ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በማላዊ ነውረኛ ቪዲዮዎችን መቅረጹን ቢቢሲ ያጋለጠው ቻይናዊ ጥፋተኛ ተባለ
ቢቢሲ በምርመራ ጋዜጠኝነት ማላዊ ውስጥ ሲፈጽም የነበረውን ድርጊት ያጋለጠበት ቻይናዊ በአገሪቱ ፍርድ ቤት ጥፋተኛ ተብሏል።
ይህንን ግለሰብ የማላዊ ፍርድ ቤት በሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር፣ ሕጻናትን አታልሎ ያልተገባ ነገር በማስፈጸምና በሌሎች ብዙ ክሶች ነው ጥፋተኛ ያለው።
ሉ ኬ ወይም በሌላኛው ስሙ ሱሱ በመባል የሚጠራው ቻይናዊው፣ ቢቢሲ የሰራውን የምርመራ ዘገባ ተከትሎ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ቆይቷል።
ፍርድ ቤት ጉዳዩን ከመረመረ በኋላ በአጠቃላይ የ12 ወራት እስራት በይኖበታል።
ነገር ግን ያለፈውን አንድ ዓመት በእስር ያሳለፈ በመሆኑ በአሁኑ ወቅት አገሪቱን በሰባት ቀናት ውስጥ ለቆ እንዲወጣና ድጋሚ ወደ ማላዊ እንዳይመለስ ተወስኖበታል።
በምርመራ ዘገባው ይህ ግለሰብ የማላዊ ሕጻናትን በቪዲዮ እየቀረጸ ለግለሰቦች ሰላምታ እንዲያስተላልፉ ያደረገ ሲሆን፣ ከሰላምታ መልዕክቶቹ አንዳንዶቹ ዘረኝነትን የሚያጎሉ እና አጸያፊዎች ነበሩ።
ቪዲዮዎቹ በቻይና የማኅበራዊ ሚዲያዎች እስከ 70 የአሜሪካን ዶላር ይሸጡ ነበር።
ቪዲዮዎቹ በሕዝብ ዘንድ ደርሰው መነጋገሪያ መሆን ሲጀምሩ የማላዊ መንግሥት የእስር ትዕዛዝ አወጣበት። ሉ ኬ ግን በፍጥነት ወደ ጎረቤት አገር ዛምቢያ ተሻገረ።
ነገር ግን ዛምቢያም ቢሆን በሕገ ወጥ መንገድ በመግባቱ በፖሊስ ተይዞ ለማላዊ ተላልፎ ተሰጠ።
ትናንት ፍርድ እስኪወስንበት ድረስ የዋስትና መብቱ ተከልክሎ በእስራት ቆይቷል።
በህጻናት ዝውውር፣ ኢንተርኔትን በሕገ ወጥ መልኩ በመጠቀም፣ ማኅበራዊ ሚዲያን ለመጥፎ ነገር በማዋል እና በአጠቃላይ በ14 ወንጀሎች ላይ ነው ክስ የተመሰረተበት።
ሉ ኬ ግን ወንጀሎቹን መፈጸሙን አስተባብሏል።
በእሱ ቪዲዮ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎችን ለመካስም 16 ሺህ የአሜሪካን ዶላር ለማላዊ መንግሥት መክፈሉን ገልጿል።
ቪዲዮዎቹን የቀረጻቸው የቻይናን ባሕል ወደ ማላዊ ለማምጣት በማስብ መሆኑን ለፍርድ ቤቱ ተናግሯል።