በቱርክ ተቃዋሚዎች በኢስታንቡል ጎዳና ትልቅ የተቃውሞ ሰልፍ አካሄዱ

በኢስታንቡል የተካሄደው የተቃውሞ ሰልፍ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ የዲሞክራሲ ደጋፊ ሠልፈኞች ወደ ቱርክ ኢስታንቡል ጎዳና በመመለስ ለታሰሩት የከተማዋ ከንቲባ ያላቸውን ድጋፍ አሳይተዋል።

የፕሬዚዳንት ሬሲፕ ጣይብ ኤርዶዋን ዋነኛ ተቀናቃኝ ሆነው የሚታዩት ኤክሬም ኢማሞግሉ ባለፈው ሳምንት በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር መዋላቸው ከፍተኛ ተቃውሞ አስነስቷል።

ኢማሞግሉ ክሱን አስተባብለው የታሰሩት ከፖለቲካ ጋር በተያያዘ መሆኑን ተናግረዋል።

ቅዳሜ ለተቃውሞ የወጣው ሕዝብ በጣም ብዙ ስለነበር ተቃውሞው ከተካሄደበት አቅራቢያ የሚገኙ ፓርኮችንም ተጠቅመዋል።

የኢማሞግሉ ሪፐብሊካን ፓርቲ (ሲኤችፒ) ሊቀመንበሩ ለብቻቸው ከታሰሩበት የጻፉትን ደብዳቤ ለሰላማዊ ሰልፈኞቹ አንብበዋል።

ኢማሞግሉ በደብዳቤው ላይ "እኔ ምንም አልፈራም። እናንተ ከጎኔ ናችሁ። ሕዝቡ አንድ ስለሆነ እኔ ምንም ስጋት የለብኝም። ሕዝቡ በጨቋኝ ላይ አንድ ሆኗል" ብለዋል።

ሚስታቸው ዲሌክም በተቃውሞው ሰልፍ ላይ ተገኝተው ለሕዝቡ "መታገል እና መፋለም እንቀጥላለን" ሲሉ ተናግረዋል።

ተቃዋሚዎች የቱርክን ቀይ እና ነጭ ባንዲራ በማውለብለብ "መብት፣ ሕግና ፍትህ!" ሲሉ ተደምጠዋል።

ኢማሞግሉ ከ2019 ጀምሮ የኢስታንቡል ከንቲባ ሆነው ሲያገለግሉ የቆዩ ሲሆን ባለፈው ዓመት በተካሄደው የከንቲባ ምርጫ አስደናቂ ድል አግኝተዋል።

እአአ በ 2028 ለሚካሄደው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ የሲኤችፒ ዕጩ ሆነው የተሾሙ ሲሆን በምርጫው የኤርዶዋንን የፍትህ እና ልማት ፓርቲን መፎካከር የሚችሉ ብቸኛ ፖለቲከኛ ተደርገው ተወስደዋል።

ኤርዶዋን ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ በስልጣን ላይ ቆይተዋል። በመጀመሪያ በጠቅላይ ሚኒስትርነት ከዚያም ከ2014 ጀምሮ በፕሬዚዳንትነት አገልግለዋል።

የቱርክን ሕገ መንግሥት እስካልቀየሩ ድረስ ከ2028 በኋላ ለፕሬዚዳንትነት መወዳደር አይችሉም።

ኢማሞግሉ ከሳምንት በፊት ከታሰሩ በኋላ ተከታታይ ሕዝባዊ ተቃውሞዎች አገሪቱ አስተናግዳለች።

የቅዳሜው ሰልፍ ሰላማዊ ቢሆንም፣ አንዳንድ ቀደም ሲል የተካሄዱ ተቃውሞዎች ፖሊስ አስለቃሽ ጭስ እና የፕላስቲክ ጥይት እስከመጠቀም ደርሷል።

ተቃውሞውን ሲዘግቡ የነበሩ ጋዜጠኞችን ጨምሮ ሁለት ሺህ የሚጠጉ ሰዎች ታስረዋል።

ይህም ትክክለኛ የፕሬስ ፈቃድ እንደሌለው ከተነገረ በኋላ የተባረረውን የቢቢሲ ዘጋቢ ማርክ ሎወንን ይጨምራል።

ኤርዶዋን የተቃውሞ ሰልፎቹን "የጎዳና ላይ ሽብርተኝነት" ነው ከማለት ባለፈ ሰልፈኞች በፖሊስ ላይ ጥቃት ፈጽመዋል፤ በሕዝብ ንብረት ላይም ጉዳት አድርሰዋል ሲሉ ከስሰዋል።

ኢማሞግሉ ጉዳያቸው በፍርድ ቤት ሲታይ ነፃ እና ፍትሃዊ የፍርድ ሂደት አይገጥማቸውም የሚል ስጋት አለ።

የኢማሞግሉ በቁጥጥር ስር የዋለው በፖለቲካዊ ምክንያት መሆኑን ውድቅ ያደረገው መንግሥት፤ የቱርክ ፍርድ ቤቶች ሙሉ በሙሉ ነፃ መሆናቸውን አስታውቋል።