የቻይናው ፕሬዚዳንት ከባይደን ጋር ባደረጉት ውይይት ከትራምፕ ጋር እንደሚሠሩ ገለጹ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የቻይናው መሪ ሺ ጂንፒንግ ከአሁኑ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ጋር ባደረጉት የመጨረሻ ውይይት ከዶናልድ ትራምፕ ጋር እሰራለሁ አሉ።
ፕሬዚደንት ሺ ዕድሉን ተጠቅመው ለዶናልድ ትራምፕ እና በዋሽንግተን ለሚኖረው ቀጣዩ አስተዳደር መልዕክት በሚመስል መልኩ የቻይናን ዓላማዎች ይፋ አድርገዋል።
ውይይቱን በተመለከተ በወጣው መረጃ መሠረት “አዲስ ቀዝቃዛ ጦርነት እንደማያስፈልግ እና ማሸነፍ እንደማይቻል አጽንኦት ሰጥተዋል። ቻይናን ማፈን ጥበብ የጎደለው፣ ተቀባይነት የሌለው እና ውድቀት ነው” ብለዋል ፕሬዝዳንት ሺ።
ሺ አክለውም በቻይና እና በአሜሪካ መካከል ያለው የተረጋጋ ግንኙነት "ለሁለቱም ወገኖች እና ለዓለም ወሳኝ ነው" ብለዋል።
ሁለቱ መሪዎች በፔሩ በተካሄደው ዓመታዊው የእስያ-ፓሲፊክ ኢኮኖሚ ትብብር (አፔክ) የመሪዎች ጉባኤ ጎን ለጎን ባደረጉት ውይይት በባይደን የስልጣን ዘመን ግንኙነታቸው "በውጣ ውረድ" መሞላቱን አምነዋል።
ፕሬዝዳንት ሺ ባረፉበት የሊማው ሆቴል በተካሄደው የቅዳሜው ስብሰባ ላይ አሜሪካ እና ቻይና "እርስ በርስ እንደ ተቃዋሚ ወይም እንደ ጠላት ከተያዩ፣ እርስ በርሳቸው ክፉ ፉክክር ውስጥ ከገቡ እና እርስ በርስ መጎዳዳት ከጀመሩ የቻይና እና የአሜሪካ ግንኙነት ይንኮታኮታል ይሆናል" ብለዋል መሪው።
ቤጂንግ ከዋሽንግተን ጋር የተረጋጋ ግንኙነት የመመሥረት ግብ እንደማይለወጥ እና ከአዲሱ የአሜሪካ አስተዳደር ጋር "ግንኙነቱን ለማስቀጠል፣ ትብብርን ለማስፋት እና ልዩነቶችን ለመቆጣጠር" እንደሚሠሩ አክለው ተናግረዋል።
ባይደን በበኩላቸው በሁለቱ የዓለም ኃያላን አገሮች መካከል ያለው ስትራቴጂካዊ ፉክክር ወደ ጦርነት ሊያድግ አይገባም ብለዋል።
"ሁለቱ አገራት የትኛውም ውድድር ወደ ግጭት እንዲገባ መፍቀድ አይችሉም። ይህ የእኛ ኃላፊነት ነው። ባለፉት አራት ዓመታት ይህንን ግንኙነት መፍጠር እንደሚቻል ያረጋገጥን ይመስለኛል" ሲሉ ተናግረዋል።
ሁለቱም መሪዎች እንደንግድ እና ታይዋንን በመሳሰሉ ጉዳዮች ዙሪያ ውጥረትን በመቀነስ ረገድ መሻሻል መታየቱን ጠቁመዋል።
ተንታኞች እንደሚሉት ከሆነ ትራምፕ ከሁለት ወራት በኋላ ወደ ዋይት ሃውስ ሲመለሱ በቻይና ምርቶች ላይ የታሪፍ ጭማሪ ለማድረግ በገቡት ቃል እና በሌሎች ምክንያቶች የአሜሪካ እና ቻይና ግንኙነት የበለጠ የማይገመት ሊሆን ይችላል።
ተመራጩ ፕሬዝዳንት ከቻይና በሚገቡት ምርቶች ላይ 60 በመቶ ቀረጥ እንደሚጥሉ ቃል ገብተዋል። ታዋቂ የቻይና ተቃዋሚዎችን የውጭ ጉዳይ እና የመከላከያ ሚንስትር ቦታዎች ላይ ሾመዋል።
ትራምፕ በመጀመሪያ የስልጣን ዘመናቸው ቤጂንግን “ስትራቴጂካዊ ተፎካካሪ” ብለዋታል። በኮሮና ወረርሽኝ ወቅት ኮቪድን “የቻይና ቫይረስ” ብለው በመጥራታቸው ግንኙነቱ ይበልጥ ሻክሯል።
የአሜሪካ ከፍተኛ ባለስልጣን ጉብኝትን ምክንያት በማድረግ ቻይና ጦሯን ወደ ታይዋን ማስጠጋቷ እና የስለላ ፊኛ ጉዳይ በባይደን ስልጣን ዘመንም ከቻይና ጋር ያለው ነበረው ግንኙነት ውጥረት ውስጥ ከቶታል።
በደሴቷ ላይ የምታቀርበው የይገባኛል ጥያቄ ቀይ መስመር ነው ትላለች ቻይና።
የባይደን አስተዳደር ከትራምፕ የመጀመሪያ የስልጣን ዘመን በኋላ ከቤጂንግ ጋር ያለውን ፉክክር “በኃላፊነት ለማስተዳደር” አልሞ ተንቀሳቅሷል።
ተንታኞች እንደሚሉት ቤጂንግ የተመራጩ ፕሬዝዳንት አለመተንበይ በጣም ያሳስባት ይሆናል።
“ቻይናውያን ለመደራደር ዝግጁ ናቸው። ምናልባትም በፍጥነት ከትራምፕ ቡድን ጋር ሊደረጉ ስለሚችሉ ንግድ ጉዳዮች ለመወያየት እንደሚገናኙ ተስፋ ያደርጋሉ” ሲሉ የጀርመኑ ማርሻል ፈንድ ኢንዶ-ፓሲፊክ ፕሮግራም ማኔጂንግ ዳይሬክተር ቦኒ ግላዘር ተናግረዋል።
"ትራምፕ በቻይና ምርቶች ላይ ከፍተኛ ታሪፍ ለመጣል ከሞከሩ አጸፋውን ለመመለስም ዝግጁ ናቸው" ብለዋል።
ቻይና “በትራምፕ ፖሊሲ ላይ ተጽዕኖ ለማድረግ አስተማማኝ መመኪያ ስለሌላት ትጨነቅ ይሆናል” ሲሉ አክለዋል።
ባይደን በበኩላቸው ከሺ ጋር ሁልጊዜ አለመግባባቶች እንደነበሩ አምነው፤ በእሳቸው እና በቻይናው መሪ መካከል የተደረጉት ውይይቶች “ግልጽ” እና “እውነተኛ” እንደነበሩ ተናግረዋል።
ባለፈው ዓመት በሳንፍራንሲስኮ የተካሄደውን እና ሁለቱም ወገኖች አደንዛዥ እጾችን እና የአየር ንብረት ለውጥን በመዋጋት ረገድ ከስምምነት የደረሱበትን ቁልፍ ስብሰባ ጨምሮ መሪዎቹ በባይደን የአስተዳደር ዘመን ሦስት ጊዜ ፊት ለፊት ተገናኝተዋል።
የባይደን አስተዳደር የትራምፕ ዘመን ታሪፎችንም አስቀጥሏል። በግንቦት ወር ደግሞ በቻይና የኤሌክትሪክ መኪኖች፣ የፀሐይ ፓኔሎች እና ብረቶች ላይ ያነጣጠረ ታክስም ጥሏል።
በአካባቢው እየጨመረ የመጣውን የቻይናን በላይነት ለመቋቋም በእስያ እና በፓስፊክ ውቅያኖስ የመከላከያ ትብብሩንም አጠናክሯል። ታይዋን በቻይና ከተወረረች አሜሪካ ትከላከላታለች ሲሉ ተሰናባቹ ፕሬዝዳንት ተናግረዋል።












