አሜሪካ ረጅም ርቀት ተወንጫፊ ሚሳኤሎችን ለዩክሬን ልትሰጥ ነው

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ለዩክሬን የላቁ የሚባሉ ረጅም ርቀት ተወንጫፊ ሚሳኤሎችን ለመስጠት እንዳቀዱ ተነገረ።
እነዚህ ተወንጫፊ ሚሳኤሎች ዩክሬን በሩሲያ ላይ እያደረገች ባለው የመልሶ ማጥቃት ዘመቻ ለመርዳት ያለመ እንደሆነም ነው የአሜሪካ ሚዲያዎች የዘገቡት።
ዩክሬን እስከ 300 ኪሎሜትር መወንጨፍ የሚችሉ ‘አርሚ ታክቲካል ሚሳይል ሲስተም’ (ATACMS) ሚሳኤሎችንም እንደሚሰጣት ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸውን የአሜሪካ ባለስልጣናትን ዋቢ አድርገው ሚዲያዎች አስነብበዋል።
እነዚህ ሚሳኤሎች ዩክሬን ከጦር አውዱ ውጭ ያሉ የሩሲያ ኢላማዎችን ለመምታት ያስችላታል ተብሏል።
አርብ እለት በክሪሚያ፣ ሴባስቶፓል የሚገኘው የሩሲያ የባህር ኃይል ዋና መስሪያ ቤት በዩክሬን ሚሳኤል ጥቃት ደርሶበታል።
የዩክሬን ወታደራዊ ምንጭ ለቢቢሲ እንደተናገሩት በሴባስቶፓል ወደብ ላይ የተፈጸመው ጥቃት ‘ ስቶርም ሻዶው’ በተሰኙ ሚሳኤሎች ነው።
እነዚህ ረጅም ርቀት ተወንጫፊ ሚሳኤሎች ከዩናይትድ ኪንግደም እና ፈረንሳይ የተገኙ ናቸው።
ምዕራባውያን ለዩክሬን እያደረጉት ያለውን የጦር መሳሪያዎች ጠቀሜታም ያሳየ ነው ተብሏል።
ስቶርም ሻዶው የተሰኙት ሚሳኤሎች ከ240 ኪሎሜትር ርቀት በላይ የመወንጨፍ አቅም አላቸው።
ኤንቢሲ ኒውስ እና ዘ ዋል ስትሪት ጆርናል ስማቸው ያልተጠቀሱ የአሜሪካ ባልስጣናትን ጠቅሰው እንደዘገቡት ፕሬዚዳንት ባይደን ለዩክሬን አቻቸው ቮሎድሚር ዘለንስኪ ትንሽ ቁጥር ያላቸው ‘አርሚ ታክቲካል ሚሳይል ሲስተም’ (ATACMS) የተሰኙ ሚሳኤሎችን እንደሚሰጧቸው ነግረዋቸዋል።
ሁለቱ መሪዎች በዚህ ሳምንት ሐሙስ ዕለት በዋይት ሃውስ ተገናኝተው ነበር።
ተወንጫፊ ሚሳኤሎቹ በሚቀጥሉት ሳምንታት ውስጥ እንደሚላኩ ዋል ስትሪት ጆርናል አክሎ ገልጿል።
ዋሽንግተን ፖስት በበኩሉ ተወንጫፊ ሚሳኤሎቹ ክላስተር ቦምቦች የታጠቁ እንደሚሆኑም በሁለቱ መሪዎች መካከል የተደረጉ ውይይቶችን የሚያውቁ በርካታ ባለስልጣናትን ዋቢ አድርጎ አስነብቧል።
አሜሪካም ሆነ ዩክሬን የአሜሪካ ሚዲያዎችን ዘገባ በይፋ አላረጋገጡም።
ከፕሬዚዳንቶቹ ውይይት በኋላ አሜሪካ ለዩክሬን ወታደራዊ ዕርዳታ የሚውል 325 ሚሊዮን ዶላር እንደምትለግስ ታውቃለች።
የአሜሪካ አብራም ታንኮችም በሚቀጥለው ሳምንት ወደ ኪዬቭ እንደሚደርስ ቢናገሩም በ‘አርሚ ታክቲካል ሚሳይል ሲስተም’ ዙሪያ ሁለቱ ፕሬዚዳንቶች አልተናገሩም።












