የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝን የዋስትና መብት ውድቅ አደረገ

የፎቶው ባለመብት, TARIKU DESALEGN/FB
የጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ የዋሰትና መብት ውድቅ ሆኖ በእስር ላይ እንዳለ ክሱን እንዲከታተል የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ወሰነ።
የጋዜጠኛው ጠበቃ ሄኖክ አክሊሉ ለቢቢሲ እንደተናሩት፣ በዛሬው ችሎት በጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የዐቃቤ ሕግ አቤቱታን ተከትሎ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ለተመስገ ደሳለኝ የሰጠውን የዋስትና መብት አንስቶታል።
የፍትሕ መጽሔት ማኔጂንግ ኤዲተር የሆነው ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ባለፈው ወር ሰኔ 27/ 2014 ዓ.ም. በ100 ሺህ ብር ዋስትና ከእስር እንዲለቀቅ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ወስኖ ነበር።
ይሁን እንጂ ዐቃቤ ሕግ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ በዋስትና ሊፈታ አይገባም በሚል አቤቱታ ካቀረበ በኋላ የፈዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሰጠው የዋስትና መብት ታግዶ ቆይቷል።
ጠቅላይ ፍርድ ቤት መከራከሪያዎችን ካደመጠ በኋላ ዛሬ ሐሙስ ሐምሌ 21/2014 ዓ.ም. በዋለው ችሎት ጋዜጠኛው የቀረበበትን ክስ በማረሚያ ቤት ሆኖ እንዲከታተል መወሰኑን ጠበቃ ሄኖክ አክሊሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
“ዛሬ በጠቅላይ ፍርድ ቤት የነበረው ክርክር ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ በዋስትና ሊወጣ ይገባል ወይስ በእስር ላይ ሆኖ ጉዳዩን ሊከታተል ይገባል የሚል ነበር” ብለዋል ጠበቃው።
ከተሰየሙት ሦስት ዳኞች መካከል ሁለቱ ጋዜጠኛ ተመስገን በእስር ሊቆይ ይገባል በማለት ከፍተኛው ፍርድ ቤት የሰጠውን የዋስትና መብት በአብላጫ ድምጽ መሻራቸውን ጠበቃው አስረድተዋል።
ሁለቱ ዳኞች፤ ጋዜጠኛ ተመስገን የተከሰሰበት ጉዳይ በዕድሜ ልክ እስራት ሊያስቀጣ የሚችል መሆኑን በማንሳት፣ የቀረቡበት ተደራራቢ ክሶች መሆናቸው እና ጋዜጠኛው የዋስትና መብቱ ቢጠበቅለት በጽሑፍ ሥራው ሊቀጥል ይችላል የሚል ምክንያቶችን አቅርበዋል ብለዋል።
የጋዜጠኛው የዋስትና መብት ሊጠበቅ ይገባል ብለው የነበሩት ዳኛ ግን፤ ዋስትና ሰብዓዊ መብት መሆኑን በማስታወስ ተከሳሹ ነጻ ሆኖ የመገመት መብቱ መጠበቅ አለበት፣ ስለዚህ ቢወጣ የዋስትና መብት ግዴታውን አይፈጽምም የሚል እምነት እንደሌላቸው ተናግረዋል ሲሉ ጠበቃ ሄኖክ አስረድተዋል።
የጋዜጠኛ ተመስገን የዋስትና መብት በጠቅላይ ፍርድ ቤቱ መሰረዙን ተከትሎ በቀጣይ ለሰበር ሰሚ ችሎት አቤቱታቸውን እንደሚያቀርቡ ጠበቃ ሄኖክ አክሊሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
“...አርብ ወይም ሰኞ የሰበር ጥያቅዬን አቀርባለሁ። ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ መደበኛ ክርክሩ ሐምሌ 26/2014 ይቀጥላል” ብለዋል።
ጋዜጠኛ ተመስገን የቀረቡበት ክሶች
ዐቃቤ ሕግ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ወታደራዊ ምስጢሮችን ለሕዝብ ይፋ በማድረግ፣ ሐሰተኛ የሆኑ ወታደራዊ መረጃዎችን በማውጣት፣ ለአመጽ ሕዝብን ማነሳሳት የሚሉ ክሶችን አቅርቦበታል።
በሦስቱም ክሶች ላይ ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ በሚሰራበት ሚዲያ ላይ በመጻፍ እነዚህን የወንጀል ተግባሮች ፈፅሟል የሚልም ወደ ሰባት የሚሆኑ የፍትሕ መፅሔት ዕትሞች በማስረጃነት መቅረባቸውን ጠበቃው ለቢቢሲ ገልጸው ነበር።
ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ግንቦት 18/2014 ዓ.ም. ከሥራ ቦታው በፀጥታ ኃይሎች ተይዞ ወደ አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ተወስዶ በእስር ላይ ይገኛል።
ተመስገን በጋዜጣና በመፅሔት ባለቤትነትና ዋና አዘጋጅነት በቆየባቸው ጊዜያት መንግሥትን በሚተቹ ጽሁፎቹ ይታወቃል።
በተደጋጋሚ ጊዜያትም የህትመት ሥራዎቹ እንዲቋረጡ ከመደረጋቸው በተጨማሪ፣ ለበርካታ ጊዜያት ለእስር መዳረጉ ይታወሳል።
ተመስገን ደሳለኝ ከአራት ዓመት በፊት ለረጅም ጊዜ በአስር ላይ ቆይቶ ከተፈታ በኋላ፣ ተቋርጣ የነበረችውን ፍትሕ መጽሔትን መልሶ በመጀመር በየሳምንቱ ለንባብ እየበቃች ትገኛለች።












