‘ባለስልጣናቱ ሽልማቱን ውድቅ እንዳደርግ ጠየቁኝ’- ሩሲያዊው የኖቤል ተሸላሚ

የዘንድሮው የኖቤል የሰላም ሽልማት አሸናፊ ሩሲያው ያን ራቺንስኪ የሃገሩ ባለስልጣናት ሽልማቱን ውድቅ እንዲያደርገው እንደመከሯቸው ተናገሩ።

ሜሞሪያል የተባለ ጭቆናን የሚቃወም ድርጅት የሚመሩት ያን ራቺንስኪ ባለስልጣቱ ሽልማቱን እንዳይቀበሉ የጠየቋቸው ከሳቸው ጋር ሽልማቱን የሚጋሩት የዩክሬንና የቤላሩስ ተሸላሚዎች በሩስያ “አግባብነትና ተቀባይነት” ስለሌላቸው መሆኑን ጠቅሰውላቸዋል።

ከሩሲያዊው ያን በተጨማሪ ዩክሬናዊ የሰብዓዊ ተሟጋች ‘ሴንተር ፎር ሲቪል ሊበርቲስ’አ እንዲሁም በእስር ላይ የሚገኝ ቤላሩሳዊ የመብት ተሟጋች አሌስ ቢያሊያትስኪ ይገኙበታል።

ሜሞሮያል ዕድሜ ጠገብ ከሆኑ የሩሲያ የሲቪል መብት ተቆርቋሪ ቡድኖች አንዱ ሲሆን ባለፈው ዓመትም በመንግሥት ተዘግቷል።

የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቢቢሲ ምላሽ እንዲሰጠው ጠይቆ ነበር።

ያን ራቺንስኪ ከቢቢሲ ሃርድቶክ ፕሮግራም ጋር ባደረጉበት ቆይታ ድርጅታቸው ሽልማቱን እንዳይቀበልና ውድቅ እንዲያደርግ ከባለስልጣናቱ ምክር ቢሰጣቸውም “ሃሳባቸውን ችላ ብለነዋል” ሲሉም ተናግረዋል።

ምንም እንኳን ደህንነታቸው ላይ ስጋት ቢጋረጥም ሜሞሪያል የሚያከናውነው ተግባር አስፈላጊ እንደሆነ ተናግረዋል።

"በዛሬዋ ሩሲያ የማንም ሰው የግል ደህንነት ሊረጋገጥ አይችልም" የሚሉት ራቺንስኪ አክለውም "ልክ ነው፣ ብዙዎች ተገድለዋል፣ ነገር ግን የመንግሥት እርምጃ ወደ የት እንደሚያመራ እናውቃለን… በሆነ መንገድ ከዚህ ልንወጣ ይገባል” ብለዋል።

ሜሞሪያል የሶቪየት ህብረት ከነበረችበት ጀምሮ የነበረውን ጭቆናን መዝግቦ የያዘ ታሪካዊ ተቋም ነው።

የተቋሙ የመጀመሪያው ሊቀመንበር አርሴኒ ሮጊንስኪ “ጸረ- ኮሚዩኒስት” የሆኑ ግለሰቦች በግዞት እስር ለሚዳረጉበት የሶቪየት የጉልበት ስራ ካምፕ እንዲገባ በማድረግ ተቀጥቷል።

የኖቤል ኮሚቴ ሽልማቱን ባበሰረበት ወቅት ሜሞሪያል “የቀድሞ ወንጀሎችን መጋፈጥ አዳዲሶችን ለመከላከል አስፈላጊ ነው” በሚለው እሳቤ ላይ የተመሰረተ መሆኑን ገልጿል።

ራቺንስኪ የኖቤል ኮሚቴው ሽልማቱን ለሦስት የተለያዩ ሀገራት ተሸላሚዎች ለመስጠት ያሳለፈውን ውሳኔ “አስደናቂ” ሲሉ ጠርተውታል።

“ ሲቪል ማህበራት በአገራት ወሰን ሳይከፋፈሉ የጋራ ችግሮችን ለመፍታት የሚሰሩ በአንድ የሚቆሙ ለመሆናቸው ማረጋገጫ ነው” ብለዋል።

ነገር ግን ሩሲያዊ ተሸላሚን የማካተቱ ውሳኔ አከራካሪና አወዛጋቢ ሆኗል።

የዩክሬን የሲቪል ነጻነቶች ማዕከልን የምትመራውና ሌላኛው የሽልማት አሸናፊ ከራቺንስኪ ጋር በአንድነት ቃለ መጠይቅ ለማድረግ ፈቃደኛ አልነበረችም። ቢቢሲም በተናጠል ነው ቃለ መጠይቅ ያደረገላቸው።

ኦሌክሳንድራ ማትቪቹክ ለምን ለየብቻ ቃለ ምልልሱን ማድረግ እንደፈለገች ስትጠየቅ “በአሁኑ ወቅት ጦርነት ላይ ነን እናም የዩክሬን የሰብአዊ መብት ተሟጋቾችን ድምፅ ከፍ ብሎ እንዲሰማ አንፈልጋለን” በማለት ምላሽ ሰጥታለች።

“ሞንም እንኳን ለየብቻ ቃለ መጠይቅ ብናደርግም ተመሳሳይ መልዕክቶችን እንደምናስተላልፍ እርግጠኛ ነኝ።" ብላለች።