉ። በተጨማሪም ኬንያውያኑ ዶሮዎቹን አርደው ኢትዮጵያውያኑ በሚፈልጉት ዓይነት 12 ብልት በማውጣት አገልግሎት ይሰጣሉ።
እኛም ትንሳዔ በዓልን ምክንያት አድርገውን ለኢትዮጵያውያኑ ዶሮ አርደው በሚፈልጉት መልኩ ከሚያርቡት መካከል አንዱን ተመልክተናል።









