ብሊንከን ከቻይናው አቻቸው ጋር ‘ግልጽነት የተሞላበት’ ንግግር አድርገዋል ተባለ

የቻይና እና የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚንስትሮች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ አንቶኒ ብሊንከን ከቻይናው አቻቸው ጋር ‘ግልጽነት የተሞላበት’ ንግግር አድርገዋል አለ።

አንቶኒ ብሊንከን ከቻይናው አቻቸው ጋር በነበራቸው ውይይት ዲፕሎማሲዊ ግንኙነትን ስለማስቀጠል እና የግንኙነት መስመሮች ከፍት መሆን እንዳለባቸው አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል ብሏል የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አንቶኒ ብሊንከን ከቻይና ባለስልጣናት ጋር ለሁለት ቀናት የሚዘልቅ ንግግር ለማድረግ ትናንት ቤይጂንግ መግባታቸው ይታወሳል። ይህ የብሊንከን ጉዞ የአሜሪካ ዲፕሎማት ወደ ቻይና ሲጓዝ ከአምስት ዓመታት ወዲህ የመጀመሪያው ያደርገዋል።

ብሊንከን ይህን ጉዞ ለማድረግ አቅደው የነበረው ከአምስት ወራት በፊት የነበረ ቢሆንም ሰላይ ነች የተባለች ግዙፉ የቻይና ፊኛ አሜሪካ ሰማይ ላይ ከታየች በኋላ ጉዟቸውን መሰረዛቸው ይታወሳል።

የአሜሪካ ባለስልጣናት ከብሊንከን ጉዞ በፊት ዋነኛው የብሊንከን የጉዞ ዓላማ እጅግ ውጥረት ያየለበትን የአሜሪካ-ቻይና ግንኙነት ማረጋገት ነው ብለው ነበር።

የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ኪን ጋንግ አገራቸው ከአሜሪካ ጋር የተረጋጋ እና ገንቢ የሆነ ግንኙነት ለመፍጠር ፍላጎት አላት ብለው ስለመናገራቸው የቻይና ብሔራዊ ጣቢያ ዘግቧል።

ሁለቱ የውጭ ጉዳይ ሚንስትሮች ውይይት ካድረጉ በኋላ የቻይናው የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ለጉብኝት ወደ ዋሽንግተን ዲሲ ለመምጣት ተስማምተዋል።

ብሊንከን በጉብኝታቸው እንደ አጀንዳ ከያዙት መካከል አንዱ የታይዋን ጉዳይ ስለመሆኑ ተመላክቷል።

ቻይና ታይዋን አንድ የራሴ ግዛት አካል ነች የምትል ሲሆን አስፈላጊ ከሆነም በኃይል ጠቅልዬ እወስዳታለሁ ትላለች።

በሌላ በኩል የራሷ የሆነ ሕገ-መንግሥት ያላት፣ በዲሞክራሲያዊ ምርጫ የተመረጡ መሪዎች እና ከ300 ሺህ ያላነሰ የጦር ሠራዊት ባለቤት ከሆነችው ታይዋን እራሷን እንደ ሉዓላዊ ግዛት የምትቆጥር ሲሆን የአሜሪካም ጠንካራ ድጋፍ አላት።

ከወራት በፊት ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ታይዋን ከቻይና ጥቃት ቢሰነዘርባት ታይዋንን ትከላከላለች ብለው ነበር።

በሁለቱ የውጭ ጉዳይ ሚንስትሮች ስብሰባ ላይ የቻይናው የውጭ ጉዳይ ሚንስትር በሁለቱ አገራት ግንኙነት ታይዋን ‘ዋነኛ አደጋ ነች’ ካሉ በኋላ ‘የታይዋን ጉዳይ የቻይና ፍላጎት ውስጥ መሠረታዊ ነው’ ስለማለታቸው ብሔራዊው ጣቢያ ጨምሮ ዘግቧል።

በዩክሬን እየተካሄደ ስላለው ጦርነት፣ የኮምፒዩተር ቴክኖሎጂ ውጤቶች ንግድ አለመግባባት፣ በአሜሪካ የፌንታሊን እጽ መስፋፋት እንዲሁም የቻይና የሰብዓዊ መብት አያያዝ ብሊንከን ከቻይና ባለስልጣናት ጋር ሊነጋገሩባቸው የሚችሉት ጉዳዮች ናቸው።

ብሊንከን ከፕሬዝዳንት ዢ ዢንፒንግ ጋር ስለመገናኘታቸው የተባለ ነገር የለም።

ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን እአአ 2021 መጀመሪያ ላይ ስልጣን ከተረከቡ በኋላ ብሊንከን ቻይናን የጎበኙ ትልቁ የአሜሪካ ባለስልጣን ሆነዋል።