የኦሮሚያ የፖሊስ አባሉ አንዲት ሴትን ‘ሸኔ’ ነሽ ብሎ በመድፈሩ 7 ዓመት ተፈረደበት

የፎቶው ባለመብት, Suro Barguda wereda Comm.
በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ጉጂ ዞን ውስጥ የፖሊስ አባል የሆነ ግለሰብ አንዲት ሴትን ‘ሸኔ’ ነሽ ብሎ በማስፈራራት በመድፈሩ እስር ተፈረደበት።
በዞኑ የሱሮ ባርጉዳ ወረዳ ፖሊስ አባል የሆነው ኮንስታብል ገነሜ ኮንሶ በመድፈር ወንጀል ጥፋተኛ ሆኖ በመገኘቱ የሰባት ዓመት እስር ተፈርዶበታል።
ስሟን ለመጠበቅ ሲባል ማንነቷን የማይገለጸው የግል ተበዳይ፤ ወንጀሉ የተፈጸመባት በተጠቀሰው ወረዳ ውስጥ ደምቢ ሶሮ ተብሎ በሚጠራ ቀበሌ ሐምሌ 04/2015 ዓ.ም. ከምሽቱ 3፡30 ላይ ከሌላ ሴት ጋር ከቤቷ በወጣችበት ወቅት መሆኑን ጉዳዩን የተመለከቱት ዳኛ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በክስ መዝገቡ ላይ እንደተገለጸው የግል ተበዳይዋ ከሌላ ሴት ጋር ሆና ከመኖሪያ ቤታቸው ወጥተው መጸዳጃ ቤት ጋር ሲደርሱ በስፍራው የነበረው ተከሳሽ የፖሊስ አባል ያስቆማቸዋል።
ዳኛ በዳኔ ደንቦቢ “በሚኖሩበት ቤት እና በመጸዳጃ ቦታው መካከል 10 ሜትር ገደማ የሚርቅ መንገድ አለ። ሴቶቹ መንገዱን አቋርጠው መጸዳጃ ቤቱ ጋር ሲደርሱ ተከሳሹ መጣባቸው” ብለዋል።
“‘በዚህ ለሊት ወደየት ነው የምትሄዱት? በምሽት መንቀሳቀስ ክልክል ስለሆነ የቅጣት 200 ብር አምጡ" በማለት የመድፈር ወንጀሉን ከመፈጸሙ በፊት ገንዘብ ለመቀበል ሙከራ አድርጎ እንደነበረ ዳኛ በዳኔ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ሁለቱ ሴቶች ገንዘብ እንደሌላቸው ሲመልሱለት ‘ኦነግ ሸኔ’ ናችሁ የሚል ሌላ ክስ ማቅረብ መጀመሩን ዳኛው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የፎቶው ባለመብት, Suro Barguda wereda Comm.
“ሸኔ” መንግሥት በሽብርተኛነት የፈረጀው እና በኦሮሚያ የተለያዩ አካባቢዎች የትጥቅ ትግል የሚያደርገው ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ብሎ የሚጠራ ቡድን ነው።
ታጣቂ ቡድኑ በአሁኑ ወቅት ጉጂ እና ቦረናን ጨምሮ በምዕራብ እና ሰሜን ሸዋ ዞኖች ውስጥ በስፋት የሚንቀሳቀስ ሲሆን፣ ከመንግሥት ኃይሎች ጋር ተደጋጋሚ ግጭት ውስጥ ይገባል።
“ለቅጣት ያለውን ገንዘብ እንደማያገኝ ሲረዳ ‘እናንተ ኦነግ ሸኔ ናችሁ። ኦነግ ሸኔ ያለበትን ቦታ ስለምታውቁ ከዚያ ነው የምትመጡት’ በማለት ተቆጣ። ተበዳዮቹም ሸኔ ናችሁ በመባላቸው ከፍተኛ ፍርሃት ውስጥ ገቡ” በማለት ዳኛ በዳኔ ጨምረው ተናግረዋል።
“የጦር መሳሪያ ደቅኖባቸው ‘እገድላችኋለሁ’ ብሎ አስፈራርቶ ወደ ጢሻ ይዟቸው ገባ። ወደ ሰዋራ ቦታ ከወሰዳቸው በኋላም አንደኛዋን ‘ቁጭ በይ ድምጽሽን እንዳታሰሚ’ በማለት ካስፈራራ በኋላ፣ ባለትዳር የሆነችውን ሌላኛዋን ሴት ደፈረ” በማለት የተፈጠረውን ሁኔታ ዳኛው ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ሚስቱ ወደ ውጪ ወጥታ የቆየችበት የተበዳይ ባለቤትም ሚስቱን ፍለጋ ሲወጣ፣ ወንጀሉ ከተፈጸመበት ቦታ መድረሱን ዳኛው ተናግረዋል።
ተከሳሽ ኮንስታብል ገነሜ በሱሮ ባርጉዳ ወረዳ ፍርድ ቤት በቀረበበት ወቅት ወንጀሉን አልፈጸምኩም ብሎ ቢከራከርም፣ ለቀረበበት ክስ የመከላከያ ማስረጃ ማቅረብ አለመቻሉን ዳኛው ተናግረዋል።
የግል ተበዳይን ጨምሮ የሦስት ሰዎች ምስክርነት ፍርድ ቤቱ መቀበሉን የገለጹት ዳኛው፣ ተከሳሽ ኮንስታብል ገነሜ በወንጀለኛ መቅጫ ሕግ አንቀጽ 620/1 መሠረት ጥፋተኛ መሆኑን ፍርድ ቤቱ ወስኗል።
አንድ ተከሳሽ በኃይል ወይም በመሳሪያ አስፈራርቶ የመድፈር ወንጀል ከፈጸመ ከ5 አስከ 15 ዓመት እስር ያስቀጣል ያሉት ዳኛው፤ “ወንጀሉ ሲፈጸም በተበዳይ ላይ የደረሰ ሌላ ተጨማሪ ጉዳት እንደሌለ”፣ እንዲሁም ኮንስታብል ገነሜ ከዚህ ቀደም ወንጀል ፈጽሞ እንደማያውቅ እና ቤተሰብ አስተዳዳሪ መሆኑን ታሳቢ በማድረግ የሰባት ዓመት እስር ተፈርዶበታል ብለዋል ዳኛው።
በምዕራብ ጉጂ ዞን ውስጥ በታጣቂዎች እና በመንግሥት ኃይሎች መካከል የሚደረገው ግጭት በአካባቢው የሰላም እና መረጋጋት እጦት ከመፍጠሩም በላይ፣ ጾታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች እንዲጨምሩ ምክንያት መሆኑን ዳኛው ጨምረው ተናግረዋል።












