በቡርኪና ፋሶ ታጣቂዎች መስጂድ እና ቤተ ክርስቲያን ላይ በፈጸሙት ጥቃት በርካቶችን ገደሉ

የተገለጠ ቁርዐን እና የሰው እጅ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ቡርኪና ፋሶ ውስጥ በአንድ መስጂድ እና ቤተክርስቲያን ላይ በተመሳሳይ ቀን በተፈጸመ ጥቃት በርካታ ሰዎች መገደላቸው የአገሪቱ ባለሥልጣናት አስታወቁ።

ናቲያቦአኒ በተባለችው ከተማ ውስጥ ለፀሎት መስጂድ ውስጥ በማለዳ የተሰበሰቡ ሰዎችን በመክበብ ታጣቂዎች በፈጸሙት ጥቃት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ሰዎች ገድለዋል።

አንድ የአካባቢው ነዋሪ ለፈረንሳይ ዜና ወኪል ኤኤፍፒ እንደተናገሩት “የጥቃቱ ሰለባዎች አብዛኞቹ ወንዶች ሲሆኑ ሁሉም ሙስሊሞች ናቸው” ብሏል።

ምዕራብ አፍሪካዊቷ አገር ቡርኪና ፋሶ ካላት ግዛት ውስጥ ከአንድ ሦስተኛ የሚልቀው በእስላማዊ አማጺያን ቁጥጥር ሥር የሚገኝ ነው።

ጥቃት ፈጻሚዎቹ እስላማዊ ተዋጊዎች መሆናቸው የተጠረጠረ ሲሆን፣ ኢላማ ያደረጉትም በዕለቱ በአካባቢው ሰፍረው የነበሩ ወታደሮችን እና አካባቢያቸውን የሚጠብቁ ሚሊሻዎች ነው።

የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ጥቃቱን በተመለከተ ባቀረቡት ሪፖርት ላይ ጥቃት ፈጻሚዎቹ በርካታ ቁጥር ያላቸው መትረየስ የታጠቁ እና በሞተር ሳይክል የመጡ መሆናቸውን አመልክተዋል።

በመስጂዱ ላይ በተፈጸመው ጥቃት የተገደሉት ሰዎች ትክክለኛ ቁጥር አስካሁን ባይታወቅም በደርዘኖች የሚሆኑ ሰዎች እንደተገደሉ ይታመናል።

ያልተረጋገጡ እና በማኅበራዊ መገናኛ መድረኮች ላይ በመስጂዱ ጥቃት የተገደሉትን ቁጥር በተመለከተ እየወጡ ያሉት አሃዞች የአገሪቱ ባለሥልጣናት ከሚሉት በእጅጉ ከፍተኛ ነው።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ጥቃቱ የተፈጸመባት ናቲያቦአኒ ከተማ በርካታ ታጣቂ ቡድኖች በሚንቀሳቀሱበት እና መረጋጋት በራቀው የቡርኪና ፋሶ ምሥራቃዊ ክፍል ውስጥ የምትገኝ ናት።

በተመሳሳይ እሁድ ቀን እዚያው በቡርኪና ፋሶ ሰሜን ምሥራቅ ግዛት ውስጥ በሚገኝ አንድ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ላይ በተፈጸመ ጥቃት ቢያንስ 15 ምዕመናን ተገድለዋል።

ኢሳካኔ በተባለው ስፍራ ለእሁድ ጸሎት ሥነ ሥርዓት በተሰባሰቡት የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን አባላት ላይ ጥቃቱን የፈጸሙት ተጠርጣሪ እስላማዊ ታጣቂዎች ናቸው ሲሉ አንድ የቤተ ክርስቲያኗ ባለሥልጣን ከሰዋል።

በመስጂድ እና በቤተክርስቲያን ላይ በተመሳሳይ ዕለት የተፈጸመው ጥቃት ተያያዥነት ይኑረው አይኑረው በይፋ የታወቀ ነገር የለም። ነገር ግን አንድ የቡርኪና ፋሶ የግል ጋዜጣ ጥቃቶቹ የተቀነባበሩ ሊሆኑ ይችላሉ ብሏል።

ቡርኪና ፋሶ ውስጥ በሃይማኖት ተቋማት እና መሪዎች ላይ የሚፈጸም ጥቃት እምብዛም ያልተለመደ አይደለም።

ከሰሜናዊቷ ጂቦ ከተማ ከአምስት ዓመት በፊት ተጠልፈው የተወሰዱ አንድ ቄስ አስካሁን የደረሱበት አልታወቀም። ከሦስት ዓመት በፊት ደግሞ ከዚያው ከተማ በታጣቂዎች የተጠለፉ አንድ ኢማም ከቀናት በኋላ ሞተው ተገኝተዋል።

የሰብአዊ እርዳታ ሠራተኞች በቡርኪና ፋሶ ያለውን ሁኔታ በዓለም ላይ ችላ ከተባሉ ቀውሶች መካከል አንዱ ነው በማለት ይገልጹታል።

በአገሪቱ ለዓመታት በዘለቀው አለመረጋጋት ምክንያት ከሁለት ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሰዎች ከቤታቸው ለመፈናቀል ተገደዋል። በተባበሩት መንግሥታት ግምት መሠረት አንድ አራተኛ የመሆኑ ከአምስት ዓመት በታች የሆናቸው የአገሪቱ ህጻናት በረሃብ ምክንያት ቀንጭረዋል።

የአገሪቱ ጦር ሠራዊት ከሁለት ዓመታት በፊት በመፈንቅለ መንግሥት ሥልጣን ሲጨብጥ አማጺያንን ለማስወገድ ቃል ቢገባም፣ ግጭቱ ሳያባራ ቀጥሏል።