በዓለም ታዋቂ የሆነው ፎቶግራፍ ከ50 ዓመታት በኋላ ያስነሳው የባለቤትነት ውዝግብ
![የደቡብ ቬየትናም ኃይሎች የ9 ዓመቷን ኪም ፑክን ጨምሮ [መሃል ላይ] የተሸበሩ ሕፃናትን ሲከተሉ](https://ichef.bbci.co.uk/ace/ws/640/cpsprodpb/26ce/live/00605760-4394-11f0-bace-e1270fc31f5e.jpg.webp)
የፎቶው ባለመብት, AP
በፎቶው ላይ ተቀጣጣይ ፈሳሽ የተረጨባት አንዲት እርቃኗን የሆነች ታዳጊ ከሌሎች ሕፃናት ጋር በስቃይ እና በአስፈሪ ሁኔታ ስትሮጥ ትታያለች።
ፎቶግራፉ 'ዘ ቴረር ኦፍ ዋር' ወይም 'ናፓልም ገርል' የሚል አርዕስት ተሰጥቶታል። ይህ ፎቶ የቬትናም ጦርነትን አስከፊነት በታዳጊዋ ስቃይ ውስጥ ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ነው። ለቬትናማውያን የፎቶ ጋዜጠኞችም የኩራት እና የተነሳሽነት ምንጭ ሆኖ ቆይቷል።
ፎቶ አንሽው ኒክ ኡት በዚህ ፎቶ ፑሊቲዘር የተባለውን ዓለም አቀፍ ሽልማት በማሸነፍ የመጀመሪያው እና ብቸኛው የቬትናም ተወላጅ ሆኗል።
አንድ ስሙን መግለፅ ያልፈለገ ቬትናማዊ ፎቶግራፈር፣ ኒክ ኡትን "ምርጥ" ሲል ገልጾታል። 'መምህሩ' እየተባለ በአድናቆት የሚጠራው ኡት፣ ብዙ ጊዜ ወደ አገሩ ይመላለስ የነበረ ሲሆን በርካታ ቬትናማውያን የፎቶ ጋዜጠኞችን አሠልጥኗል፤ ልምዱንም አጋርቷል።
ሆኖም ከ50 ዓመት በኋላ ከፎቶግራፉ ባለቤትነት ጋር በተያያዘ ሙግት ገጥሞታል።
ይህ ፎቶግራፍ ጥር ላይ በሰንዳንስ ፊልም ፌስቲቫል ላይ በቀረበው 'ዘ ስትሪንገር' ዘጋቢ ፊልም ላይ ጥያቄ ተነስቶበታል።
ፊልሙ ፎቶግራፉ አሁን የ87 ዓመት የዕድሜ ባለጸጋ በሆኑት ፎቶግራፈር ኚየን ታንህ ኚህ የተነሳ ነው የሚል ከባድ ክስ አቅርቧል።
ዘጋቢ ፊልሙን ተከትሎም ዎርልድ ፕሬስ ፎቶ (WPP) በጉዳዩ ላይ ምርመራ የከፈተ ሲሆን፣ ከኡት የፎቶግራፍ ባለቤትነቱን ለመንጠቅ ወስኗል። ይህም በፎቶ ጋዜጠኞች ዘንድ ክፍፍል እንዲፈጠር አድርጓል።
"ጀግና የሆነውን አንጋፋ ፎቶግራፈር ሥራ ለመንጠቅ አሳማኝ ማስረጃ ያስፈልጋል" ሲል አንድ የፎቶ ጋዜጠኛ ለቢቢሲ ተናግሯል።
ጨምሮም "በዲጂታል ዘመን አንድ ምሥል እንዲህ ዓይነት ውዝግብ መፍጠሩ የተለመደ አይደለም። በመሆኑም ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልገናል። ውዝግቡ ይህንን ወሳኝ የሆነ ፎቶግራፍ ታሪክ እንዲያጠፋ አሊያም እርስ በርስ መቋሰል እንዲኖር መፍቀድ የለብንም" ብሏል።
የፎቶግራፉ ትክክለኛነት ጥያቄ ውስጥ የሚገባ አይደለም።
ሆኖም ፎቶግራፈሩም የታሪኩ አካል በመሆኑ ውዝግቡ ስሜታዊነትን እንደፈጠረ በሚሱሪ ዩኒቨርሲቲ የፎቶ ጋዜጠኝነት ተባባሪ ፕሮፌሰር የሆኑት ኬት ግሪንውድ ተናግረዋል።
"ጦርነቱ በራሱ ውስብስብ የሆነ ታሪክ ነው ያለው። አሁንም ድረስ ከባድ ስሜቶችን የሚፈጥር ነው፤ በመሆኑም ፎቶግራፉን ጥያቄ ውስጥ መክተት እነዚህን ስሜቶችም መንካት ነው የሚሆነው" ብለዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images/World Press Photo
'ናፓልም ገርል'
'ናፓልም ገርል' የሚል ስያሜ የተሰጠው ይህ ፎቶግራፍ የተነሳው እንደ አውሮፓውያኑ ሰኔ 8/1972 የደቡብ ቬትናም አየር ኃይል ትራንግ ባንግ መንደርን ከደበደበ በኋላ ነበር።
በፎቶው ላይ መነጋገሪያ የሆነችው ታዳጊዋ ኪም ፑክ በወቅቱ ከወንድሟ፣ ከአክስት እና ከአጎቷ ልጆች ጋር በአንድ ቤተ መቅደስ ግቢ ውስጥ እየተጫወቱ ነበር።
ያኔ ኡት ለአሶሺየትድ ፕሬስ ነበር የሚሠራው። እርሱ እንደሚለው ፍንዳታውን ተከትሎ የመንደሯ ነዋሪዎች በቅርብ ወዳለ አውራ ጎዳና እየሮጡ ነበር።
ኡት የሞተ ሕፃንን በእቅፋቸው ይዘው የነበሩ አያትን ፎቶግራፍ ካነሳ በኋላ ነበር ፑክ በአየር ላይ እጆቿን ዘርግታ ስትሮጥ የተመለከተው። ከዚያም ፎቶ ለማንሳት ወደ እርሷ ሮጠ። ፎቶግራፉንም አነሳ። በቃጠሎው የተላላጠ ቆዳዋን ቀርቦ እንደተመለከተም ወዲያው በሰውነቷ ላይ ውሃ ደፍቶባት ልጆቹን ይዞ ወደ ሆስፒታል ከነፈ።
ዲጂታል ካሜራዎች ከመፈልሰፋቸው በፊት ፎቶግራፈሮች ያነሷቸውን ፎቶዎች ፊልሞች ቢሮ ውስጥ ነበር የሚያስቀምጡት። ከዚያም የስቱዲዮ አርታኢው ፎቶዎቹን አውጥቶ ያደራጃል፤ የትኛው ፎቶ ወደ ዋና መሥሪያ ቤቱ መላክ እንዳለበትም ይወስናል።
"ወደ ቢሮ ስመለስ 'የሚገርም ልዩ የሆነ ፎቶ አለኝ ' ስል ጮህኩኝ። ሁሉም ፎቶውን ለመመልከት ዞሩ" ሲል የነበረውን ሁኔታ ጥር ወር ላይ ለቢቢሲ ተናግሯል።
ኡት እንደሚለው በወቅቱ ሥራ ላይ የነበሩት የፎቶ ስቱዲዮው አርታኢ ዩቺ ጃክሰን ኢሺዛኪ ነበሩ። ኢሺዛኪ ፊልሙን ሲያደራጁ ከጎናቸው ቆሞ ነበር። ኢሻኪዝ በፎቶው ላይ የኡትን ስም ፅፈው ምሥሉን ወደ ዋና ክፍሉ ይዘውት ሄዱ።
"ሁሉም ሰው ፎቶግራፉን ተመልክቶታል። የሆነ ሰው ግን አለቃዬን ሆርስት ፋስን ጠራና ከምሳ በአፋጣኝ እንዲመለስ ነገረው" ይላል ኡት።
ኡት እንደሚለው ከሆነ ፋስ ከፎቶ አርታኢው ካርል ሮቢንሰን ቀድመው ደርሰው ፎቶው ይላክ አይላክ በሚለው ላይ ሲከራከሩ ነበር።
በፎቶው ላይ መግለጫ (ካፕሽን) የመጻፍ ኃላፊነት ያለበት ሮቢንሰን፣ ርቃን ምሥል ስላለበት ፎቶውን መላክ ትክክለኛ አለመሆኑን በመግለጽ ውድቅ አደረገው።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ኡት ይህን ይበል እንጂ ሮቢንሰን ከዚህ የተለየ ሃሳብ ነው ለቢቢሲ ያጋራው። እርሱ እንደሚለው ከምሳ በኋላ በፎቶ ማጠቢያው ክፍል ያገኛቸው ፋስን ሳይሆን ኢሺዛኪን እና አንድ ቴክኒሽያንን ነበር።
እንደ ሮቢንሰን ከሆነ ፊልሙ መጀመሪያውኑ ተስተካክሎ ለግምገማ ወጥቶ ነበር። በተመሳሳይ ሁኔታ ላይ የተነሱ ሁለት ፎቶግራፎች ነበሩ። አንደኛው ከጎን በኩል ሌላኛው ከፊት ለፊት የተነሱ ናቸው። ሁለቱም በተለያዩ ፎቶግራፈሮች ነበር የቀረቡት።
ሮቢንሰን በፎቶ አንሺዎች ዝርዝር ውስጥ ያልተለመደ ስም ተመልክቷል። " የቬትናማውያን ፎቶግራፈሮች ሙሉ ዝርዝር ነበረን። እነዚህ ፎቶግራፈሮች ሲቪሊያን አሊያም አንዳንድ ጊዜ ተጨማሪ ገንዘብ ለማግኘት የሚሠሩ ወታደሮች ሊሆኑ ይችላሉ" ብሏል።
ሮቢንሰን፣ ፋስ ከተመለሱ በኋላ የትኛው ፎቶ መላክ እንዳለበትም አልተከራከሩም። ኡትም በፎቶ መረጣው ሂደት ላይ እንዳልነበረ ገልጿል።
ሮቢንሰን የፎቶውን መግለጫ ሲፅፍ ግን ፋስ ወደ እርሱ ቀረብ ብለው የፎቶውን ባለቤትነት ለአሶሺየትድ ፕሬስ (ኤፒ) ባልደረባ ኡት እንዲሰጥ በሹክሹክታ እንደነገሩት ገልጿል። "ከልጆቼ እና ከቬትናማዊቷ ባለቤቴ ጋር በሴጎን መቆየት ስለፈለኩ የመከራከር አቅሙ አልነበረኝም" ብሏል ሮቢንሰን።
ከዚያ በኋላ ፋስ እና ኢሺዛኪ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።
ሮቢንሰንም ፎቶግራፈሩን ይቅርታ መጠየቅ እንደሚፈልግ የገለጸ ቢሆንም ስሙን ግን አያስታውሰውም ነበር።
ከዚያ ግን እንደ አውሮፓውያኑ በ2015 በቀድሞ የኤፒ ባልደረባ አማካኝነት የኚህን ስም አገኘው። ሆኖም ኚህ የት እንደሚገኝ ማወቅ አልቻለም ነበር።
ከሰባት ዓመታት በኋላም ኡት እና ኪም የፎቶግራፉን 50ኛ ዓመት ለማክበር ከሮማው ካቶሊክ ሊቀጳጳስ ፖፕ ፍራንሲስ ጋር ተገናኙ።
"ከዚያም የሚመጣውን ሁሉ ለመጋፈጥ ወሰንኩ። መሸሽ አልቻልኩም" ይላል።
ሮቢንሰን፣ ጋሪይ ናይት የተባለ የፎቶ ጋዜጠኛ አግኝቶ 'ዘ ስትሪንገር' የተባለውን ዘጋቢ ፊልም አስመልክቶ ቃለመጠይቅ እንዲያደርግለት ተስማሙ።
በኋላ ላይ ሴያጎን ውድቀት በኋላ በስደተኝነት ወደ አሜሪካ ሄዶ የነበረውን እና በአውሮፓውያኑ በ2002 ወደ አገሩ የተመለሰውን ኚህን አገኙት።
"ዝም ጭጭ ነበር ያልኩት፣ ድምጽ አልባ ነበርኩ፣ በጭንቀት እና በሕመም ውስጥ ነበርኩ። ብዙ ጫና ባሳደሩብኝ ስሜቶች ውስጥ ነበርኩ" ብሏል ኚህ።
"ከእውነት በላይ ወሳኝ የሆነ ነገር የለም።"
ምርመራ
ዘጋቢ ፊልሙ እየተሠራ እንደሆነ ከታወቀ በኋላ ኤፒ ያሉትን ምሥሎች፣ በሕይወት ያሉ ምስክሮችን እና የኡት ካሜራን በመፈተሽ የራሱን ምርመራ ማካሄድ ጀመረ።
ጥር እና ግንቦት ወር ላይ ሁለት ዘገባዎችን ያወጣ ሲሆን፣ በዚህም የኡትን የፎቶ ባለቤትነት የሚያስነጥቅ ምንም እርግጠኛ ማስረጃ እንደሌለ ደምድሟል። ይሁንና የዜና ወኪሉ በምሥሉ ላይ ወሳኝ የሆነ ጥያቄ እንዳለው ገልጿል።
ኤፒ ፎቶግራፉ በፔንታክስ ካሜራ ሳይነሳ እንዳልቀረ ጠቁሟል። ይህም ኡት ተጠቀምኩት ካለው ካሜራ ጋር የሚቃረን ነው።
ኡት አራት ካሜራዎች እንዳሉት እና ሁለቱ ሌጅካስ ቀሪዎቹ ሁለቱ ደግሞ ኒኮንስ እንደሆኑ ነበር የገለጸው። በዚያን ወቅትም ምሥሉን ለማንሳት የተጠቀመው ሌካ የተባለውን ካሜራ እንደሆነ ገልጿል።
በኤፒ ሲጠየቅም ለካሜራው ሞዴል ብዙም ትኩረት አለመስጠቱን፤ ነገር ግን የምሥሉ ፊልም ሌካ ከተባለው ካሜራ የተገኘ እንደሆነ ፋስ እንደነገሩት አስረድቷል።
በዚያኑ ዕለት ደግሞ ጌህ ፔንታክስ የሚመስል ካሜራ በእጆቹ ይዞ ፎቶ ተነስቷል።
ዘጋቢ ፊልሙ እና ኤፒ በእጃቸው ያሉትን ምሥሎች፣ ፎቶግራፎች እና የሳተላይት ምሥሎችን በመጠቀም የጊዜ ቅደም ተከትልን በመመልከት የፎቶውን ባለቤት ለመለየት ሞክረዋል።
በዚህም ናፓልም ገርል ፎቶግራፍ ከተነሳ በኋላ የተቀረፁ ተንቀሳቃሽ ምሥሎች ውስጥ የሆነ የደበዘዘ ሰው ምሥል ይታያል። ይህ ምሥል የኡት እንደሆነ ይታመናል። ሆኖም ኡት ሕፃናቱ ካሉበት በርቀት ላይ ነው የነበረው።
ዘጋቢ ፊልሙ እንደሚለው ኡት ከቪዲዮ ካሜራው 60 ሜትር ርቀት ላይ እንደሚገኝ የገለጸ ሲሆን፣ ይህም ፎቶውን ካነሳ በኋላ የሚታይበት ቦታ ለማድረስ መሮጥ ይኖርበታል።
ኤፒ በበኩሉ ርቀቱ ከ28.8 እስከ 48 ሜትር ይደርሳል ሲልም የምሥሉ 28 በመቶ የሚሆነው የካሜራው ፍሬም ስህተት ነው ሲል ሞግቷል።
ከምርመራው ምን ተገኘ?
ኤፒም ሆነ ደብሊውፒፒ በፎቶግራፈሩ ማንነት ላይ እርግጠኛ አልሆኑም። እንዲያም ደብሊውፒፒ ሦስተኛ ፎቶግራፈር ፎቶውን አንስቶት ሊሆን እንደሚችል ጠቁሟል።
እስካሁን እነዚህ ጥያቄዎች መልስ አላገኙም። በወቅቱ የነበሩ በርካታ ጋዜጠኞች ዘጋቢ ፊልሙ ያቀረበውን እውነታ መሠረተ ቢስ ሲሉ ውድቅ ያደረጉት ሲሆን፣ በፊልሙ ላይ ለመሳተፍ ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል።
ጌህ አንዱን የታጠበ ፎቶግራፍ ፋስ እንደሰጡት ተናግረዋል። ሆኖም ባለቤታቸው በተናደደችበት ወቅት እንደቀደደችው ገልጿል።
ኡት በበኩሉ የፎቶው ባለመብት እንደሆነ የገለጸ ሲሆን፣ በስም ማጥፋት ክስ ለመክፈት እንዳቀደ ተናግሯል።
"ሰዎች ከፎቶው ጀርባ ስላለው እውነታ ማወቅ ይፈልጋሉ" ያለው ስሙ ያልተጠቀሰ ቬትናማዊ ፎቶግራፈር "ምን እንደተከሰተ ለማወቅ ተጨማሪ ጊዜ እና ማስረጃዎች ያስፈልጉናል" ብሏል።
ናፓልም ገርል የተሰኘው ፎቶግራፍ ለአስርተ ዓመታት ተፅዕኖ ፈጣሪ እንደሆነ ጥርጥር የለም። ሆኖም በታሪኩ ላይ የሚቀርቡ ክሶች ጥላ አጥልተውበታል።















