ሞዛምቢክ በጥብቅ ስትፈልገው የነበረውን አሸባሪ መግደሏን አስታወቀች

ሞዛምቢካውያን ነዋሪዎች

የፎቶው ባለመብት, AFP

ሞዛምቢክ በጥብቅ ስትፈልገው የነበረው እና ከእስላማዊ መንግሥት (አይኤስ) ጋር ግንኙነት ያለው የጂሃዲስት ቡድን መሪን መግደሏን አስታወቀች።

መሪው በአገሪቱ ሰሜናዊ ክፍል እየተዋጋ እንደነበር የተገለጸ ሲሆን በመንግሥት ኃይሎችም መገደሉም ተነግሯል።

ቦኖማዴ ማቹዴ ኦማር ወይም ኢብን ኦማር በመባል የሚታወቀው መሪ ጦርነቱ ከተጀመረበት ከጎሮጎሳውያኑ 2017 ጀምሮ አማጺያኑን ይመራ እንደነበር የአገሪቱ መከላከያ ሚኒስቴር አስታውቋል።

ከኦማር በተጨማሪም ሌሎች ሁለት ከፍተኛ አመራሮች መገደላቸውን የመከላከያ ሚኒስቴር መግለጫ አትቷል።

የአገሪቱ መንግሥት ገድያቸዋለሁ የሚላቸውን አመራሮች በተመለከተ በገለልተኛ ወገን የተረጋገጠ ነገር የለም።

ከሁለት ዓመት በፊት የአሜሪካ መንግሥት ኦማርን አሸባሪ በሚል ፈርጆታል።

በአገሪቱ በካቦ ዴልጋዶ ግዛት በተፈጸሙ ጥቃቶች እንዲሁም ፓልማ በተሰኘው ሆቴል ለበርካቶች ሞት ምክንያት የሆነውን ጥቃት ያቀነባበረው ኦማር እንደሆነም አሜሪካ አስታውቃለች።

ከአንድ ወር በፊት የሞዛምቢክ ጦር ከሩዋንዳ እና ከደቡብ አፍሪካ በመጡ በመቶዎች በሚቆጠሩ ወታደሮች በመታገዝ በአማጺያኑ ላይ ከፍተኛ የጥቃት ዘመቻ መክፈቱን አስታውቆ ነበር።

ኦማር እና ሁለት ተባባሪዎቹ በሰራዊቱ እና የውጭ አጋሮች ጋር በተደረገ የጋራ ዘመቻ በማኮሚያ በሚገኝ ጫካ ውስጥ መገደላቸውንም ነው መንግሥት ያስታወቀው።

የሞዛምቢክ ፕሬዚዳንት ፊሊፔ ኒዩሲ ግድያዎቹ የተከናወኑት ማክሰኞ መሆኑን አርብ ዕለት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተናግረዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በሰሜናዊ ሞዛምቢክ እየተከሰተ ያለው ጦርነት ከአንድ ሚሊዮን በላይ ነዋሪዎች ቀያቸውን ለቀው እንዲወጡ አስገድዷቸዋል ብሏል።

በአገሪቱ ባለው ጦርነት በተጨማሪም በብዙ ቢሊዮን ዶላር የሚገመት የነዳጅ ፕሮጀክት እንዲቆም አስገድዷል።

በጋዝ እና ሩቢ በተሰኘው ማዕድን የበለጸገችው የካቦ ዴልጋዶ ግዛት የተፈጥሮ ሃብቷን መበዝበዝ የሚፈልጉ በርካታ ቡድኖች መስህብ ናት።

በአካባቢዋም በርካታ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ማዕድን በመቆፈር ሥራም ተሰማርተዋል።

ምንም እንኳን አካባቢዋ በተፈጥሮ ሃብቷ የታደለች ቢሆን በርካታ ሞዛምቢካውያን ለከፍተኛ ድህነት የተጋለጡባት ሥፍራ ናት።

የአካባቢው ነዋሪዎች ከመሬት እና የሥራ ዕድል ከማጣት ጋር በተያያዘ የሚያነሷቸው ቅሬታዎች አማጺያኑ በርካታ ሰዎችን እንዲመለምሉ አስተዋጽኦ አድርጓል።

ጦርነቱ እየተካሄደበት ባሉት አምስት ዓመታት ሰላማዊ ዜጎች ከመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች እና አማጺያን አሰቃቂ ጥቃቶች እንደደረሰባቸው የመብት ተሟጋቾች ይናገራሉ።