ትራምፕ በጃፓን ላይ እስከ 35 በመቶ ታሪፍ ለመጣል ዛቱ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በሁለቱ አገራት መካከል የታሪፍ ስምምነት ላይ ለመድረስ የተቀመጠው ቀነ ገደብ ከመጠናቀቁ በፊት መግባባት ላይ የማይደረስ ከሆነ በጃፓን ላይ "30 ወይም 35 በመቶ" ታሪፍ እንደሚጥሉ ዛቱ።
ይህም በፈረንጆቹ ሚያዝያ 2 ቀን በዓለም ዙሪያ ባሉ አገራት ላይ ከፍተኛ የገቢ ቀረጥ ባወጁበት ወቅት ጃፓን ላይ ከተጣለው የ24 በመቶ ታሪፍ የበለጠ ይሆናል።
በአብዛኞቹ የንግድ አጋሮች ላይ ተጥሎ የነበረው ታሪፍ ከዋሽንግተን ጋር የሚደራደሩበት ጊዜ ለመስጠት በሚል ለ90 ቀናት ወደ 10 በመቶ ዝቅ ብሎ ነበር።
ይህ የእፎይታ ጊዜ በሚቀጥለው ሳምንት ረቡዕ የሚገባደድ ሲሆን ፕሬዝዳንት ትራምፕ ቀነ ገደቡን የማራዘም ሃሳብ እንደሌላቸው ተናግረዋል።
ትራምፕ ከቶኪዮ ጋር ስምምነት ላይ መድረስ ስለመቻሉ ጥራጣሬ አላቸው።
"ከጃፓን ጋር ያለንን ጉዳይ ጨርሰናል። ስምምነት እንደምናደርግ እርግጠኛ አይደለሁም። እጠራጠራለሁ" ሲሉ ማክሰኞ በኤር ፎርስ ዋን ላይ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
ጃፓን ረቡዕ ዕለት በጋዜጣዊ መግለጫቸው ላይ ትራምፕ የታሪፍ ጭማሪ ለማድረግ ስላደረጉት ዛቻ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥባለች።
"ፕሬዚደንት ትራምፕ የተናገሩትን እናውቃለን፤ ነገርግን የአሜሪካ መንግሠዕት ባለስልጣናት በሚሰጡት እያንዳንዱ አስተያየት ላይ ምላሽ አንሰጥም" ሲሉ የአገሪቱ ምክትል ዋና ፀሀፊ ካዙሂኮ አኦኪ ተናግረዋል።
እንደሌሎች ብዙ አገሮች፣ አብዛኛው የጃፓን ወደ አሜሪካ የምትልካቸው ምርቶች በአሁኑ ጊዜ 10 በመቶ ቀረጥ ተጥሎባቸዋል።
በተጨማሪም በጃፓን ተሽከርካሪዎች እና የተሽከርካሪ ክፍሎች ላይ 25 በመቶ የገቢ ታክስ አለባቸው።
ብረት እና አሉሚኒየም ላይ ደግሞ 50 በመቶ ታሪፍ ይጣልባቸዋል።
ማክሰኞ ዕለት የጃፓን የካቢኔ ዋና ፀሃፊ ዮሺማሳ ሃያሺ ከዋሽንግተን ጋር ለመስማማት ሲሉ የአገራቸውን ገበሬዎች ሊጎዱ የሚችሉ ዕርምጃዎችን እንደማይወስዱ ተናግረዋል ።
"አገራት አሜሪካን በተመለከተ ምን ያህል ቅጥ እንዳጡ ለሰዎች ለማሳየት ያህል፣ የእኛን ሩዝ አይገዙም ነገር ግን ከፍተኛ የሆነ የሩዝ እጥረት አለባቸው፤ [ይህን ስል] ለጃፓን ትልቅ ክብር አለኝ" ሲሉ በትሩዝ የማኅበራዊ ገጻቸው ላይ ጽፈዋል።
ትራምፕ በአዲሶቹ ታሪፎች የእፎይታ ጊዜ ውስጥ 90 የንግድ ስምምነቶችን እንደሚፈርሙ የተናገሩ ቢሆንም እስካሁን ከአሜሪካ ጋር ስምምነት የደረሰችው እንግሊዝ ብቻ ናት።












