ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በዲሞክራቲክ ኮንጎ እየተካሔደ ያለው ምንድነው? በግጭቱ ሩዋንዳ ለምን ትሳተፋለች?
በማዕድን የበለፀገችው ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ላለፉት 30 ዓመታት በግጭት ስትታመስ ቆይታለች። በተለይ ደግሞ ከሩዋንዳ የዘር ጭፍጨፋ በኋላ በዲሞክራቲክ ኮንጎ ሰላም ሰፍኖ አያውቅም።
የተለያዩ የታጠቁ ቡድኖች ማዕከላዊውን መንግሥት ለማውረድ እና ሰፊዋን ሀገር ለመቆጣጠር ሙከራ አድርገዋል።
በዲአር ኮንጎ ያለው አለመረጋጋት ጎረቤትን ሀገራትንም የሚነካ ነው። በተለይ በ1990ዎቹ የአፍሪካ የዓለም ጦርነት በተባለለት ግጭት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ሞተዋል።
በጎማ እየሆነ ያለው ምንድነው?
ኤም23 የተባለው አማፂ ቡድን በምሥራቅ ዲሞክራቲክ ኮንጎ የምትገኝ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ነዋሪዎች ያላትን ጎማ ከተማ በቅፅበታዊ ጥቃት በቁጥጥር ሥር አውሏል።
ጎማ ከሩዋንዳ ጋር በሚዋሰነው ድንበር ላይ ትገኛለች። ከተማዋ በማዕድን ለበለፀጉ በርካታ ሥፍራዎች ቅርብ ናት። በተለይ ወርቅ፣ ኮልተን እና ቲን የተባሉ ማዕድኖች የሚወጡት እዚህ አካባቢ ነው።
ቲን እና ኮልተን ለሞባይል ስልክ እና ለኤሌክትሪክ መኪናዎች ባትሪ ማምረቻ የሚውሉ ተፈላጊ ማዕድኖች ናቸው።
አማፂያኑ ከተማዋን መቆጣጠራቸውን አሳውቀዋል። ነገር ግን የኮንግ መንግሥት ወታደሮቹ አሁንም ቁልፍ የሚባሉ ቦታዎችን እንደተቆጣጠረ አሳውቋል።
ኤም23 ማነው?
ኤም23 የቱትሲ ጎሳ አማፂ ቡድን ነው። ቡድኑ የጦር መሣሪያ የታጠቀው አናሳ ጎሳ መሆኑን ተከትሎ ራሱን ለመከላከል እንደሆነ ይናገራል።
የቡድኑ አባላት እንደሚሉት ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ ግጭቱ እንዲቆም የደረሷቸው ስምምነቶች አልተከበሩም። ኤም23 የተባለው ስም የመጣው በአውሮፓ መጋቢት 23/2009 ከተደረሰው የሰላም ስምምነት ነው።
አማፂው ቡድን በ2012 ከተቋቋመ በኋላ በፍጥነት ተስፋፍቶ ጎማን ተቆጣጠረ። ይህን ድርጊቱን ተከትሎ የጦር ወንጀል እና የሰብዓዊ መብት ጥሰት ፈፅሟል የሚል ወቀሳ ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ተሰማ።
ኤም23 ከጎማ ለቆ ከወጣ በኋላ በኮንጎ ጦር ሠራዊት እና በተባበሩት መንግሥታት ኃይል በደረሰበት ከፍተኛ ሽንፈት ምክንያት ከሀገር ለመውጣት ተገደደ።
የኤም23 ተዋጊዎች ቱትሲዎች ጥበቃ የሚደረግላቸው ከሆነ ጦር ሠራዊቱን ተቀላቅለው ለማገልገል ተስማሙ።
ነገር ግን በ2021 ቡድኑ ድጋሚ ታጥቆ ወደ ጫካ በመግባት የተገባው ቃል መሰበሩን አሳወቀ።
ሩዋንዳ በግጭቱ ተሳታፊ ናት?
ጎረቤት ሀገር ሩዋንዳ ኤም23ን ትደግፋለች የሚለውን ወቀሳ በተደጋጋሚ ታስተባብላለች። ቢሆን የተባበሩት መንግሥታት ባለሙያዎች ከ2012 ጀምሮ ሩዋንዳ የጦር መሣሪያ፣ ሎጂስቲክ እንዲሁም አማፂ ቡድኑን በመምራት ሩዋንዳን ይወቅሳሉ።
የዲአር ኮንጎ መንግሥት፣ ዩናይትድ ስቴትስ እና ፈረንሳይም እንዲሁ ሩዋንዳ ቡድኑን ትደግፋለች ይላሉ። ባለፈው ዓመት የተባበሩት መንግሥታት ሙያተኞች 4 ሺህ የሚሆን የሩዋንዳ ወታደሮች ከኤም23 ጎን እየተዋጉ ነው ብለው ነበር።
ሩዋንዳ ባለፈው እሑድ ባወጣችው መግለጫ ኤም23 የተባለውን ቡድን መርዳቷን ባትክድም ድንበር አካባቢ ያለው ግጭት "የግዛት አንድነቷ እና ፀጥታዋ ላይ አደጋ እንደደቀነ" ገልፃለች።
መግለጫው አክሎ የኮንጎ ባለሥልጣናት ከኤም23 ጋር ለድርድር ለመቀመጥ ባለመሻታቸው ምክንያት ግጭቱ በመባባሱ ሩዋንዳ ስሟ እየጠፋ ነው።
ባለፈው ዓመት ዲአር ኮንጎ እና ሩዋንዳ የተሳተፉበት አንጎላ ያሸማገለችው የሰላም ድርድር ውጤታማ ሳይሆን ቀርቷል።
ከሩዋንዳ ጋር ያለው ግንኙነት ምንድነው?
አሁን ያለው ግጭት ከአውሮፓውያኑ 1994 የሩዋንዳ የዘር ጭፍጨፋ ጋር የሚያገናኘው ነገር አለው።
በወቅቱ 800 ሺህ የሚሆኑ የቱትሲ ማኅበረሰብ አባላት በሁቱ አክራሪዎች ተጨፍጭፈዋል። የዘር ጭፍጨፋው የተቋጨው የቱትሲ አማፂ ኃይል ያደረገውን ግስጋሴ ተከትሎ ነው። የወቅቱ የታጣቂ ቡድኑ መሪ የአሁኑ የሩዋንዳ ፕሬዝደንት ፖል ካጋሜ ናቸው።
የበቀል እርምጃን በመሸሽ ከአንድ ሚሊዮን በላይ የሚሆን ሁቱዎች ወደ ዲአር ኮንጎ ተሰደዱ። የሩዋንዳ ጦር ሁለት ጊዜ ዲአር ኮንጎን ወሯል። ምክንያቱ ደግሞ የዘር ጭፍጨፋ ፈፅመው ወደ ኮንጎ የተሰደዱ ሰዎችን ለማጥቃት በሚል ነው።
ግጭቱ 30 ዓመታት ቢያልፉትም ዲሞክራቲክ ፎርስስ ፎር ዘ ሊበሬሽን ኦፍ ሩዋንዳ የተባለው በሁቱዎች የሚመራው እና ለሩዋንዳ ዘር ጭፍጨፋ ተጠያቂ የሆነው ቡድን አሁን ዲአር ኮንጎ ውስጥ ይንቀሳቀሳል።
ሩዋንዳ ይህን ቡድን 'ዘር ጨፍጫፊ ሚሊሻ' ትለዋለች። የኮንጎ ባለሥልጣናት ከቡድኑ ጋር አብረው እየሠሩ ነው ስትልም ትወቀሳለች። ኮንጎ ይህን ወቀሳ ታስተባብላች።
ይህ ታጣቂ ቡድን ለኪጋሊ ስጋት መሆኑ እስካላቆመ ድረስ ሩዋንዳ ከዲአር ኮንጎ የምትወጣ አይመስልም።
ሩዋንዳ በምሥራቅ ዲአር ኮንጎ ያለውን ግጭት ተጠቅማ ከማዕድን ሀብቱ ተቋድሳለች ብለው የሚወቅሱም ብዙዎች ናቸው።
የተባበሩት መንግሥት ምን እየሠራ ነው?
የተባበሩት መንግሥታት ኃይል ከአውሮፓውያኑ 1999 ጀምሮ በሥፍራው ነበር። አሁን ያለው ኃይል ከ10 ሺህ ወታደሮች የያዘ ነው።
ነገር ግን ፎርስ ኢንተርቬንሽን ብርጌድ ከተባለው ክንፍ ውጪ ታጣቂዎች ላይ እርምጃ መውሰድ አይችልም። ይህ ብርጌድ በ2013 ኤም23 እንዲጠናከር አስተዋፅዖ ያደረገ ነው።
የተባበሩት መንግሥት ኃይል ሥራውን እየሠራ አይለደም ብለው የሚወቅሱ የኮንጎ ዜጎች ብዙ ናቸው። ፕሬዝደንት ፌሊክስ ቲሼኬዲ የመንግሥታቱ ኃይል ባለፈው የአውሮፓውያኑ ዓመት መገባደጃ ለቆ እንዲወጣ ጠይቀው ነበር። ቢሆንም ቆይታው ለአንድ ዓመት እንዲራዘም ሆኗል።
የደቡብ አፍሪካ ሀገራት ጥምረት የሆነው ሳዴክ ወታደሮቹን በዲአር ኮንጎ ቢያሰማራም የአማፂያኑን ጥቃት ማስቆም አልቻለም።
ደቡብ አፍሪካ ባለፈው ሳምንት በነበረ ጥቃት 9 ወታደሮቿ እንደተገደሉ አሳውቃለች። ሦስት የማላዊ ወታደሮችም ተገድለዋል። የተባበሩት መንግሥታት ኃይል አባል የሆነ አንድ ኡራጋዊ ወታደርም መገደሉ ተዘግቧል።