ኮኬይን ከመጠቀም 25 የታሊባን ተዋጊዎችን እስከ መገድል የተተረከበት የልዑል ሃሪ መጽሐፍ

የፎቶው ባለመብት, ANDREW KELLY
ልዑል ሃሪ የግል ሕይወቱ ላይ በሚያተኩረው መጽሐፉ ኮኬይን ከመጠቀም እስከ 25 የታሊባን ተዋጊዎች መግደል እንዲሁም አባቱ ንጉሥ ቻርልስ እንጀራ እናታቸውን እንዳያገቡ መቃወማቸውን ያካተተ አወዛጋቢ ሁነቶችን አጋርቷል።
የእንግሊዝኛ ቅጂው ገና ይፋ ያልሆነው የዚህ መጸሐፍ ይዘት መነገር የጀመረው ትናንት ሐሙስ ታኅሣሥ 27/2015 ዓ.ም. ጀምሮ ነበር።
የእንግሊዝ መገናኛ ብዙኃን ሃሪ በዚህ መጽሐፉ ታላቅ ወንድሙ ልዑል ዊሊያም አካላዊ ጥቃት አድርሶብኛል ማለቱን መዘገባቸው አነጋጋሪ ጉዳይ ሆኖ ቆይቷል።
ዘ ጋርዲያን ሃሪ ‘ስፔር’ በተሰኘ መጽሐፉ ወንድሙ “አንገቴን ይዞ፤ የአንገት ጌጤን በመበጠስ መሬት ላይ ዘርሮኛል” ስለማለቱ ዘግቧል።
ከዚህ በተጨማሪም ሁለቱ ወንድማማቾች በሃሪ ባለቤት ሜጋን ዙሪያ ተጨቃጭቀው እንደነበረ በመጽሐፉ ላይ ተጠቅሷል ተብሏል።
በስፓኒሽ ቋንቋ የታተመው ቅጂ ከእንግሊዝኛው ቀድሞ ለገበያ የቀረበ ሲሆን፣ በመጽሐፉ የሰፈሩ ሌሎች አነጋጋሪ ጉዳዮች ይፋ ሆነዋል።
የቻርልስ አዲስ ትዳር
ልዑል ሃሪ እና ልዑል ዊሊያም ከንጉሥ ቻርልስ ሦስተኛ እና በመኪና አደጋ ሕይወቷ ካለፈው የዌልሷ ልዕል ዳያና ይወለዳሉ።
ከልዕልት ዳያና ሞት በኋላ ሁለቱ ልጆች አባታቸው ቻርልስ ካሚላን እንዳያገቡ መለመናቸውን ሃሪ በመጽሐፉ ላይ አስፍሯል።
ካሚላ በይፋ ንጉሥውያን ቤተሰቡን ከመቀላቀሏ በፊት እርሱ እና ሃሪ ከካሚላ ጋር ስብሰባ መቀመጣቸውን ገልጿል።
ዳያና እአአ 1997 ላይ ሃሪ ገና የ12 ዓመት ልጅ ሳለ ነበር ፓሪስ ፈረንሳይ ውስጥ በመኪና አደጋ ሕይወቷ ያለፈው። ሃሪ በመጽሐፉ የእናቱ ሞት ሐዘን በእጅጉ እንደጎዳው ገልጿል።
“ዊሊያም ዘረረኝ”
ሃሪ ‘ስፔር’ በተሰኘ መጽሐፉ አካቷቸዋል ከተባሉ ጉዳዮች እስካሁን ብዙዎችን ያነጋገረው በታላቅ ወንድሙ አካላዊ ጥቃት እንደተሰነዘረበት የገለጸበት ነው።
“የውሃ ብርጭቆ አስቀመጠ፤ በሌላ ስም ጠራኝ እና ወደ እኔ መጣ። በጣም በፍጥነት ነው የሆነው። አንገቴን ያዘኝ. . . መሬት ላይ ጣለኝ። የውሻ መመገቢያ ሳህን ላይ ወደቅኩ፤ ከጀርባዬ ሆኖ ተሰባበሮ ስብርባሪው ወገኝ። በወደቅኩበት ዞሮብኝ ባለሁበት ቆየው፤ ከዚያ ተነስቼ ቆምኩ እና እንዲወጣ ነገርኩት” ሲል ጽፏል።
ሃሪ በመጽሐፉ በወቅቱ በብስጭት ውስጥ የነበረው ታላቅ ወንድሙ መልሶ እንዲመታው ቢጠይቀውም ሃሪ ያን ከማድረግ መቆጠቡን ገልጿል።

የፎቶው ባለመብት, PA Media
ኮኬይን መጠቀም
ሃሪ ገና የ17 ዓመት ወጣት ሳለ ኮኬይን የተባለውን አደገኛ አደንዛዥ ዕጽ ሰው ከተሰጠው በኋላ በተለያዩ አጋጣሚዎች ዕጹን መጠቀሙን በመጽሐፉ አምኗል።
ሃሪ ኮኬይን መጠቀሙ ባያስደስተኝም፤ “የተለየው ሰው እንደሆንኩ እንዲሰማኝ አድርጎኛል” ብሏል።
“የተለመደውን ሥርዓት ለመቀየር የትኛውንም ነገር ለመሞከር ዝግጁ የሆንኩበት የ17 ዓመት ልጅ ነበርኩ” ብሏል።
ሃሪ በኤተን ኮሌጅ ተማሪ ሳለ በኮሌጁ መጸዳጃ ቤት ውስጥ ካናቢስ ማጨሱንም እንዲሁ በመጽሐፉ ገልጿል።
ሃሪ ታላቅ ወንድሙ ይማር የነበረበትን ኤተን ኮሌጅ መቀላቀሉ ደስተኛ እንዳላደረገው ጭምር ገልጿል። ሃሪ በየኮሌጅ ትምህርቱን ለመጀመር በሚሰናዳበት ወቅት “አላውቅምህ፤ አንተም አታውቀኝም” ሲል ዊሊያም እንደተናገረው ሃሪ ጽፏል።

የፎቶው ባለመብት, PA Media
የታሊባን ተዋጊዎችን ስለመግደል
ሃሪ በመጽሐፉ የብሪታኒያ ሠራዊት አባል ሆኖ በአፍጋኒስታን የሄሊኮፕተር አብራሪ ሳለ፣ ስድስት ዘመቻዎች ላይ መሳተፉን እና በእነዚህ ተልዕኮዎች ሲዋጓቸው የነበሩ 25 የታሊባን ወታደሮችን መግደሉን ተናግሯል።
ክስተቱ ኩራት እንዲሰማኝ ባያደርግም የሚያሳፍረኝ ግን አይደለም ብሏል። እነዚያ 25 መጥፎ ሰዎች ሰዎችን ከመግደላቸው በፊት መወገድ የነበሩባቸው ናቸው ብሎ የሚያስብብት አጋጣሚ እንደነበረ ጽፏል።
ስለ ሜጋን እና ሠርጋቸው
በሃሪ ‘ስፔር’ መጽሐፉ ላይ ከወንድሙ ጋር በትዳር አጋሩ ሜጋን ዙሪያ ተጨቃጭቀው እንደነበረ ገልጿል።
በዚህ መጽሐፍ ልዑል ዊሊያም ታናሽ ወንድሙ አፍሪካ አሜሪካዊቷ ሜጋንን የማግባቱ ዕቅዱ እንዳልተዋጠለት ሃሪ ጽፏል።
ዊሊያም ሜጋንን ‘አስቸጋሪ’፣ ‘ሥነ-ምግባር የጎደላት’ እና ‘አጸያፊ’ ብሎ ስለመግለጹ ተዘግቧል።
ሠርጋቸውን በተመለከተም ንጉሥውያን ቤተሰብ አባላት የጋብቻ ሥነ-ስርዓቱ የሚካሄድበትን ቦታ እና ቀን በተመለከተ ውሳኔ ለመስጠት ሲጓተቱ ነበር ብሏል።
ሃሪ ሠርጉ በቅዱስ ጵውሎስ ካቴድራል አልያም በዌስትሚንስተር አቤይ ማከናወን እንደሚችል ወንድሙን ሲያማክር ሁለቱ ስፍራዎች የቻርልስ እና የዲያና እንዲሁም የዊሊያም እና ካትሪን ሠርግ የተከናወነበት በመሆኑ በሁለቱ ቦታዎች ሠርጉን ማድረግ እንደማልችል ነገሮኛል ብሏል።
ዊሊያም የጥንዶቹ ሠርግ በአባታቸው መኖሪያ ቤት በሚገኝ አነስተኛ ቤተ-መቅደስ እንዲከናወን ሃሳብ መስጠቱን ሃሪ ገልጿል።
ዊሊያም እንዳለው ሳይሆን ሃሪ እና ሜጋን እአአ 2018 ላይ በዊንዘር በቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ-መቅደስ ጋብቻቸውን ፈጽመዋል።
ሃሪ በመጽሐፉ ስላነሳቸው ክሶች የልዑል ዊሊያም ይፋዊ መኖሪያ ቤት ኪንግስተን ቤተ-መንግሥትም ሆነ የንጉሥ ቻርልስ መኖሪያ ቤት ባኪንግሃም ፓላስ በጉዳዩ ላይ አስተያየት ከመሰጠት ተቆጥበዋል።












