የፈረንሳይ ፖሊስ ለትራፊክ አልታዘዝ ያለን ታዳጊ ተኩሶ ገደለ

በመኪናው መስኮት አጠገብ ከሚታዩ ፖሊሶች አንደኛው መሣሪያ ደግኖ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የፈረንሳይ ፖሊስ ማክሰኞ ዕለት ከፓሪስ ከተማ ውጪ በትራፊክ ፖሊስ እንዲቆም ቢታዘዝም ለመቆም ፈቃደኛ ያልሆነውን የ17 ዓመት ታዳጊ ተኩሶ ገደለ።

በማኅበራዊ ሚዲያ የተሰራጩ ተንቀሳቃሽ ምስሎች እንደሚያሳዩት የተኩስ ድምጽ ከመሰማቱ በፊት የፖሊስ መኮንኑ በመኪናው አሽከርካሪ ላይ መሣሪያ ደግኖ ታይቷል። ከዚያ በኋላም መኪናው ተጋጭቶ ቆሟል።

በተተኮሰበት ጥይት ደረቱ ላይ የተመታው የ17 ዓመቱ ታዳጊ የሕክምና እርዳታ ቢደረግለትም እዚያ ቦታው ላይ ሕይወቱ አልፏል።

ይህንን ተከትሎም በፈረንሳይ ቁጣ ተቅስቅሷል። ምሽቱን በተቀሰቀሰ ተቃውሞ አለመረጋጋት የተፈጠረ ሲሆን 15 ሰዎችም በቁጥጥር ሥር ውለዋል።

አደጋውን የሚያሳየው ተንቀሳቃሽ ምስል በፈረንሳዩ የዜና ወኪል ኤኤአፍ ፒ የተረጋገጠ ሲሆን ሁለት የፖሊስ መኮንኖች መኪናውን ለማስቆም ሲሞክሩ ያሳያል። አንደኛው በመኪናው መስኮት መሣሪያውን በአሽከርካሪው ላይ የደገነ ሲሆን ታዳጊው ለመንቀሳቀስ ሲሞክር የተኮሰ ይመስላል።

የዜና ወኪሉ እንደዘገበው በተንቀሳቃሽ ምስሉ ላይ አንድ ግለሰብ "ጭንቅላትህ ላይ ልትመታ ነው" ሲል ይሰማል። ይሁን እንጂ ይህን የተናገረው ማን እንደሆነ ግልጽ አይደለም።

ናኤል ኤም የተባለው ታዳጊው ሲያሸከረክር በነበረው መኪና ውስጥ ሁለት ሌሎች ግለሰቦች የነበሩ ሲሆን አንደኛው ሲያመልጥ ሌላኛው በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ውሏል።

ታዳጊው ላይ የተኮሰው የ38 ዓመቱ የፖሊስ መኮንንም በግድያ ወንጀል ተከሷል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ግድያውን ተከትሎ ታዳጊው በተገደለበት በምዕራብ ፓሪስ ናንቴሬ ማክሰኞ ምሽት ተቃውሞ ቀስቅሷል።

በዚህም መኪኖች እና የቆሻሻ መጣያዎች በእሳት የተቃጠሉ ሲሆን የአውቶብስ ማቆሚያዎችም ወድመዋል።

የአድማ በታኝ ፖሊስ ተቃዋሚዎቹን ለመበተን አስለቃሽ ጭስ ተጥቅሟል። የተወሰኑትም ምሽቱን መንገድ ዘግተዋል።

የፈረንሳይ ባለሥልጣናትም ሁለት የተለያዩ ምርመራዎችን ከፍተዋል።

የፓሪስ ፖሊስ አዛዥ ሎረንት ኑኔዝ ለፈረንሳይ ቴሌቪዥን ጣቢያ (ቢኤፍኤምቲቪ) እንደተናገሩት የፖሊስ መኮንኑ ታዳጊው ላይ ቃታውን የሳበው ስጋት ገብቶት ሊሆን እንደሚችል ጠቁመው፣ የፖሊሱ ድርጊት ግን ጥያቄዎችን አስነስቷል ብለዋል።

የ17 ዓመቱ ታዳጊ ቤተሰቦች ጠበቃ ያሲን ቦዝሮም በበኩላቸው ድርጊቱን ሕገ ወጥ የሆነ መከላከል ነው ያሉ ሲሆን ቪዲዮው ፖሊሱ ታዳጊውን በግፍ ሲገድለው አሳይቷል ሲሉ ለቴሌቪዥን ጣቢያው ተናግረዋል።

የተጎጂ ቤተሰቦችን የወከሉት ሌላ ጠበቃ ጀኒፈር ካምብላ ለአገር ወስጥ መገናኛ ብዙኃን እንደተናገሩት "የተከሰተው አደጋ ምክንያታዊ ለማድረግ የሚያስችል ነገር የለም። የታዳጊው ሞት ምክንያት ግድያ ነው"

በማኅበራዊ ሚዲያ የተጋራውን ተንቀሳቃሽ ምስል "በጣም አስደንጋጭ" ያሉት የፈረንሳይ የውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ጀራልድ ዳርማኒን፣ በክስተቱ ላይ የተሳተፉት ሁለቱ የፖሊስ መኮንኖች በፖሊስ ምርመራ እንደተደረገባቸው ማክሰኞ ዕለት ለምክር ቤቱ ተናግረዋል።

በፈረንሳይ ተመሳሳይ ከስተት ሲያጋጥም ይህ የመጀመሪያው አይደለም።

ከሁለት ሳምንታት በፊትም በምዕራብ ፈረንሳይ በምትገኘው ከተማ በትራፊክ መቆሚያ ላይ የፖሊስ መኮንን ገጭቷል በሚል የ19 ዓመቱ አሽከርካሪ በፖሊስ ተተኩሶበት ተገድሏል።

ባለፈው ዓመት ደግሞ ከትራፊክ መቆሚያ ጋር ተያይዞ በፖሊስ በተተኮሰባቸው ጥይት በቁጥር ከፍተኛ የተባለው 13 ሰዎች ተገድለዋል።