አይሲሲ አሜሪካ በዳኞቹ እና በአቃቢያነ ሕጎቹ ላይ የጣለችውን አዲስ ማዕቀብ በጽኑ አወገዘ

ዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት (አይሲሲ) አሜሪካ በዳኞቹ እና አቃቤ ሕጎች ላይ የጣለችውን አዲስ ማዕቀብ በጽኑ አንደሚያወግዝ ገለፀ።

ረቡዕ ዕለት የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአይሲሲ ሁለት ዳኞች እና ሁለት አቃቤ ሕጎች ላይ የአሜሪካ እና የእስራኤል ዜጎችን ለመክሰስ በሚያደርጉት ጥረት የተነሳ አዲስ ማዕቀብ እንደሚጥል አስታውቋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ አይሲሲን በአሜሪካ እና በእስራኤል ላይ "የብሔራዊ ደህንነት ስጋት" በመደቀን እና "ሕግን ለማጥቂያ መሳሪያነት" በመጠቀም ወንጅለዋል።

የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ የአሜሪካን እርምጃ አወድሰዋል።

አይሲሲ ኔታንያሁ እና የቀድሞው የመከላከያ ሚኒስትር ዮአቭ ጋላንት እስራኤል በጋዛ ባካሄደችው ጦርነት ምክንያት በጦር ወንጀሎች እና በሰብአዊነት ላይ በፈጸሙት ወንጀሎች የተነሳ የእስር ማዘዣ አውጥቶባቸዋል።

በአሜሪካ ማዕቀብ ከተጣለባቸው መካከል አንዱ የሆኑት ኒኮላስ ጊሎው ዜጋዋ የሆኑት ፈረንሣይ ድርጊቱን "አሳዛኝ" ስትል በማውገዝ ከአይሲሲን ጎን ቆማለች።

በአሜሪካ ማዕቀብ የተጣለባቸው ሌሎች ሦስት የአይሲሲ ኃላፊዎች የካናዳው ዳኛ ኪምበርሊ ፕሮስት እንዲሁም የፊጂ ዜግነት ያላቸው ምክትል አቃቤ ሕግ ናዝሃት ሻሚም ካን እና ሴኔጋላዊው ማሜ ማንዲያዬ ኒያንግ ናቸው።

ሩቢዮ ፍርድ ቤቱን "በፖለቲካዊ አሰራር፣ ስልጣን አላግባብ በመጠቀም እና በሕገ ወጥ የተለጠጠ ዳኝነት" ጠቅሰው በመግለጫቸው ላይ አውግዘዋል።

አይሲሲ በዘር ማጥፋት፣ በሰብዓዊነት ላይ በተፈጸሙ ወንጀሎች እና በጦር ወንጀሎች ላይ ክስ የማቅረብ ስልጣን ያለው ዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት ነው።

ፍርድ ቤቱ አሜሪካ አሁን የጣለችውን ማዕቀብ ነፃነቱን እና ገለልተኝነቱን የሚጋፋ "ግልጽ ጥቃት" ሲል ገልጾታል።

አክሎምም "እንዲሁም ሁሉም ሰው ሊከተላቸው ለሚገባቸው ዓለም አቀፍ ሕጎች እና ከሁሉም በላይ ደግሞ በዓለም ላይ ለሚሰቃዩ በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ንፁኃን ሰዎች ስድብ ነው" ብሏል።

የፈረንሳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ማዕቀቡ "ከገለልተኛ የፍትህ አካል መርህ ጋር የሚቃረን ነው" ሲል መተቸቱን አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ ውሳኔውን በደስታ ተቀብለውታል።

"በእስራኤል ላይ የተወሰደውን አስከፊ የስም ማጥፋት ዘመቻ የሚቃወም ጠንካራ እርምጃ ነው።"

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት እንደገለጸው ጊሎው በኔታንያሁ እና ጋላንት ላይ የእስር ማዘዣ በመፍቀዳቸው የተነሳ ማዕቀብ ተጥሎባቸዋል።

እንዲሁም ካናዳዊው ዳኛ ፕሮስት በአፍጋኒስታን በሚገኙ የአሜሪካ ወታደሮች ላይ በሚደረገው ምርመራ የተነሳ ማዕቀብ እንደተጣለባቸው ገልጾ፣ ካን እና ኒያንግ ሁለቱም "በእስራኤል ላይ ሕጋዊ ያልሆኑ እርምጃዎች" ተጠያቂ ናቸው ብሏል።

ማዕቀቡ አራቱም የሕግ ባለሙያዎቹ በአሜሪካ ያላቸውን ማንኛውንም ንብረት እንዳያንቀሳቅሱ ያግዳል።

ይህ የአሁኑ ማዕቀብ በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ አሜሪካ በሌሎች አራት ዳኞች እንዲሁም በአይሲሲ ዋና አቃቤ ሕግ ካሪም ካን ኬሲ ላይ ከጣለችው ጋር ተመሳሳይ ነው።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ኃላፊ ከዚህ ቀደም ውሳኔው "የሕግ የበላይነትን ከማክበር" ጋር በቀጥታ ይቃረናል በማለት አሜሪካ በአራቱ ዳኞች ላይ የጣለችውን ማዕቀብ እንድታነሳ ጠይቀው ነበር።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በሐምሌ ወር ላይ የትራምፕ አስተዳደር እስራኤል በጋዛ የምትፈጽመውን ወታደራዊ ጥቃት፤ በድፍረት በመተቸት የሚታወቁትን በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ልዩ ራፖርተር ፍራንቼስካ አልባኔሴ ላይ ማዕቀብ ጥሏል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ እርምጃውን ልዩ ራፖርተሯ ለዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት (አይሲሲ) ካላቸው ድጋፍ ጋር አያይዘውታል።

አልባኔሴ በኤክስ ገጻቸው ላይ በለጠፉት መልዕክት ማዕቀቡን በሚመለከት በቀጥታ ባይናገሩም "ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በዚህ ቀንም ሁልጊዜ እንደማደርገው ከፍትህ ጎን በፅኑ እና በአሳማኝ ሁኔታ እቆማለሁ" ብለዋል።

በጣሊያን የተወለዱት ልዩ ራፖርተሯ ከዚህ በፊት ለአይሲሲ የጻፏቸውን የድጋፍ መልዕክቶች ዳግም በማጋራት፤ ችሎቱን ከመሠረቱ አገራት መካከል መገኘታቸውን ጠቅሰው ጠበቆች እና ዳኞች "ፍትሕን ከፍ ባለ ዋጋ ብዙ ጊዜ በራሳቸው ሕይወት ጭምር ይከላከላሉ" ብለዋል።

"ይህንን ባህል ለማክበር አስባለሁ" ሲሉ በልጥፋቸው ላይ ጽፈዋል።