ደቡብ አፍሪካ ለሃይማኖት ሠራተኞች የሥራ ፈቃድ መስጠት አቆመች

ሼፐርድ ቡሽሪ እና ባለቤታቸው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ደቡብ አፍሪካ በተለያዩ የሃይማኖት ሥራዎች ላይ ለሚሰማሩ የውጪ ዜጎች ስትሰጥ የቆየችውን የሥራ እና ቋሚ የመኖሪያ ፈቃድ መስጠት ማቆሟን የአገር ውስጥ ሚኒስቴር አስታወቀ።

ሚኒስትሩ አሮን ሞቶሳሌዲ አወዛጋቢውን ማላዊውን ሼፐርድ ቡሺሪ እና ባለቤቱ ጉዳይን በተመለከተ ምርመራ በሚያከናውነው የፓርላማ ኮሚቴ ፊት ቀርበው እአአ በ2020 በሕገ-ወጥ መልኩ የተገኘ ገንዘብን ሕጋዊ አስመስሎ የማቅረብ ክስ እያለባቸው እንዴት ከአገር ሊወጡ እንደቻሉ አብራርተዋል።

ቡሺሪ የደቡብ አፍሪካ የመኖሪያ ፍቃድ እንዲያገኙ ረድታችኋል በሚል አንድ ከፍተኛ የደቡብ አፍሪካ የአገር ውስጥ ጉዳይ ባለስልጣን እና አራት የተቋሙ ሠራተኞች ከስራ ታግደዋል።

ደቡብ አፍሪካ ቡሺሪ ወደ ማላዊ ማምለጡን ተከትሎም ማላዊ አሳልፋ እንድትሰጣት ጥያቄዋን በይፋ አቅርባለች።

"እኛ ባለን የሰዎች የዝውውር ቁጥጥር ስርዓታችን ውስጥ ቡሽሪ እና ባለቤታቸው ከአገር መውጣታቸውን የሚያሳይ ምንም አይነት ማስረጃ እንደማያሳይ ማረጋገጥ እፈልጋለሁ። ይህ ማለት ግለሰቦቹ አገሪቱን ለቀው የወጡት በሕገ-ወጥ መንገድ ነበር ማለት ነው" ሲሉ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚስትሩ ሞቶሳሌዲ ተናግረዋል።

ሚኒስትሩ አክለውም በአስገድዶ መድፈር እና በሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ክስ የቀረበበት ሌላኛው ናይጄሪያዊ ወንጌላዊ ቲሞቲ ኦሞትሶ እንዴት የደቡብ አፍሪካን የመኖሪያ ፍቃድ እንዳገኘ ለማወቅ ምርመራ መጀመሩን ተናግረዋል።

"እኛ እያልን ያለነው ግለሰቦቹ እንደ ጎብኚዎች ብቻ መምጣት አለባቸው ነው። ነገር ግን እንደ ጎብኚ መጥተው ሥራ መሥራት ይችላሉ። ይህ ለውጥ እነዚህ የሃይማኖት ሰራተኞች ቋሚ ነዋሪ የሚሆኑበት ምንም መንገድ የለም ማለት ነው” ሲሉ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።