ሶማሊያ በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል በተፈጠረው ውጥረት ገለልተኛ መሆኗን ገለፀች

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

የሶማሊያ ውጭ ጉዳይ ምክትል ሚኒስትር ሐሰን ሞሐመድ አሊ በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል በተፈጠረው ውጥረት አገራቸው "ገለልተኛ" መሆኗን ተናገሩ።

ምክትል ሚኒስትሩ ይህንን ያሉት ከቢቢሲ ሶማልኛ ጋር እሁድ ጥቅምት 1/2019 ዓ.ም. በነበራቸው ቃለ ምልልስ ወቅት ነው።

"የሶማሊያ መንግሥት አቋም ሰላማዊ እና ገለልተኛ ነው" ያሉት ሚኒስትሩ ከአገራቱ ጋር ታሪካዊ፣ መልክዓ ምድራዊ እንዲሁም ሃይማኖታዊ ትስስር እንዳለ ተናግረዋል።

ሶማሊያ ባለፈው ሳምንት ከግብፅ፣ ሱዳን እና ኤርትራ ጋር በመሆን የፈረመችው የኤል አላሚን ስምምነት ከአባይ ወንዝ አጠቃቀም አንጻር የታችኛው ተፋሰስ አገራት የሆኑትን ግብፅ እና ሱዳንን የሚጎዳ የተናጠል ድርጊትን ውድቅ ያደርጋል።

መስከረም 24/2019 ዓ.ም. በግብፅ በተካሄደው የአራትዮሽ ጉባዔ ላይ ተሳትፋ ከኢትዮጵያ ጋር በሕዳሴ ግድብ የሚወዛገቡት ሱዳን እና ግብፅን አቋም የሚደግፍ፣ በድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ላይ ተፈጻሚነት ያላቸውን ዓለም አቀፍ ሕጎች ማክበር አስፈላጊ መሆኑን የሚገልጽ መግለጫ አውጥታለች።

በጉባዔው ላይ የግብፁ ፕሬዝዳንት አብዱል ፋታህ አል ሲሲ፤ የኤርትራው ኢሳያስ አፈወርቂ፣ የሶማሊያው ሐሰን ሼኽ ሞሐሙድ እና የሱዳን ሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤት ሊቀመንበር ጄነራል አብዱል ፋታህ አል ቡርሃን ተሳትፈዋል።

በተጨማሪም አራቱ አገራት በቀይ ባሕር ላይ የሚደረግ የመርከቦች እንቅስቃሴ ነፃነት መብትን በመግለጫቸው ላይ ጠቅሰው፣ የቀይ ባሕር አስተዳደር እና ቁጥጥር በቀይ ባሕር ዳርቻ በሚገኙ አገራት ብቸኛ ኃላፊነት ስር የሚወድቅ መሆኑን አስታውቀዋል።

ኢትዮጵያ እና ኤርትራ መካከል ያለው ፍጥጫ በተካረረበት ወቅት የተደረገው ይህ ጉባዔ ባወጣው የጋራ መግለጫ በአፍሪካ ቀንድ የሚፈጠሩ ውጥረቶች እና አለመግባባቶች ፖለቲካዊ እና ሰላማዊ መፍትሄዎች እንዲፈለጉ ጥሪ አቅርቧል።

በግብፅ ኤል አላሚን ከተማ በተካሄደው የአራቱ አገራት የመሪዎች ጉባኤ ማጠቃለያ ላይ የወጣው ይህ የጋራ መግለጫ፣ የቀጣናው መረጋጋት በሉዓላዊነት፣ በግዛት አንድነት፣ በመልካም ጉርብትና ግንኙነት መርሆዎች መከበር ላይ እንዲሁም በውስጣዊ ጉዳዮች ላይ ጣልቃ አለመግባትን እንደሚያካትት ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ከጉባዔው በኋላ ባወጣው መግለጫ ከአባይ ወንዝ እና ከቀይ ባሕር ጋር የተያያዙ መልክዓ ምድራዊ እና ታሪካዊ እውነታዎች በፖለቲካ ትርክቶች እና በኃይል እርምጃዎች ሊቀየሩ አይችሉም ብሏል።

የሶማሊያ ውጭ ጉዳይ ምክትል ሚኒስትር ሐሰን ሞሐመድ አሊ አገራችው ከሁለቱም አገራት ጋር በተለያዩ ጉዳዮች አብሮ የመሥራት ስምምነት እንዳላት አስታውሰው ሶማሊያ "በቀጣናው የሚካሄደውን ለውጥ በቅርበት እየተከታተለች ነው" ብለዋል።

ሚኒስትሩ አክለውም ሶማሊያ የራሷን እና የቀጣናውን ጥቅም ለማስከበር እየሠራች መሆኑንም ጨምረው ገልጸው "ከሁሉም አገራት ጋር መልካም የሚባል ግንኙነት አለን። በዚህ ረገድ ምንም የተቀየረ ነገር የለም" ብለዋል

"ቀጣናው በአሁኑ ወቅት በርካታ ተግዳሮቶች እየገጠሙት ነው። ዋናው ትኩረት ተጨማሪ ችግሮችን ከመፍጠር መቆጠብ እና እንደ ደኅንነት፣ ኢኮኖሚ እና የመንቀሳቀስ ነጻነት ባሉ ጉዳዮች ላይ ተጽዕኖ እያሳደሩ ያሉትን ነባር ችግሮች መፍታት ነው" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ሶማሊያ ብሔራዊ ጥቅሞቿንና አንድነቷን በመጠበቅ ረገድ እነዚህን ተግዳሮቶች ለመፍታት የበኩሏን ሚና መወጣት አለባት ያሉት ሚኒስትሩ፣ "በቀጣናዊ ጉዳዮች ላይም አስተዋጽኦ የማድረግ ኃላፊነት አለባት።"

በአገራቱ መካከል ባለው ውጥረት ውስጥ ሶማሊያ ገለልተኛ አቋም ይዛ እንደሆነ ተጠይቀው ሲመልሱ ሚኒስትሩ ሲመልሱ ሞቃዲሾ ከሁሉም አገራት ጋር ጥሩ ግንኙነት እንዳላት ገልጸዋል።

"ሶማሊያ በዚህ ረገድ ገለልተኛ አቋም አላት፤ ከእነዚህ አገራት ሁሉ ጋርም ጥሩ ግንኙነት አለን። እኛ እስከምናውቀው ድረስ በእነዚህ ግንኙነቶች ላይ ምንም ዓይነት ለውጥ አልተከሰተም" ብለዋል።

ኢትዮጵያ ነጻ አገርነቷን ካወጀችው ሶማሊላንድ ጋር የመግባቢያ ስምምነት ከፈረመች በኋላ ከሶማሊያ ጋር ውዝግብ ውስጥ ገብታ የነበረ ሲሆን፣ በቱርክ አሸማጋይነት አለመግባባታቸውን መፍታታቸው ይታወቃል።

ሶማሊያ ከኢትዮጵያ አንጻር ከተመሠረተው የአራት አገራት ጥምረት ውስጥ በመግባት በአባይ እና በቀይ ባሕር ጉዳይ የኢትዮጵያን ፍላጎት የሚጻረር የአቋም መግለጫ ላይ ተሳታፊ መሆኗ በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን ግንኙነት ሊያበላሸው እንደሚችል በስፋት ሲነገር ነበር።

ኢትዮጵያ የሶማሊያን መንግሥት ለመጠበቅ እና ለመደገፍ ከሁለት አስር ዓመታት በላይ ወታደሮቿን ያሰማራች ሲሆን፣ በሶማሊያ ውስጥ አል ሻባብን በመዋጋት እና የአገሪቱን ፀጥታ በመጠበቅ ውስጥ ጉልህ ሚና አላት።

ግብፅ ውስጥ በተካሄደው እና ኤርትራ፣ ሱዳን እና ሶማሊያ ያወጡት የአቋም መግለጫ ኢትዮጵያ በግልጽ የተቃወመችው ነው።