የሳዑዲ አረቢያው አል-ሂላል ምባፔን ለመግዛት 259 ሚሊዮን ፓውንድ አቅርቧል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የሳዑዲ አረቢያው ክለብ አል-ሂላል ፈረንሳዊው ኪሊያን ምባፔን ክብረ ወሰን በሆነ 259 ሚሊዮን ፓውንድ ከፒኤስጂ ለመግዛት ጥያቄ አስገባ።
የ24 ዓመቱ የፈረንሳይ አምበል ከፒኤስጂ ጋር ያለውን ውል ሊቋጭ አንድ ዓመት ይቀረዋል።
ነገር ግን ከክለቡ ጋር ያለውን ውል ላለማራዘም የወሰነ ሲሆን ክለቡ ደግሞ ተጫዋቹን በሚቀጥለው ዓመት በነፃ ከሚያጣው አሁን ቢሸጠው ይመርጣል።
ብራዚላዊው ኔይማር በፈረንጆቹ 2017 ከባርሴሎን በ200 ሚሊዮን ፓውንድ የመጣበት ዋጋ ክብረ-ወሰን ነው።
ምባፔ በ2017 ከሞናኮ ወደ ፒኤስጂ የመጣው 166 ሚሊዮን ፓውንድ ወጥቶበት ነው።
ቼልሲ፣ ማንቸስተር ዩናይትድ፣ ቶተንሃም፣ ኢንተር ሚላን እና ባርሴሎና ተጫዋቹን ለመግዛት ፍላጎት እንዳላቸው ተገልጧል።
ምባፔ፤ በሚቀጥለው ዓመት ውሉ ሲጠናቀቅ በነፃ ወደ ሪያል ማድሪድ ማቅናት እንደሚሻ ይነገራል።
ፒኤስጂ ምናልባት ምባፔ በውሰት ወደ ሌላ ክለብ አቅንቶ ውሉ እስኪጠናቀቅ ድረስ ቢቆይ ቅር እንደማይላቸው ጋዜጦች ዘግበዋል።
ይህ ማለት ምባፔ ከ12 ወራት በኋላ በነፃ ሪያል ማድሪድን ቢቀላቀልም እስከዚያው ድረስ በውሰት ለፒኤስጂ ገንዘብ ያስገኛል።
የፒኤስጂ ሊቀ-መንበር አል-ኼላይፊ በምባፔ ጉዳይ ጠንከር ያለ እርምጃ ሊወስዱ እንደሚችሉ ይፋ አድርገዋል።
ምባፔ፤ የክለቡን ውሳኔ የማያከብር ከሆነ ለአንድ ዓመት ያክል ለቡድኑ እንደማይመረጥ ሊቀመንበሩ ጠቆም አድርገዋል።
ይህ የሚሆን ከሆነ ደግሞ ምባፔ ለአውሮፓ ዋንጫ 2024 የመመረጥ ዕድሉ ጠባብ ይሆናል ማለት ነው።
የሳዑዲ አረቢያ ሕዝብ ኢንቨስትመንት ፈንድ ንብረት የሆነው አል-ሂላል ሩበን ኔቬስን ከዎልቭስ፤ ካሊዱ ኩሊባሊን ደግሞ ከቼልሲ አስፈርሟል።
ግንቦት 2022 ነው ምባፔ ከፒኤስጂ ጋር ለሁለት ተጨማሪ ዓመት ለመቆየት፤ ከተቻለም ለማራዘም የሚያስችለውንና ብዙ ገንዘብ የሚያስገኝለትን ውል የፈረመው።
ምባፔ ሃገሩን ፈረንሳይን ወክሎ በዓለም ዋንጫው ፍፃሜ 3 ጎሎችን ቢያስቆጥርም በፍፁም ቅጣት ምት አርጀንቲና ማሸነፏ አይዘነጋም።
መጋቢት 2023 ኡጎ ሎሪስ ከብሔራዊ ቡድን ራሱን ማግለሉን ተከትሎ ምባፔ የፈረንሳይ አምበል ሆኖ ተመረጠ።
ወርሃ ሚያዚያ ከፒኤስጂ ጋር አምስተኛ በጠቅላላው ስድስተኛ የሊግ 1 ዋንጫ ያነሳው ምባፔ ከክለቡ ጋር መቆየት ቢሻም ውሉን እንደማያራዝም በትዊተር ገፁ ገለጠ።
በያዝነው ወር መባቻ የፒኤስጂው ሊቀመንበር ምባፔ ከክለቡ ጋር መቆየት ከሻተ ውሉን ማራዘም እንዳለበት ቢነግሩትም እሱ ግን ክለቡ “ከፋፋይ ነው” ሲል ለፈረንሳይ ጋዜጣ አስተያየት ሰጠ።
ፒኤስጂ ለክረምት ወራት ልምምድ ወደ ጃፓን እና ደቡብ ኮሪያ ሲያቀና ምባፔን ጥሎት በረረ።
ይህን ተከትሎ የፈረንሳይ ተጫዋቾች ማሕበር ክለቡ ምባፔን ጥሎት በመሄዱ ክስ ሊመሠርት እንደሚችል ይፋ አደረገ።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ነው የሳዑዲ አረቢያው አል-ሂላል ምባፔን ታይቶ በማይታወቅ 259 ሚሊዮን ፓውንድ ለመግዛት ጥያቄ ያቀረበው።












