ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በሞዛምቢክ ሐሰተኛ የአይፎን ስልኮችን ያመርታሉ የተባሉ ቻይናውያን በፖሊስ ተያዙ
በደቡባዊ አፍሪካዊቷ ሞዛምቢክ ውስጥ ሐሰተኛ አይፎን ስልኮችን በማምረት የተጠረጠሩ ሁለት የቻይና ዜጎች በቁጥጥር ሥር ዋሉ።
የአገሪቱ ባለሥልጣናት ከሁለቱ ግለሰቦች በተጨማሪ 1 ሺህ 165 ሐሰተኛ የአፕል አይፎን ስልኮች መያዛቸውን አስታውቀዋል።
ሁለት የቻይናውያን በቁጥጥር ሥር የዋሉት ሐሰተኛ አይፎኖችን በሚያመረቱበት በአገሪቷ ዋና ከተማ ማፑቶ ውስጥ በሚገኝ አፓርትመንት ውስጥ ነው።
ፖሊስ እንደገለጸው ተጠርጣሪዎቹ የቻይና ዜጎች፣ ለስልኮቹ የተለየ መለያ (ሲሪያል) ቁጥርን ጨምሮ ውስብስብ የሆኑ ስልታዊ አካሄዶችን ተጠቅመዋል።
ይሁን እንጂ በፖሊስ የተያዙት ተጠርጣሪ ቻይናውያን የፈፀምነው ምንም ዓይነት ስህተት የለም ብለዋል።
የጉምሩክ ባለሥልጣናት በደረሳቸውን ጥቆማ መሠረት ባደረጉት ክትትል ተጠርጣሪዎቹ መያዛቸውን ገልጸዋል።
በማፑቶ ከተማ የሞዛምቢክ የጉምሩክ ዳይሬክተር የሆኑት ጊኖ ጆን “የደረሰን ጥቆማ ጥርጣሬ ፈጠረብን። ጥቆማውን ይዘን ትክክለኛነቱን ለማረጋገጥ የኦፕሬሽን ሰንሰለቶቻችንን ዘረጋን።ከዚያም ከሦስት ሳምንታት ምርመራና ክትትል በኋላ ይህንን የሐሰተኛ አፕል አይፎን ስልኮች መገጣጠሚያ ፋብሪካ አገኘነው” ብለዋል።
ዳይሬክተሩ ጨምረውም ከተያዙት ስልኮች መካከል የተወሰኑት በሕገ ወጥ መንገድ ወደ አገሪቱ ገብተዋል ተብለው የተጠረጠሩ መሆናቸውንና ሌሎቹ ደግሞ በስርቆት የተገኙ መሆናቸውን ተናግረዋል።
“የመኖሪያ ሕንጻን ነው እንደ ፋብሪካ ሲገለገሉበት የነበረው። ሐሰተኛ የሞባይል ስልኮች እዚህ ተሰርተዋል። ልዩ የሆነው ዓለም አቀፍ የሞባይል ስልኮች መለያ (ሲሪያል) ቁጥር ተሰጥቷቸው የሚሸጡት ደግሞ አልቶ ሜይ በተባለ አካባቢ በሚገኝ ሱቅ ውስጥ ነው” ብለዋል።
በአፍሪካ እና በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ውስጥ በዋጋቸው ውድ የሆኑ የሞባይል ቀፎዎችን በሕገ ወጥ መንገድ አስመስሎ በመስራት ገበያ ላይ ይውላሉ።
በዚህም ተጠቃሚዎች ለሐሰተኛ ምርቶቹ ከፍተኛ ዋጋን ከመክፈላቸው በተጨማሪ ተገቢውን አገልግሎት ባለማግኘት ለኪሳራ ይዳረጋሉ።
ስለዚህም እንዲህ ዓይነት ቁሳቁሶችን ከሚታወቁ የምርት አቅራቢዎች እንዲገዙ ተጠቃሚዎች ይመከራሉ።