የአሜሪካ ገበሬዎች በእርሻቸው ላይ የሚረጩት የሰው ሽንት ለምርታቸው የሚሰጠው ጥቅም

የፎቶው ባለመብት, Rich Earth Institute
በጥንታዊቷ ሮም እና ቻይና ሽንት እንደ ማዳበሪያ ያገለግል ነበር።
አሁንም በአሜሪካ ቬርሞንት የሚገኙ ገበሬዎች ምርታቸውን ለማሳደግ እና ሰብሎቻቸውን በዘላቂነት ለማልማት ይህንን የሰብል ማዳበርያ ዳግም መጠቀም ጀምረዋል።
ቤቲ ዊሊያምስ ወደ ንጽሕና ቤት ስትሄድ ሽንቷ እንደማይባክን ማወቅ ትፈልጋለች።
ላለፉት 12 ዓመታት እርሷ እና በአሜሪካ ቬርሞንት ውስጥ የሚኖሩ ጎረቤቶቿ ሽንታቸውን በትጋት ሰብስበው ገበሬዎች ለሰብላቸው ማዳበሪያነት እንዲገለገሉበት ሰጥተዋል።
"በውስጣቸው የተለያዩ ንጥረ ነገሮችን የያዙ ሰብሎችን እንመገባለን። እነዚህ ውስጣችን የሚብላሉ ብዙ ንጥረ ነገሮች እንደገና ጥቅም ላይ ውለው ለእኛ እና ለእንስሶቻችን ምግብ ማዳበሪያነት እንዲውሉ ማድረግ ይችላል። ስለዚህ ይህ ለእኔ ተገቢ እርምጃ ነው" ትላለች ዊልያምስ።
ዊልያምስ የሽንት ንጥረ ነገርን መልሶ ጥቅም ላይ ማዋል ላይ የሚሠራ ድርጅት ውስጥ ትሳተፋለች።
እሷ እና 250 ጎረቤቶቿ ለፕሮግራሙ በየዓመቱ ተመልሶ ጥቅም ላይ እንዲውል በሚል 45 ሺህ 400 ሊትር ሽንት ይለግሳሉ።
የአካባቢው ነዋሪዎች የለገሱት ሽንት በመኪና ተሰብስቦ በ80 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ፓስቸራይዝድ ወደሚሆንበት (ወደሚጣራበት) ስፍራ ይጓጓዛል።
ከዚያም በጥንቃቄ ፓስቸራይዝድ ታንከር ውስጥ ከተቀመጠ በኋላ፣ ቡቃያው ተገቢው የዕድገት ደረጃ ላይ ሲደርስ በአካባቢው ማሳዎች ላይ ይረጫል።
ተመራማሪዎች የሽንት ማዳበሪያ እንደ ጎመን እና ቆስጣ ባሉ ሰብሎች ላይ፣ ዝቅተኛ ለምነት ባለው አፈር ውስጥ እንኳን ቢሆን ማዳበሪያ ከሌለው ምርት ጋር ሲነጻጸር ምርትን እንደሚያሻሽል ይናገራሉ።
ሽንት ለማዳበሪያነት የሚያገለግለው በውስጡ በያዛቸው የናይትሮጅን እና የፎስፈረስ ንጥረ ነገር የተነሳ ነው።
በብዙ የእርሻ ማሳዎች ጥቅም ላይ የሚውሉት ሰው ሠራሽ ማዳበሪያዎች ውስጥ የሚጨመሩት እነዚሁ ተመሳሳይ ንጥረ ነገሮች ናቸው።

የፎቶው ባለመብት, Rich Earth Institute
ነገር ግን እነዚህ ሰው ሠራሽ ማዳበሪያዎች የአካባቢ ደኅንነት ላይ አሉታዊ ጉዳት ያስከትላሉ።
ናይትሮጅን የሚመረተው ከነዳጅ ሲሆን፣ ፎስፈረስ ማዕድንን በማውጣት ሂደት ደግሞ ጎጂ የሆኑ መርዛማ ኬሚካሎች ይፈጥራሉ።
ከዚህ ሁሉ በተቃራኒ ደግሞ ሽንት በነጻ ይገኛል። ዊልያምስ እንደምትለው "ሁሉም ሰው ይሸናል። ያልተጠቀምንበት ሀብት ነው።"
በሚቺጋን ዩኒቨርሲቲ የሲቪል እና የአካባቢ ምኅንድስና ፕሮፌሰር የሆኑት ናንሲ ላቭ ባለፉት አስርት ዓመታት ውስጥ ከቡድኑ ጋር በሠሩበት ወቅት ከመደበኛ ሰው ሠራሽ ማዳበሪያ ይልቅ ሽንትን መጠቀም የበካይ ጋዝ ልቀትን እንደሚቀንስ እና ግማሽ ያህል የውሃ መጠን ብቻ እንደሚፈልግ ደርሰውበታል።
የሽንት ንጥረ ነገሮችን በተመለከተ ሲናገሩም፣ ሽንት የተለመደመ አድራሻው ወራጅ ውሃዎች፣ ወንዞች ናቸው ይላሉ።
በሽንት ውስጥ ያለው ናይትሮጅን እና ፎስፈረስ ደግሞ ከወራጅ ውሃ ውስጥ ሙሉ በሙሉ አይወገድም።
እነዚህ ንጥረ ነገሮች ወደ ወንዞች እና ሐይቆች ሲገቡ አልጌዎች ጥቅም ላይ ያውሏቸዋል።
ውጤቱም የውሃ መስመሮችን የሚዘጋው የአልጌ አበባዎች ሊሆን ይችላል።
የሥነ-ምኅዳሩን ሚዛን በማዛባትም በውሃ ውስጥ የሚኖሩ ሌሎች ሕይወት ያላቸውን ነገሮች ይገድላል።
በዚህ ላይ ጥናት እና ምርምር እየሠራ ያለው ተቋም ዋና ዳይሬክተር የሆነችው ጃሚና ሹፓክ "ሰውነታችን ብዙ ንጥረ ነገሮችን ይፈጥራል። እነዚህ ንጥረ ነገሮች ደግሞ በከንቱ አይባክኑም። ብዙ ችግሮችን ያስከትላሉ።"
ንጥረ ነገሮቹ ለአልጌዎች ምግብ ናቸው። ከዚህም ባሻገር ለሰብሎችም አስፈላጊ ንጥረ ነገር ናቸው።
"ናይትሮጂንን በየትኛውም ቦታ ብታስቀምጡ ተክሎች እንዲበቅሉ ያግዛል። በውሃ ውስጥ ካለ አልጌዎች እንዲበቅሉ ይረዳል። መሬት ላይ ከሆነ ደግሞ ተክሎች እንዲበቅሉ ይረዳቸዋል" በማለት ሹፓክ ታብራራለች።
አክላም በዚህ ምክንያት በንጥረ ነገር የበለፀገ ሽንትን ከወራጅ ውሃዎች በማሸሽ እና ወደ የእርሻ ማሳ በማምጣት ጎጂ የሆኑ የአልጌ አበቦችን እያስወገድን ገበሬዎች ሰብላቸውን እንዲያመርቱ እናግዛለን ብላለች።
ከተመራማሪዎቹ ቡድን ጋር አብረው የሚሠሩ ገበሬዎች ምን ያህል ሽንት ወደ ማሳቸው እንደሚሄድ፣ ምን ያህሉ ደግሞ በውሃ ፍሳሾች እንደሚወገድ በማስላት ለመቀነስ እርምጃዎችን ይወስዳሉ።
ስለዚህም የተዘራው ሰብል ጠቃሚ ንጥረ ነገሮችን መውሰድ በሚችልበት ጊዜ፣ ከቡቃያ ከፍ ብለው ገና ፍሬ ማፍራት ሳይጀምሩ ጥቅም ላይ ይውላል።
ሽንቱ ለማዳበሪያነት ጥቅም ላይ በሚውልበት ወቅት የሚባክን ነገር እንዳይኖር የአፈር እርጥበቱም ይለካል። "ይህ ማለት ፍሳሽ አይኖርም ማለት አይደለም" ትላለች ሹፓክ።

የፎቶው ባለመብት, Rich Earth Institute
በቬርሞንት የሚገኘው የምርምር ማዕከል በአሜሪካ ሽንትን መልሶ ጥቅም ላይ በማዋል ፈር ቀዳጅ ፕሮጀክት ነው።
ነገር ግን በሌሎች አገሮችም ተመሳሳይ ፕሮጀክቶች በመካሄድ ላይ ናቸው።
በፓሪስ፣ በጎ ፈቃደኞች የሴይን ወንዝ ለመታደግ እና የዳቦ ስንዴን ለማምረት ሽንት እየሰበሰቡ ነው።
የስዊድን ሥራ ፈጣሪዎች በጎትላንድ ደሴት ዙሪያ በአልጌ አበቦች ምክንያት የሚደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ ሽንት የሚሰበስብ እና ወደ ማዳበሪያነት የሚቀይር አሠራር ዘርግተዋል።
በደቡብ አፍሪካ፣ በኔፓል እና በኒጀር ሪፐብሊክም ሽንትን መልሶ ጥቅም ላይ ለማዋል እየተሠራ ነው።
ነገር ግን ይህንን ፕሮጀክት ማስፋፋት እንቅፋቶችም አሉት።
ሹፓክ በቬርሞንት የገበሬዎች የሽንት ፍላጎት ከአቅርቦት ይበልጣል ትላለች።
የሚፈለገውን የሽንት መጠን ለመሰብሰብ እና መልሶ ጥቅም ላይ ለማዋል ደግሞ የአካባቢ አስተዳደሮችም ሆኑ አገራት ሕግ፣ መመሪያ እና ደንብ የላቸውም።
በአንዳንድ አካባቢዎች ሽንትን አጠራቅሞ መልሶ ጥቅም ላይ ለማዋል ከፍሳሽ አስወጋጆች ጋር ለመሥራት መዋዋላቸውን ሹፓክ ታነሳለች።
ከዚህ ባሻገር ደግሞ ሽንትን ከቦታ ቦታ ማጓጓዝ ከባድ መሆኑን ሹፓክ ትገልጻለች።
ሽንትን ሰብሰብበው የሚያጓጉዙ መኪናዎች ሽታዎችን ሊፈጥሩ ይችላሉ። በዚህም የተነሳ በቬርሞንት ሽንት ከቦታ ቦታ የሚጓጓዘው በ16 ኪሎ ሜትር ርቀት ብቻ ነው።
ሽንትን ዳግም ጥቅም ላይ ለማዋል የሚታሰብ ከሆነ ግን ረዥም ርቀት ለማጓጓዝ መፍትሄ መታሰብ እንዳለበት ተመራማሪዎቹ ይመክራሉ።
ከሹፓክ ፕሮጀክት ጋር እየሠራ የሚገኘው የሚቺጋን ዩኒቨርስቲም አቀዝቅዞ በበረዶ መልክ ለማጓጓዝ የሚያስችል ፈጠራ ሠርቶ ጥቅም ላይ ማዋል ጀምሯል።

የፎቶው ባለመብት, Rich Earth Institute
ሌላው ሽንትን መልሶ ጥቅም ላይ ለማዋል ያለው ፈታኙ ጉዳይ ምርት ለመሰብሰብ የሚያስፍለገው ቱቦ ነው።
ሽንትን በመሰብሰብ ሂደት ውስጥ የውሃ ብክነትን ለመቀነስ ሲባል ከመደበኛው የንጽህና ቤት በተለየ ዝቅተኛ ውሃ መጠቀም ይፈለጋል።
በዚህ ወቅት ያለው የሽንት መውረጃ ቱቦ ከተለመደው የተለየ በመሆኑ በሚፈጠረው ሽታ የተነሳ እንደ ኒሞኒያ ላሉ የመተንፈሻ አካል በሽታዎች ተጠቃሚዎችን ሊያጋልጥ ይችላል የሚል ስጋት አለ።
ከዚህ ሁሉ በተለየ ደግሞ ሽንት እንደ ማዳበሪያነት ተመልሶ ጥቅም ላይ ሲውል በውስጡ ያሉ የተለያዩ መድኃኒቶች ጉዳይ የሚያሳስባቸው ግሰለቦች አሉ።
ሹፓክ "በየጊዜው የሚቀርብልን ትልቁ ጥያቄ ነው" ትላለች።
ተመራማሪዎች ሽንትን በማዳበሪያነት ተጠቅመው ባደጉ አትክልቶች ላይ የካፌይን እና የህመም ማስታገሻ በምን ያህል መጠን ይገኛሉ የሚለውን ለማወቅ ጥናት አድርገው ነበር።
በእርግጥ የመጨረሻው ውጤት ገና ይፋ ባይሆንም የመጀመሪያ ግኝት የሚያሳየው ሽንትን በማዳበሪያነት የተጠቀሙ አትክልቶች ውስጥ ያለው የመድኃኒት መጠን "እጅግ በጣም ትንሽ " ነው።
ዊሊያምስ ከጤና ጭንቀቶች እና ውዥንብሮች ባሻገር በአስቸኳይ መለወጥ ያለበት የምዕራባውያን ቆሻሻ አወጋገድ ባህል እንደሆነ ትጠቁማለች።
"በተለይ [በአሜሪካ] ሰዎች ቆሻሻቸው የት እንደሚሄድ በትክክል አያስቡም። በተወሰነ ደረጃ ቆሻሻን ዳግም ጥቅም ላይ ስለማዋል ያስባሉ። ይህም ቢሆን ከሰው አካል ስለሚወጣው ፍሳሽ አወጋገድ እና ዳግም ጥቅም ላይ ማዋል አይደለም። ይህ ለሰው ልጅ አዲስ አድማስ ነው።"












