ከ17 ዓመት ሴት ጋር ወሲብ በመፈጸም የተከሰሰው የ18 ዓመት እንግሊዛዊ በዱባይ ታሰረ

የፎቶው ባለመብት, Detained in Dubai
ዱባይ ውስጥ ከ17 ዓመት እንግሊዛዊት ሴት ጋር ወሲብ በመፈጸም የተከሰሰው የ18 ዓመት እንግሊዛዊ ታሰረ።
ማርከስ ፋካራ የተባለው ወጣት በዱባይ እጁን ሰጥቶ የአንድ ዓመት እስራት ቅጣቱን እየተጠባበቀ ነው ተብሏል።
የልጅቷ እናት የተለዋወጡትን የጽሑፍ መልዕክት ካየች በኋላ ጉዳዩን ለዱባይ ፖሊስ ጠቁማለች። ፖሊስም ማርከስ በሆቴሉ ሳለ አስሮታል። ከታሰረ በኋላ በዋስ ተለቋል። ቤተሰቦቹ ለሥራ ወደ ለንደን ተመልሰዋል።
በዱባይ ከ18 ዓመት በታች ካለ ሰው ጋር ወሲብ መፈጸም ወንጀል ነው።
ዲቴንድ ኢን ዱባይ የተሰኘው የዩናይትድ ኪንግደም የመብት ተሟጋች ቡድን እንዳለው ማርከስ ለፖሊስ ራሱን አሳልፎ ሰጥቷል።
እንግሊዛዊውን እየደገፈው እንደሆነ በዱባይ ያለው የዩኬ ቢሮም አስታውቋል።
የዲቴንድ ኢን ዱባይ ዋና ኃላፊ ራዳ ስተርሊንግ እንዳለችው፣ ማርከስ በእስር ቆይታው በአካላዊና አእምሯዊ ጤናው ላይ የሚያተኩር ይሆናል።
"ይግባኝ ከጠየቀ በአጭር ጊዜ ይለቀቅ ይሆናል። በዱባይ ለዓመት ለመታሰር እጁን ለሰጠ ሰው ምን ማለት ይቻላል። በጣም ጠንካራና መልካም ሰው ነው። ቶሎ ወደ አገሩ ይመለሳል ብዬ አምናለሁ" ብላለች።
ወላጆቹ ይቅርታ እንዲደረግለት እየጠየቁ ነው።
የዩኬ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጸሐፊ ዴቪድ ላሚ "ድጋፍ እንዲሰጡም" ጠይቀዋል።
የዳውኒንግ ስትሪት ቃል አቀባይ ባለፈው ወር "ጉዳዩ ለማርከስ ቤተሰቦች ከባድ እንደሆነ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይገነዘባሉ" ብለዋል።
የሁለቱ ወጣቶች ቤተሰቦች በተባበሩት አረብ ኤምሬትስና በዩናይትድ ኪንግደም ሽርሽር ላይ ነበሩ። በዩኬ ለወሲብ ፈቃድ የሚሰጥበት ዕድሜ 16 ነው።
ማርከስ ስለ ፍቅር ግንኙነቱ ለቤተሰቦቹ ቢናገርም እሷ ግን ለቤተሰቦቿ አልገለጸችም ነበር።
የዱባይ መንግሥት "በአገሪቱ ሕግ ዕድሜዋ ለግብረ ሥጋ ግንኙነት አልደረሰም። ቅሬታ ያቀረበችውም እናቷ ናት። የዱባይ ሕግ የሁሉንም አካላት መብት ለማስጠበቅ የቆመ ነው" ሲል መግለጫ አውጥቷል።












