ግብፅ ከአፍሪካ ዋንጫ ውድድር ውጪ ሆነች

የግብጹ ግብ ጠባቂ የመለያ ምት ስቶ ዴሞክራቲ ኮንጎ ወደ ቀጣይ ዙር ማለፍ ችላለች።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የግብጹ ግብ ጠባቂ የመለያ ምት ስቶ ዴሞክራቲ ኮንጎ ወደ ቀጣይ ዙር ማለፍ ችላለች።

የሰባት ጊዜ የአፍሪካ ዋንጫ አሸናፊ የሆነችው ግብፅ በዲሞክራቲክ ኮንጎ ተሸንፋ ከአህጉራዊው የእግር ኳስ ውድድር ውጪ ሆነች።

በመለያ ምት ግብፅን በመርታት ከውድድሩ ውጪ ያደረገቻት ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እና ጊኒ ከምድባቸው ሩብ ፍጻሜውን መቀላቀላቸውን አረጋግጠዋል።

ግምት ያልተሰጣቸው ቡድኖች አስደናቂ ውጤት እያስመዘገቡ በሚገኙበት በአይቮሪ ኮስት እየተካሄደ ባለው የአፍሪካ ዋንጫ በኮንጎው እና በግብፅ ጨዋታ ላይ ሜሻክ ኤሊያ ዲሞክራቲክ ኮንጎን ቀዳሚ ማድርግ ችሎ ነበር።

የመጀመሪያው አጋማሻ መጠናቀቂያ ላይ ፈርኦኖቹ ያገኙትን የፍጹም ቅጣት ምት ሞስጠፋ ሞሐመድ አስቆጥሮ ሁለቱ ቡድኖች በአቻ ውጤት ወደ መልበሻ ክፍል አቅንተዋል።

ሁለተኛው አጋማሽም በተመሳሳይ ውጤት ተጠናቋል።

በአፍሪካ ዋንጫው ወደ ተጨማሪ ሰዓት ባቀናው በዚህ የመጀመሪያ ጨዋታ የግብፁ ሞሐመድ ሃምዲ ሁለተኛ ቢጫ ካርድ በመመልከቱ በቀይ ካርድ ከሜዳ ተወግዷል።

ጨዋታው በአቻ ውጤት በመጠናቀቁም ሁለቱ ቡድኖች ወደ መለያ መለያ ምት አቅንተዋል።

በመለያ ምቱ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ 8 ለ 7 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችላለች።

አምበሏን ሞሐመድ ሳላህን በጉዳት ያጣችው ግብፅ በዘንድሮው አፍሪካ ዋንጫ አንድም ጨዋታ ማሸነፍ አልቻለችም።

ግብፅ ባለፈው የአፍሪካ ዋንጫ ለፍጻሜ ደርሳ በሴኔጋል መሸነፏ ይታወሳል።

ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎም በተመሳሳይ መልኩ ወደ ጥሎ ማለፉ የደረሰችው ሦስቱንም የምድብ ጨዋታዎች አቻ በመለያየት ነው።

በዚህም ምክንያት ይመስላል ሁለቱ ቡድኖች በመደበኛው ሰዓት አቻ መለያታቸው ብዙዎችን ያላስገረመው።

በሌላኛው የጥሎ ማለፍ ጨዋታ ደግሞ ጊኒ ሩብ ፍጻሜ የደረሰችበትን ውጤት አስመዝግባለች።

ኢኳቶሪያል ጊኒን 1 ለ 0 በማሸነፍ ነው ጊኒ ለሩብ ፍጻሜ የደረሰችው።

ጨዋታው በመጀመሪያው አጋማሽ ያለምንም ጎል ተጠናቋል።

የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ተጫዋቾች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ተጫዋቾች

ሁለተኛው አጋማሽ ከተጀመረ ከአስር ደቂቃ በኋላ ፌደሪኮ ቢኮሮ በፈጸመው ጥፋት በቀይ ካርድ ከሜዳ ተሰናብቷል።

በኋላ ላይ ኢኳቶሪያል ጊኒ ፍጹም ቅጣት ምት ብታገኝም አምበሉ ኤሚሊዮ ንሱዬ ሳይጠቀምበት ቀርቷል።

አጥቂው የአፍሪካ ዋንጫው ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪነትን በአምስት ጎሎች እየመራ ይገኝ ነበር።

ጨዋታው ያለምንም ጎል ወደ ተጨማሪ ሰዓት ሊያመራ ነው ተብሎ ሲጠበቅ የጊኒው አጥቂ ሞሐመድ ባዮ የአሸናፊቷን ኳስ ከመረብ ላይ አሳርፏል።

በሩብ ፍጻሜው የፊታችን አርብ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ከጊኒ የሚገናኙ ይሆናል።

የአፍሪካ ዋንጫ የጥሎ ማለፍ ጨዋታዎች ዛሬ ሰኞ ምሽትም ቀጥለው ይከናወናሉ።

በዚህም ምሽት 2፡00 ሰዓት ላይ ኬፕ ቨርዴ እና ሞሪታንያ ይጋጠማሉ።

አስተናጋጇ እና በአጣብቂኝ ጥሎ ማለፉን የተቀላቀለችው አይቮሪ ኮስት ለዋንጫው ቅድሚያ ግምት ካገኘችው ሴኔጋል ጋር ምሽት 5፡00 ሰዓት ይጫወታሉ።