በመፈንቅለ መንግሥት ከሥልጣናቸው የወረዱት የኒጀሩ ፕሬዝደንት አሜሪካ እንድትረዳቸው ተማፀኑ

ሬዝደንት ሞሐመድ ባዙም

የፎቶው ባለመብት, AFP

በመፈንቅለ-መንግሥት ከሥልጣን የተወገዱት የኒጀር ፕሬዝዳንት አሜሪካ እና “ዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ” በሃገሪቱ “ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓት እንዲሰፍን” እርዳታ እንዲያደርጉ ጠየቁ።

ዋሺንግተን ፖስት በተሰኘው ጋዜጣ ሐሳባቸውን ያሰፈሩት ፕሬዝደንት ሞሐመድ ባዙም “በእገታ ሥር” ሆነው ይህን እንደፃፉ ገልጠዋል።

ፕሬዝደንት ባዙም ከሥልጣን ከተወገዱ በኋላ በምዕራብ አፍሪካዊቷ ሃገር አመፅ ተነስቷል።

ሐሙስ ዕለት በጉልበት ወደ ሥልጣን የመጡት ወታደሮች በፈረንሳይ፣ ዩናይትድ ስቴትስ፣ ናጄሪያ እና ቶጎ ያሉ የኒጀር አምባሰደሮችን እንደሚያሰናብቱ አስታውቀዋል።

በብሔራዊው ቴሌቪዥን ጣቢያ በሰጡት መግለጫ የአራቱ አምባሳደሮች የሥራ ፈቃድ “ከጥቅም ውጭ ሆኗል” ብለዋል።

ከሰዓታት በፊት በአሜሪካ የኒጀር አምባሳደር ኪያሪ ሊማን-ቲንጉሪ፤ ኤኤፍፒ ለተሰኘው የዜና ወኪል ጁንታው “ወደ ምክንታዊነት እንዲመጣ” እና “መሰል አፍሪካ ስኬታማ እንደማትሆን” ተናግረው ነበር።

ለኒውክሌር ኃይል እጅግ አስፈላጊ የሆነውን ዩራኒየም በስፋት የምታመርተው ኒጀር ከሰሜን አፍሪካ ወደ ሜድትራኒያን ለሚያቀኑ ስደተኞችም ወሳኝ መተላለፊያ ናት።

በጋዜጣ ሐሳባቸውን ያሰፈሩት የቀድሞው ፕሬዝደንት ባዙም መፈንቅለ-መንግሥቱ የሚሳካ ከሆነ “ለሃገራችን፣ ቀጣናችን እና ለመላው ዓለም” ከፍተኛ ኪሳራ ነው ብለዋል።

“የጋራ ለምንላቸው እንደ ዲሞክራሲና ሕግ ማክበር ላሉ እሴቶች መታገል ድኅነትና ሽብርተኝነትን ለመታገል ብቸኛ አማራጭ ናቸው” ሲሉ ፅፈዋል።

“የኒጀር ሕዝብ በዚህ ወሳኝ ሰዓት የምታደርጉትን እርዳታ በፍፁም አይዘነጋውም።” ብለዋል "በእገታ ስር" ሆነው መልዕክታቸውን ያስተላለፉት ፕሬዝደንት።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ባዙም አክለው የመፈንቅለ-መንግሥቱ መሪዎች ከሩሲያ ቅጥረኛ ቡድን ቫግነር ጋር ያለውን ግንኙነትም አንስተዋል።

“ጠቅላላው የሳህል ክልል በቫግነር ቡድን በኩል በሩሲያ ተፅዕኖ ሥር ሊወድቅ ይችላል። የሩሲያ ጨካሽ ሽብርተኝነትን በዩክሬን አይተነዋል” ይላል ፅሑፋቸው።

በኒጀር በርካታ የመንግሥት ግልበጣው ደጋፊዎች ሩሲያን የሚደግፉ መፈክሮችና የሩሲያን ሰንደቅ ይዘው ታይተዋል።

ሐሙስ ዕለት በርካታ ሰዎች ወደ ኒያሜይ አደባባይ ወጥተው ሰላማዊ ሰልፍ ያደረጉ ሲሆን መፈንቅለ-መንግሥቱን ደግፈው፤ ኒጀር ላይ ማዕቀብ የጣሉ የምዕራብ አፍሪካ ሃገራትን ኮንነዋል።

አሜሪካ እንደምትለው በፕሬዝደንት ባዙም መንግሥት ግልበጣ የሩሲያው ቫግነር ቡድን እጁ እንዳለበት የሚጠቁም ነገር የለም።

ነገር ግን የቫግነር ቡድን መሪ በኒጀር የተካሄደውን መፈንቅለ-መንግሥት ድል ነው ሲሉ ገልጠውታል።

የአውሮፓ ሕብረት፣ ዩናይትድ ስቴትስ እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መፈንቅለ-መንግሥቱን አጥብቀው ተቃውመውታል።

በያዝነው ሳምንት መባቻ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን ከፕሬዝደንት ባዙም ጋር በስልክ የተነጋገሩ ሲሆን ሃገራቸው በኒጀር በዲሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጠ መሪ እንዲኖር እርዳታ እንደምታደርግ ቃል ገብተዋል።

በዲሞክራሲያዊ መንገድ ተመርጠው ወደ ሥልጣን የመጡት ፕሬዝደንት ባዙም ባለፈው ሳምንት በገዛ ጠባቂዎቻቸው ነው በቁጥጥር ሥር የዋሉት።

የመፈንቅለ መንግሥቱ መሪ ጄኔራል አብዱራህማኔ ቺያኒ የሃገሪቱ መሪ ሆነው ተሹመዋል።

ኒጀር፤ በጂሃዲስቶች ኃይሎች በሚታመሰው የምዕራብ አፍሪካ ቀጣና ካሉ ሃገራት ከምዕራባዊያን ጋር በማበር ትታወቃለች።

ጎረቤቶቿ ቡርኪና ፋሶ እና ማሊ በተመሳሳይ በመፈንቅለ-መንግሥት ወደ ሥልጣን በመጡ መሪዎች ተገዝተዋል።