ሲቲ ከቶተንሃም እና ኒውካስል ከዩናይትድ. . . የሳምንቱ ተጠባቂ ጨዋታዎች ግምት

ቶተንሃሞች ያለፉትን ሦስት የሊግ ጨዋታዎች ተሸንፈዋል። በርካታ ተጫዋቾችንም በጉዳት አጥተዋል። እሑድ ከማንቸስተር ሲቲ ጋር በሚያደርጉት ጨዋታ በማጥቃት ላይ የተመሰረተውን አጨዋወታቸውን ይቀይራሉ?
የቢቢሲው የእግር ኳስ ተንታኝ ክሪስ ሱተን “ማንቸስተር ሲቲን በማጥቃት ለመጫወት ስለሚሞክሩ በመልሶ ማጥቃት ተጋላጭ ይሆናሉ” ይላል።
እንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ 14ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ቅዳሜ እና እሑድ ይከናወናሉ።
ሱተን የእነዚህን ጨዋታዎች ግምት እንደሚከተለው አስቀምጧል።
ቅዳሜ: አርሴናል ከ ዎልቭስ
ዎልቭስ ባለፉት ጥቂት ጨዋታዎች ከሜዳ ላይ ብቃት ይልቅ በቫር ያልተገባ ውሳኔ ነጥቦችን አጥተዋል።
አርሴናሎች ባለፈው ሳምንት ባለቀ ሰዓት ባስቆጠሩት ጨዋታ ብሬንትፎርድን አሸንፈዋል። ይህም ጨዋታ ቀላል አይሆንም።
አርሴናልን እየጠቀመ ያለው የተከላካይ መስመሩ ጥንካሬ ሲሆን በዚህ ጨዋታም ጎል የሚቆጠርባቸው አይመስለኝም።
ግምት፡ 2 – 0
ብሬንትፎርድ ከ ሉተን
ሉተን እጅ አለመስጠትን ከማሳየታቸውም በላይ ባለፈው ሳምንት ክሪስታል ፓላስን በማሸነፋቸው ተደንቄያለሁ።
የሮብ ኤድዋርድስ ቡድን ብዙዎች ባልገመቱት መልኩ እየተጫወተ ይገኛል።
በዚህ ጨዋታ ብሬትፎርዶች ባለፈው ሳምንት ከደረሰባቸው ሽንፈት አገግመው ሦስት ነጥብ የሚያሳኩበት ይሆናል።
ግምት፡ 2 – 0
በርንሌይ ከ ሼፊልድ
ብርንሌይ በሜዳው ያደረጋቸውን ሰባት ጨዋታዎች በሙሉ ተሸንፏል። ሼፊልድ ደግሞ ከሜዳው ውጭ ባደረጋቸው ስድስት ጨዋታዎች አንድ ነጥብ ብቻ ነው ያሳካው።
ከሁለቱ ቡድኖች ለየትኛው ማድላት እንዳለብን አላውቅም።
ስለዚህ ጨዋታው አቻ ይጠናቀቃል እላለሁ።
ከተሸናነፉ ግን የተሸናፊው ቡድን አሰልጣኝ ጫና ይበዛበታል።
ግምት፡ 1 – 1
ኖቲንግሃም ፎረስት ከ ኤቨርተን
ይህ ለፎረስቶች ትልቅ ጨዋታ ነው።
አሰልጣኝ ስቲቭ ኩፐር ጫና ውስጥ መሆናቸው እየተዘገበ ነው።
ኤቨርተንም ከዚህ ጨዋታ ነጥብ ይፈልጋል። ባለፈው ሳምንት በማንቸስተር ዩናይትድ 3 ለ 0 ቢሸነፉም ከፈጠሩት ዕድል አንጻር ዕድለኛ አልነበሩም።
ይህ ጨዋታ አቻ ይጠናቀቃል የሚል ስሜት የነበረኝ ቢሆንም አሰልጣን ሾን ዳይሽ የማሸነፊያ መንገዱን የሚያገኙ ይመስለኛል።
ግምት፡ 0 – 1

ኒውካስል ከ ማንቸስተር ዩናይትድ
ማንቸስተር ዩናይትድ ረቡዕ ዕለት ከጋላታሳራይ ጋር ወደ ፊት ሲሄድ ጥሩ የነበረ ቢሆንም የኋላ መስመሩ ደግሞ ደካማ ሆኖ አምሽቷል።
ኒውካስሎች ከፒኤስጂ ጋር ነጥብ የተጋሩበት መንገድ የሚፈጥረው ቁጣ ለዚህ ጨዋታ መነሳሻነት ያውሉታል።
የኤዲ ሃው ቡድን ባለፈው ሳምንት ቼልሲን ያሸነፈ ሲሆን በዚህ ሳምንትም ማንቸስተርን እንደሚያሸነፉ እገምታለሁ።
ይህ ለኤሪክ ቴን ሃግ ከባድ ጨዋታ ሲሆን ጥሩ የነበረው ጉዟቸው የሚያከትምበትም ይሆናል።
ግምት፡ 3 – 1
እሑድ: በርንመዝ ከ አስቶን ቪላ
አስቶን ቪላ በጥሩ አቋም ላይ ሲገኝ በርንመዝም በጥሩ ግስጋሴ ላይ ነው።
በርንመዝ ካለፉት አራት ጨዋታዎች ሦስቱን በማሸነፉ ጨዋታውን ለመገመት አዳጋች ያደርገዋል።
ቪላ ባለፈው ሳምንት ስፐርስን በማሸነፍ ድንቅ ውጤት አስመዝግቧል።
በርንመዝ ላይ ለማስቆጠር አስቸጋሪ ቡድን በመሆኑ ቪላ ይፈተናል ብዬ አስባለሁ።
ግምት፡ 1 – 1

ቼልሲ ከ ብራይተን
ቼልሲ የሚዋዥቅ አቋም በማሳየት ላይ ነው።
ብራይተን ብዙ ጎሎችን ስለሚያስተናግድ ለመገመት አስቸጋሪ ያደርገዋል።
ቼልሲ ካለፈው ሳምንት የኒውካስል ሽንፈት በኋላ የሚያገግሙበት ጨዋታ ነው።
ይህንን ጨዋታ በጠባብ ውጤት ያሸንፋል።
ግምት፡ 3 – 2
ሊቨርፑል ከ ፉልሃም
ፉልሃም ሰኞ ዕለት ዎልቭስን በማሸነፍ ሦስት ነጥብ አሳክተዋል።
ከአንፊልድ ነጥብ ለማግኘት ዕድለኛም መሆን ያስፈልጋቸዋል።
ሊቨርፑል ባለፈው ሳምንት ኢትሃድ ላይ አቻ ቢለያይም በዚህ ሳምንት ሦስት ነጥብ ያስፈልገዋል።
ቀያዮቹ የግብ ዘቡን አሊሰንን እና አጥቂው ዲዮጎ ጆታን በጉዳት ቢያጡም ይህንን ጨዋታ ማሸነፍ ይጠበቅባቸዋል። ሞሐመድ ሳላህ አስቆጥሮ የየርገን ክሎፕ ቡድን በቀላሉ እንደሚያሸንፍ እጠብቃለሁ።
ግምት፡ 3 – 0
ዌስት ሃም ከ ክሪስታል ፓላስ
ክሪስታል ፓላስ መጥፎ ባይጫወትም ካለፉት አምስት ጨዋታዎች አራቱን ተሸንፏል።
ዌስት ሃም የጃሮድ ቦዌን ወደ ሙሉ አቋም መመለስን ይጠብቃሉ።
ዌስት ሃም ዩሮፓ ሊግ ላይ ሀሙስ መጫወቱ ፓላሶችን የሚጠቅም ቢሆንም ጨዋታው አቻ የሚጠናቀቅ ይመስለኛል።
ግምት፡ 1 – 1
ማንቸስተር ሲቲ ከ ቶተንሃም
ስፐርሶች ከቪላ ጋር በነበረው ጨዋታ ቤን ዴቪስን እና ኤመርሰን ሮያልን በተከላካይ መስመር አሰልፈዋል።
በዚህ ጨዋታ ማንም ይሰለፍ ማን ምርጥ አቋማቸው ላይ መገኘት ይኖርባቸዋል።
ክፍት እና ቶተንሃም ዕድሎችን የሚፈጥርበት ጨዋታ እንደሚሆን እጠብቃለሁ።
ሲቲዎችን ዕድሎችን መፍጠር ብቻ ሳይሆን ለመጠቀምም ወደ ኋላ አይሉም።
በጨዋታው በርካታ ጎሎች ሲቆጠሩ ፔፕ ጋርዲዮላ ቡድን አብዛኛውን ያስቆጥራል።
ግምት፡ 4 – 2












