በኮንጎ የአማጺያን ዘረፋን ተከትሎ 500 የኤምፖክስ ታማሚዎች ከህክምና ማዕከላት አመለጡ

በምስራቅ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በቀጠለው ጦርነት ምክንያት ባለፈው ወር ከ500 በላይ የኤምፖክስ ታማሚዎች ከክሊኒኮች ማምለጣቸው ታውቋል ።

በአህጉሪቱ ግንባር ቀደም የጤና ተቋም የሆነው የአፍሪካ የበሽታዎች መቆጣጠሪያ እና መከላከያ (አፍሪካ ሲዲሲ) ባለስልጣናት እንደገለጹት ባለፈው ዓመት በዲሞክራቲክ ኮንጎ ከ900 ሰዎች በላይ ህይወታቸውን ባጡበት እና በከፍተኛ ሁኔታ በሚዛመተው በሽታ የሚታመሙ ሰዎች መጥፋት ስጋትን ፈጥሯል።

ታማሚዎቹ ጎማ እና ቡካቩ ከተሰኙ ሁለት ከተሞች ሸሽተዋል። ከተሞቹ ባለፉት ሳምንታት በሩዋንዳ በሚደገፈው ኤም23 አማጺያን ቁጥጥር ስር ውለዋል።

በጎማ የሚገኝ የአንድ ክሊኒክ ኃላፊ የሆኑት ዶክተር ሳሙኤል ሙሂንዶ ለቢቢሲ እንደተናገሩት "ተዘርፈናል። መሳሪያዎቻችንን አጥተናል። አደጋ ውስጥ ነን" ብለዋል።

ቀደም ሲል የዝንጀሮ ፈንጣጣ ተብሎ የሚጠራው ኤምፖክስ እንደ ቁስል፣ ራስ ምታት እና ትኩሳት የመሳሰሉ ምልክቶች ይታዩበታል።

እንደ አፍሪካ ሲዲሲ ዘገባ ከሆነ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የበርካታ ወረርሽኞች ማዕከል በሆነችው አገር ከጥር ወር ጀምሮ ወደ 2 ሺህ 890 የሚጠጉ የኤምፖክስ ታማሚዎች ሲመዘገቡ የ80 ሰዎች ህይወት ተቀጥፏል።

ዶ/ር ሙሂንዶ በጥር ወር መገባደጃ ላይ በተፈጠረው ጦርነት ምክንያት 128 ህሙማን ጎማ ከሚገኘው ሙጉንጋ ጤና ጣቢያ እንደሸሹ ገልጸዋል።

በክሊኒኩ ውስጥ ያሉ መረጃዎች ስለወደሙ የጤና ባለሙያዎቹ ታማሚዎቹን መልሰው ማግኘት አልቻሉም ብለዋል።

በጎማ በሚገኘው እና ኤምፖክስን ከሚያክምው ቢሴንጊማና ሆስፒታል ዘራፊዎች መድኃኒቶችንና የግል መከላከያ መሳሪያዎችን ወስደዋል።

ከማዕከሉ ውጭ እሳት የተነሳ ሲሆን ወንጀለኞቹ ሲወጡ የታካሚዎች የህክምና ማስረጃዎች ወለሉ ላይ ተጥለው ተገኝተዋል።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የተከሰተውን ጦርነት በመሸሽ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የተጠለሉበት ካምፕ እንዲዘጋ ኤም23 መወሰኑ ሁኔታውን ይበልጥ ውስብስብ አድርጎታል።

ባለፈው ሳምንትም እንዲለቁ 72 ሰዓታት ቢሰጣቸውም ኤም23 ሃሳቡን በመቀየር "በፍቃደኝነት መመለስ" የሚያበረታታ ነው ብሏል።

"አሁን የተፈናቀሉ ሰዎች ወደ ተመለሱባቸው አካባቢዎች ወረርሽኙ እንዳይከሰት እንፈራለን" ብለዋል ዶክተር ሙሂንዶ።

አፍሪካ ሲዲሲም ፍርሃቱን አስተጋብቷል።

የአፍሪካ ሲዲሲ የኤምፖክስ ሥራ አስኪያጅ ዶ/ር ንጋሺ ንጎንጎ በበኩላቸው "አሁን በድጋሚ የተኩስ አቁም እንዲደረግ እና ለኤጀንሲው የሰብአዊነት ኮሪደር እንዲመቻች እንጠይቃለን" ብለዋል።

ባለፈው ሳምንት አፍሪካ ሲዲሲ ጦርነቱ እየተባባሰ በመሄዱ እና አማጺያኑ ተጨማሪ ግዛት በመቆጣጠራቸው የጠፉ የኤምፖክስ ​​ታማሚዎች ቁጥር በ100 ከፍ ብሏል።

ዶ/ር ንጎንጎ አክለውም በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ "ከፍተኛ የመተላለፍ አቅም ያለው" አዲስ የኤምፖክስ ዝርያ ተገኝቷል።

በኤም23 እና በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ጦር መካከል በተፈጠረው ግጭት እና በገንዘብ እጥረት ምክንያት አገሪቱ ለበሽታው ምላሽ መስጠት እንዳትችል ሆናለች።

በተባበሩት መንግስታት የህጻናት ኤጀንሲ (ዩኒሴፍ) እና በዩኬ ኤድ ዳይሬክት የገንዘብ ድጋፍ የሚደረግለትና በሙጉንጋ የሚገኘው የኤምፖክስ ​​ተቋም ባለፈው ሳምንት እንደገና ሊከፈት ችሏል።

በርካታ ህሙማንን ለማስናገድ በመገደዱ ምክንያት አራት ወይም አምስት ታካሚዎች አንድ አልጋ የሚጋሩበት አጋጣሚ ተፈጥሯል።

ከሁለት ልጆቹ ጋር በሙጉንጋ ህክምና እየተደረገለት የነበረው የ23 ዓመቱ ሳዲኪ ቢቺቺ አሪስቲዴ "መጀመሪያ ከሚኖቫ ወደ ጎማ ተሰደድኩ" ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል።

"(የተፈናቃዮች ካምፕ ውስጥ) መታመም ጀመርኩ። በጣቶቼ ጀመረ። ቀጥሎም ቁስሎች ወጡብኝ፣ እጆቼ መሰነጣጠቅ ጀመሩ። ጎረቤቶቼ ልጆቼን ይዤ ወደ ሙጉንጋ እንድሄድ ሲነግሩኝ ባለቤቴን ትቼ ወጣሁ።"

ባለፈው ሳምንት ወደ ክሊኒኩ ከመድረሱ በፊት ኤምፖክስ የያዛቸው "በጣም ብዙ" ሰዎችን ማየቱን ተናግሯል።

የዩኒሴፍ የጎማ የጤና ባለሙያ የሆኑት ዶ/ር ኡማኒ ሩአፊ ለቢቢሲ እንደተናገሩት የሙጉንጋ ሆስፒታል በድጋሚ የተከፈተበት ብቸኛ ምክንያት ሠራተኞቹ አንዳንድ መሳሪያዎችን እና መድሃኒቶችን ከዘራፊዎቹ መደበቅ በመቻላቸው ነው።

ነገር ግን በሌሎች የህክምና ጣቢያዎች ባለመሳካቱ ሙሉ በሙሉ የተዘረፉ በርካታ ማዕከላት አሉ ሲል ገልጿል።