በኑሮ ውድነት የተማረረው ኬንያዊ በአደባባይ እራሱን በእሳት አቃጠለ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በአገሪቱ የተከሰተውን የኑሮ ውድነት አልቻልኩትም ያለው ኬንያዊ እራሱን በአደባባይ በእሳት በማቃጠል ሕይወቱን ለማጥፋት ሞከረ።
በምሥራቃዊቷ የባሕር ዳርቻ ከተማ ሞምባሳ ውስጥ ነዋሪ የሆነው ኬንያዊ፣ በከፍተኛ ሁኔታ የጨመረውን የኑሮ ውድነት በመቃወም እራሱ ላይ እሳት የለኮሰው ሐሙስ ዕለት ከሰዓት በኋላ ነው።
ግለሰቡ እራሱን ለማቃጠል የሞከረው፣ በመዝናኛዋ ከተማ ሞምባሳ ውስጥ መሃል መንገድ ላይ በሚገኝ ከፍተኛ እንቅስቃሴ በሚካሄድበት አደባባይ ባለ ሐውልት ላይ ወጥቶ ነው።
በኬንያውያን ማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ በስፋት በተሰራጨው ቪዲዮ ላይ፣ ግለሰቡ የኬንያን ሰንደቅ ዓላማ ይዞ በከፍተኛ ድምጽ ተቃውሞውን ሲያሰማ ከቆየ በኋላ መላው ሰውነቱ በእሳት ሲያይዝ ይታያል።
ነገር ግን በዙሪያው ሆነው ሲመለከቱት በነበሩ ሰዎች አማካይነት በፍጥነት እሳቱ እንዲጠፋ ተደርጎ ሕይወቱ ሊተርፍ ችሏል።
በኑሮ ውድነት እና በአገሪቱ ፖለቲካ የተማረረው ኬንያዊ እራሱን በእሳት በማቃጠል ለማጥፋት ያደረገው ሙከራ በዙሪያው በነበሩ ሰዎች ጥረት ሳይሳካ ከቀረ በኋላ፣ ወደ ሆስፒታል ተወስዶ ሕክምና እየተደረገለት ይገኛል።
ግለሰቡ በዙሪያው ለነበሩ የዐይን እማኞች እንደተናገረው እራሱን ለማጥፋት ምክንያት የሆነው በከፍተኛ ሁኔታ የጨመረውን የኑሮ ውድነት እና ባለፈው ዓመት ተካሂዶ “ተሰርቋል” የተባለውን ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ በመቃወም ነው።
በምርጫው ተቃዋሚው ራይላ ኦዲንጋ በጠባብ የድምጽ ልዩነት በዊሊያም ሩቶ የተሸነፉ ሲሆን፣ ተቃዋሚው ምርጫው የድምጽ ማጭበርበር ተፈጽሞበታል በማለት ቢከሱም የአገሪቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ውጤቱን ተቀብሎ አጽድቆታል።
በኬንያ ያለው የኑሮ ውድነት በፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ አስተዳደር ላይ ከፍተኛ ጥያቄን እያስነሳ ሲሆን፣ በቅርቡ መንግሥታቸው የጣላቸው የተለያዩ ዓይነት ታክሶች የኑሮ ውድነቱን ያባብሰዋል በሚል ተቃውሞ ሲቀርብባቸው ቆይቷል።
የዛሬ ዓመት በተካሄደው ምርጫ የተሸነፉት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ራይላ ኦዲንጋ እና ደጋፊዎቻቸው አሁን ድረስ የምርጫውን ውጤት ያልተቀበሉት ሲሆን ባገኙት አጋጣሚዎች ሁሉ ይህንን እያንጸባረቁ ይገኛሉ።
ባለፉት ሁለት ወራትም የኑሮ ውድነትን፣ መንግሥት የጣለውን ታክስ እንዲሁም ከምርጫው ውጤት ጋር በተያያዘ ያላቸውን ተቃውሞ በማንሳት ደጋፊዎቻቸው ተከታታይ የአደባባይ ተቃውሞ እንዲያደርጉ ጠርተው በአገሪቱ ቀውስ ተፈጥሮ ነበር።
ዋና ከተማዋን ናይሮቢን ጨምሮ በአገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች ውስጥ በተካሄዱት የአደባባይ ተቃውሞዎች የፀጥታ ኃይሎች በወሰዱት እርምጃ በርካታ ሰዎች ተገድለዋል፣ ከፍተኛ የንብረት ውድመት ተከስቷል።
በአሁኑ ወቅት መንግሥት እና ተቃዋሚዎች በሚነሱ ጥያቄዎች ዙሪያ ድርድር ለማድረግ ተስማምተው ውይይት ጀምረዋል።












