ትራምፕ ትችት ከተነሳበት የቢቢሲ ዘጋቢ ፊልም ጋር በተያያዘ ተቋሙ ላይ የአንድ ቢሊዮን ዶላር ክስ ለመመሥረት ዛቱ

የፎቶው ባለመብት, Reuters / AFP via Getty Images
ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ፤ ንግግራቸውን ቆርጦ ያቀረበበት መንገድ ትችት ያስነሳውን ዘጋቢ ፊልም በተመለከተ ቢቢሲ ላይ ሕጋዊ እርምጃ ለመውሰድ ዛቱ።
የፕሬዝዳንቱ የሕግ አማካሪ ቡድን፤ ቢቢሲ ዘጋቢ ፊልሙን "ሙሉ በሙሉ እና ፍትሐዊ በሆነ መልኩ እንዲያወርድ" እስከ አርብ ሕዳር 5/2018 ዓ.ም. ድረስ ቀነ ገደብ ሰጥተዋል። ይህ የማይፈጸም ከሆነም የአንድ ቢሊዮን ዶላር ክስ እንደሚመሠርቱ አስጠንቅቀዋል።
ሾልኮ የወጣ የቢቢሲ የውስጥ ማስታወሻ፤ መገናኛ ብዙኃኑ ትራምፕ ከአምስት ዓመት ገደማ በፊት ምርጫ በተሸነፉበት ወቅት በአንድ መድረክ ላይ በተለያዩ ደቂቃዎች ያደረጓቸውን ሁለት ንግግሮች አንድ ላይ ማቅረቡን አሳይቷል። ይህ መደረጉም ትራምፕ ሰዎች የአገሪቱ ኮንግረስ የሚገኝበትን ካፒቶል ሂል እንዲያጠቁ በግልጽ ያነሳሱ እንዳስመሰለም ተገልጿል።
ይህ ጉዳይ ሾልኮ መውጣቱን ተከትሎ ከኃላፊነት ከለቀቁ አመራሮች አንዱ የሆኑት የቢቢሲ ኒውስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዴብራህ ተርነስ መገናኛ ብዙኃኑ "ተቋማዊ መልድዎ" የለበትም ሲሉ ተከላክለዋል። የቢቢሲ ዋና ዳይሬክተር ቲም ዴቪም ከዚሁ ጋር በተያያዘ ኃላፊነታቸውን ለቅቀዋል።
ሁለቱ አመራሮች እሑድ ዕለት እንደሚለቅቁ ያስታወቁት የእንግሊዙ ዘ ቴሌግራፍ ጋዜጣ ሾልኮ የወጣ የቢቢሲ የውስጥ ማስታወሻን በማጣቀስ ያወጣውን ዘገባ ተከትሎ ጫና ከተፈጠረባቸው በኋላ ነው። ማስታወሻው የቢቢሲ ኤዲቶሪያል ስታንዳርድ ኮሚቴ ገለልተኛ የውጭ አማካሪ በነበረው ማይክል ፔስኮት የተዘጋጀ ነው።
የቀድሞው አማካሪ ማስታወሻ፤ የጋዛ ዘገባዎችን በተመለከተ እንዲሁም ጸረ ትራምፕ እና ጸረ እስራኤል ናቸው ያላቸውን ጉዳዮች በመጥቀስ ቢቢሲን በአድሏዊነት ይከስሳል።
ወደ አንድ ወገን ያደላ የፆታ ቅየራ አዘጋገብ እና ሌሎች "የሚረብሹ ጉዳዮችም" ተጠቅሰዋል። በቢቢሲ ፓናሮማ ፕሮግራም ዘጋቢ ፊልም ላይ የተደረገው የአርትኦት ጉዳይንም አንስቷል።
የቢቢሲ ቦርድ ሊቀ መንበር ሳሚር ሻህ የዘጋቢ ፊልሙ ዝግጅት ላይ "የውሳኔ አሰጣጥ ስህተት" መፈጸሙን አምነዋል። የትራምፕ ንግግር አርትኦት የተደረገበት መንገድም "እርምጃ እንዲወሰድ ቀጥታ ጥሪ የተላለፈ" አስመስሎ እንዳቀረበ ተናግረዋል። ቢቢሲ ይቅርታ እንደሚጠይቅም አክለዋል።
ሊቀ መንበሩ ለፓርላማው የባህል፣ ሚዲያ እና ስፖርት ኮሚቴ ምላሽ ለመስጠት በጻፉት ደብዳቤ ላይ ቢቢሲ ጉዳዩን "ለመቅበር ሞክሯል" እንዲሁም በማስታወሻው የተነሱትን ስጋቶች በተመለከተ ምንም እርምጃ አልወሰደም መባሉን ውድቅ አድርገውታል። "በቀላሉ፤ እውነት አይደለም" ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
እሑድ ዕለት ለቢቢሲ የደረሰው የትራምፕ ደብዳቤ ኮርፖሬሽኑ ይቅርታ እንዲጠይቅ እና ፕሬዳንቱን "በተገቢው መንገድ እንዲክስ" ያሳስባል። ቢቢሲ፤ በፕሬዝዳንቱ ላይ "ሐሰተኛ፣ ስም የሚያጠፋ፣ የሚያንኳስስ፣ የሚያሳስት እና አቀጣጣይ መግለጫ" አውጥቷል ሲልም ደብዳቤው ይከስሳል።
የትራምፕ ጠበቃ የሆኑት አሌሃንድሮ ብሪቶ ቢቢሲን በፍሎሪዳ ግዛት ሕግ መሠረት ስም በማጥፋት ከስሰዋል።
የቦርድ ሊቀ መንበሩ ሻህ ለፓርላማው ኮሚቴ በጻፉት ደብዳቤ፤ የውስጥ ማስታወሻው ከወጣ ወዲህ ቢቢሲ ከ500 በላይ አቤቱታዎችን መቀበሉን ገልጸዋል።
ቢቢሲ የአሜሪካ ምርጫ ዘገባዎቹን በተመለከተ በጥር እና ግንቦት ወራት ባደረገው ሰፊ ግምገማ ወቅት የፓናሮማ ዘጋቢ ፊልም አርትኦት ጉዳይ ውይይት እንደተደረገበት አስታውቀዋል።
የቢቢሲ ኤዲቶሪያል ጋይድላይንስ እና ስታንዳርድ ኮሚቴ ባደረገው በዚህ ግምገማ ወቅት የቀድሞው አማካሪ ፔስኮት እና የተወሰኑ የኮሚቴ አባላት ስለ ጉዳዩ ስጋታቸውን ማሰማታቸውንም አክለዋል።
ሻህ፤ "ቢቢሲ ኒውስ ክሊፑን ኤዲት ያደረገበት ዓላማ የንግግሩን መልዕክት [አጠቃሎ] ለማስተላለፍ እንደነበር መስማታቸውን" ተናግረዋል።
ይህም የተደረገው የፓናሮማ ተከታታዮች "የፕሬዝዳንት ትራምፕ ደጋፊዎች ንግግሩን እንዴት እንደተቀበሉት እንዲሁም በወቅቱ መሬት ላይ ምን እየተፈጠረ እንደነበር ይበልጥ እንዲረዱ" ለማድረግ ሲባል መሆኑን አብራርተዋል።
እንደ የቦርድ ሊቀ መንበሩ ገለጻ፤ ጉዳዩ ይበልጥ ንግግር ያልተደረገበት "ይሄ ነው የሚባል የተመልካች አስተያየት ባለማምጣቱ እና ከአሜሪካ ምርጫ በፊት የተላለፈ በመሆኑ" ነው።
የቢቢሲ ቦርድ ሊቀ መንበር ሳሚር ሻህ፤ "መለስ ተብሎ ሲታይ፤ ይበልጥ መደበኛ እርምጃ መውሰድ የተሻለ ነበር" ብለዋል።















