የኬንያ ፓርላማ አዲሱን የታክስ ሕግ በተቃወሙ በእሳት ሲያያዝ ፖሊስ ተቃዋሚዎችን ገደለ

የኬንያ ፓርላማ ያጸደቀውን አዲስ የታክስ ሕግ ለመቃወም አደባባይ የወጡ ኬንያውያን የአገሪቱን ፓርላማ በእሳት ሲያቃጥሉ፤ ከመካከላቸውም ቢያንስ አምስቱ በፀጥታ ኃይሎች መገደላቸው ተዘገበ።
ወጣቶቹ የተቃውሞ ድምጻቸውን ለማሰማት ወደ ፓርላማው በመሄድ የምክር ቤቱን አጥር ጥሰው በመግባት ወደ መሰብሰቢያ አዳራሹ ገብተው ታይተዋል።
ፖሊስ በከፍተኛ ቁጥር የወጡ ወጣቶችን ለመበተን ጥይት እና አስቀሽ ጭስ ተኩሷል። በርካታ ሰዎች በጥይት መመታታቸው የተገለጸ ሲሆን፣ ከ10 ያላነሱ ሰዎች ሕይወታቸው ማለፉን ሮይተርስ የዜና ወኪል የአደጋ ጊዜ ሠራተኞችን ጠቅሶ ዘግቧል።
ፖሊስ ፓርላማውን ጨምሮ ቁልፍ የመሆኑ የመንግሥት ተቋማትን ለመጠበቅ እና ተቃዋሚ ሰልፈኞችን ለመበተን እያደረገ ባለው ጥረት የሟቾች ቁጥር ሊጨመር እንደሚችል ይጠበቃል።
አዲሱ የቀረጥ ሕግ ኑሮ ያስወድድብናል ሲሉ የቆዩት ኬንያውያን ወጣቶች በኢንተርኔት አማካይነት ተሰባስበው ከአገሪቱ ፓርላማ ፊት ለፊት የተቃውሞ ድምጻቸውን ለማሰማት በከፍተኛ ቁጥር ወጥተዋል።
ይህን ተከትሎ መንግሥት የኢንተርኔት ግንኙነትን ዘገምተኛ እንዲሆን ማድረጉ እየተነገረ ነው። በመላው ዓለም የኢንተርኔት ግንኙነትን የሚቆጣጠረው ኔትብሎክስ ባለፉት ሰዓታት በኬንያ የኢንተርኔት ግንኙነት መቆራረጥ እንዳጋጠመ ገልጿል።
ተቃዋሚዎች ኤክስ (ትዊተር) መረጃ ለመለዋወጥ የሚጠቀሙ ሲሆን ከሰዓት በኋላ የትዊተር አገልግሎት እየተቆራረጠ ይገኛል።
የተባባሰውን ተቃውሞ ተከትሎ የግል የቴሌቪዥን ጣቢያ የሆነው ኬቲኤን በሚያቀርበው ዘገባ ምክንያት ከመንግሥት የመዝጋት ማስፈራሪያ እንደደረሰበት አስታውቋል።
ለ24 ሰዓታት የሚሰራጨው የቴሌቪዥን ጣቢያ ግን፣ ምንም እንኳን የመዘጋት ዛቻ ቢገጥመውም ዘገባዎችን የማቅረብ የጋዜጠኝነት ኃላፊነቱን እንደሚወጣ አቋሙን ገልጿል።
ቴሌቪዥን ጣቢያው ዛሬ የተቃውሞ ዘገባው በዩቲዩብ ብቻ ከ200 ሺህ በላይ ተመልካቾች ነበሩት።
ከመዲናዋ ናይሮቢ በተጨማሪ የተለያዩ ግዛቶች አስተዳዳሪ መሥሪያ ቤቶች ላይ ጥቃት ተፈጽሟል። የናኩሩ ግዛት አስተዳዳሪ መሥሪያ ቤት በተቃዋሚዎች መወረሩን ሲትዝን የተባለው የቴሌቪዥን ጣቢያ ዘግቧል።
ከጥቂት ሰዓታት በፊት የአገሪቱ ምክር ቤት አባላት ከፍተኛ ተቃውሞ ገጥሞት የነበረውን እና በተለያዩ ምርት እና አገልግሎቶች ላይ ተጨማሪ ታክስ የሚጥለውን አወዛጋቢ ረቂቅ ሕግ አጽደቀዋል።
ፖሊስ ቁጥጥር አቅም በላይ የሆኑ አብዛኛዎቹ ወጣቶች የሆኑ ተቃዋሚዎች የፓርላማውን በር ጥሰው ሲገቡ በመቶዎች የሚቆጠሩ የፓርላማ አባላት ከምክር ቤቱ ምድር ቤት ለመደበቅ ሲሯሯጡ የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን አሳይተዋል።
ከዚህ በተጨማሪ ተቃዋሚዎች አንደኛውን የፓርላማውን ክፍል በእሳት አያይዘዋል።
በተለያዩ ማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ እየተሠራጩ ያሉ ምሥሎች እና ቪዲዮዎች ተቃዋሚ ወጣቶቹ በፓርላማው የመሰብሰቢያ አዳራሽ ውስጥ ሆነው ተቃውሞ ሲያሰሙ ይታያሉ።
የኬንያው ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶም ሆኑ ከፍተኛ ባለሥልጣናት አስካሁን ባለው ክስተት ላይ እስካሁን ያሉት ነገር የሌለ ሲሆን፣ የአገሪቱ ጦር ሠራዊት ቀውሱን ለመቆጣጠር ትዕዛዝ እስኪሰጠው ድረስ በተጠንቀቅ እንዲቆም መታዘዙ እየተነገረ ነው።
በዛሬው ሰልፍ ላይ ከተሳተፉ ወጣቶች መካከል ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ተቃዋሚዎች እንደተጎዱ የተገለጸ ሲሆን፣ በአገሪቱ ትልቁ ወደ ሆነው ኬንያታ ሆስፒታል ወደ 45 ገደማ የሚሆኑ ሰልፈኞች ቆስለው ተወስደዋል።
ሆስፒታሉ በኤክስ ገጹ ላይ የተለያየ የጉዳት የደረሰባቸው ተቃዋሚዎች ሕክምና እየተደረገላቸው መሆኑን አመልክቷል።
ሆስፒታሉ እስካሁን ሕይወታቸው ያለፉ ተቃዋሚዎች እንደሌሉ፣ ገልጾ ከተጎጂዎቹ መካከል ሰባቱ ሴቶች ናቸው ብሏል።
በኑሮ ውድነት የተማረሩት ኬንያውያን መንግሥት ተጨማሪ ታክሶችን ሊጥል መሆኑን እና ረቂቅ ሕግ ማዘጋጀቱን ተከትሎ ላለፉት ሳምንታት ተቃውሟቸውን ሲያሰሙ ቆይተዋል።
መንግሥት በበኩለ ታክስ በመጨመር ተጨማሪ ብድር ከሌሎች ምንጮች መውሰድ ሳያስፈልገው ለአስፈላጊ የመንግሥት ወጪዎች እና አገልግሎቶች ገቢ ለማግኘት ዓላማ አድርጎ መሆኑን ገልጿል።
መንግሥት የቀረጥ ጭማሪ ሊያደርግባቸው ካሰባቸው ምርቶች እና አገልግሎቶች መካከል በዳቦ ላይ 16 በመቶ እና ምግብ ዘይት ደግሞ 25 በመቶ ተካቶ ነበር።
ነገር ግን በተካሄደው ተቃውሞ ምክንያት እነዚህ እና ሌሎች የተወሰኑትን ማስቀረቱን ባለፈው ሳምንት ቢያሳውቅም ተቃውሞው ቀጥሏል። በዛሬው ዕለትም በሕዝቡ ዘንድ ድጋፍ ያላገኘው ረቂቅ በምክር ቤቱ ከጸደቀ በኋላ ነው ተቃዋሚዎች ወደ ፓርላማው ጥሰው የገቡት።
የአካባቢ ጥበቃን ያግዛል በሚል የተጣለው ታክስም የሴቶች ንጽህና መጠበቂያ እና የሕጻናት የሽንት ጨርቅን ጨምሮ በርካታ ከውጭ ሚገቡ ምርቶች ላይ ታክስ ጥሏል።
ባለፈው እሁድ ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ተቃውሞውን እንደሚረዱ እና በወጣቶች ዘንድ ያለውን ስጋት ለመቅረፍ ውይይት እንደሚያደርጉ ቃል ገብተው ነበር።












