ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የአሜሪካ ኢሚግሬሽን በመቶዎች የሚቆጠሩ ደቡብ ኮሪያውያንን በሃዩንዳይ ፋብሪካ በቁጥጥር ስር አዋለ
የአሜሪካ ኢሚግሬሽን እና ጉምሩክ ባለሥልጣን (አይስ) በጆርጂያ ግዛት በሚገኘው የሃየዩንዳይ መኪና ማምረቻ ባደረገው ወረራ ቢያንስ 500 ሰዎችን በቁጥጥር ስር አዋለ።
በዚህም የታሰሩት አብዛኛዎቹ የደቡብ ኮሪያ ዜጎች እንደሆኑ ተገልጿል።
የኮሪያው የመኪና አምራች ሃዩንዳይ ይህንን 1214 ሄክታር ስፋት ያለው ስፍራ የገነባው የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ለማምረት ሲሆን ለአንድ ዓመት ያህልም አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል።
በፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሁለተኛው የስልጣን ዘመን በስራ ቦታ ላይ የተፈጸመ ከፍተኛው እስር እንደሆነ ተነግሯል።
ደቡብ ኮሪያ ይህ የኢሚግሬሽን ባለስልጣኑ ድርጊት "እንዳሳሰባት እና እንዳሳዘናት" ገልጻ የአሜሪካ መንግሥት የዜጎቹን መብት እንዲያከብር አሳስባለች።
የሃገር ውስጥ ደህንንት ዲፓርትመንት ለቢቢሲ እንደገለጸው ወኪሎቹ በፋብሪካው ፍተሻ ያደረጉት "ህጋዊ ያልሆነ የቅጥር አሰራር እና ሌሎች ከባድ የፌደራል ወንጀሎች ይፈጸማሉ" የሚሉ ክሶችን ተከትሎ ነው።
በአትላንታ የሃገር ውስጥ ደህንነት ምርመራ ልዩ ወኪል የሆኑት ስቲቭ ሸራንክ "ለወራት የወንጀል ምርመራ አካሂደን ማስረጃዎችን እና ሰነዶችን ሰብስበናል እንዲሁም ቃለ መጠይቆችን አድርገናል። ያሉንን ማስረጃዎች በሙሉ አቅርበን የፍርድ ቤት የፍተሻ ማዘዣ አግኝተን ነው ይህንን ያከናወንነው" ሲሉ አርብ ዕለት ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
ስቲቭ ሽራንክ በተቋሙ የምርመራ ታሪክ ውስጥ በአንድ ስፍራ የተፈጸመ ትልቁ ኦፕሬሸን እንደሆነም አክለዋል።
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በአሜሪካ ውስጥ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ግንባታዎችን ማስፋፋት ከሚለው ፖሊሲያቸው ጋር ተያይዞ ይህ እስር ለውጥረት በር የሚከፍት ሆኗል።
አሜሪካ ዋና አጋሬ ከምትላት ደቡብ ኮሪያ ጋር ያላትን ግንኙነት ሊያሻክር ይችላል።
ትራምፕ ሰነድ አልባ ስደተኞችን ከአገራቸው ለማስወጣት ከምርጫ ዘመቻቸው ጀምሮ ሲናገሩት የቆየ ነው።
ፕሬዚዳንት ትራምፕ በመኪና ማምረቻ ስፍራው "ህገወጥ የውጭ ዜጎች ነበሩ፤ የአሜሪካ ኢሚግሬሽን ባለስልጣናት ስራቸውን እየሰሩ ነበር" ሲሉ አርብ ዕለት ተናግረዋል።
ከደቡብ ኮሪያ የተሰጠውን ምላሽ አስመልክቶ ከአንድ ጋዜጠኛ ለቀረበላቸው ጥያቄ ትራምፕ ሲመልሱ "ከሌሎች አገራት ጋር ተስማምተን መኖር እንፈልጋለን፤ ጥሩና የተረጋጋ የሰው ኃይል እንዲኖረን እንፈልጋለን" ብለዋል።
ሆኖም "እኔ እንደተረዳሁት በርካታ ህገወጥ ስደተኞች አሉ፤ አንዳንዶቹ የማይረባ ስብዕና ያላቸው ናቸው። በርካታ የውጭ ሃገር ዜጎች በዚህ ፋብሪካ በስራ ላይ ተሰማርተዋል" ሲሉም ተናግረዋል።
"እነዚህ ሰራተኞች በባይደን የስልጣን ዘመን የመጡ ናቸው። በህገወጥ መንገድ ነው የመጡት" ሲሉ አክለዋል።
በዚህ የፋብሪካው ወረራ በህገወጥ መንገድ ወደ አገሪቱ የገቡ ወይም በህገወጥ መንገድ ሲሰሩ የነበሩ 475 ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የኢሚግሬሽን ባለስልጣናት አስታውቀዋል።
ግለሰቦቹ በጆርጆያ በሚገኘው የአሜሪካ ኢሚግሬሽን እና ጉምሩክ ባለሥልጣን (አይስ) ማዕከል ውስጥ ታስረው ይገኛሉ።
ከነዚህ ውስጥ 300 የሚሆኑት የኮሪያ ዜጎች መሆናቸው ተገልጿል።
ሃዩንዳይ ሞተር ኩባንያ "ሁኔታውን በቅርበት እየተከታተለ እና ሁኔታዎችን ለመረዳት እየሰራ መሆኑን" ባወጣው መግለጫ አትቷል።
አክሎም "ከታስሩት መካከል አንዳቸውም በሃዩንዳይ በቀጥታ ተቀጥረው እንደማይሰሩ ተረድተናል" ሲል አክሏል።
የሃዩንዳይ የኤሌክትሪክ ተሽካርካሪዎች የማምረት ስራ አለመስተጓጎሉን ሮይተርስ ዘግቧል።
ሆኖም አጋሩና ባትሪዎችን የሚያመርተው የደቡብ ኮሪያ ኤልጂ ኤነርጂ ሶሉሽንስ ስራውን ማቆሙ ተገልጿል።