ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በአሜሪካ ሕዝብ በተሰበሰበበት መኪና የነዳው ግለሰብ 10 ሰዎች ገደለ
በአሜሪካ፣ ኒው ኦርሊያንስ ከተማ በሚገኘው ፍሬንች ኳርተር በሚባለው አካባቢ አንድ አሽከርካሪ ሰዎች በተሰበሰቡበት በመኪና በመግጨት አሥር ሰዎችን ሲገድል ቢያንስ 35 የሚጠጉ ሰዎችን ደግሞ ማቁሰሉ ተገለጸ።
በርበን በተባለ ጎዳና በከፍተኛ ፍጥነት መኪናውን እየነዳ የሄደው አሽከርካሪ ከመኪናው ወጥቶ ጥይት መተኮስ መጀመሩንና ፖሊሶችም መልሰው እንደተኮሱበት ተገልጿል።
የዓይን እማኞች እንዳሉት ብዙ ሰዎች ተጎድተው መንገድ ላይ ወድቀው ታይተዋል።
የኒው ኦርሊያንስ ፖሊስ ቃል አቀባይ ለቢቢሲ የአሜሪካ አጋር ሲቢኤስ "መጀመሪያ ላይ በደረሰን ሪፖርት መኪናው የተሰበሰቡ ሰዎች ላይ ወጥቷል" ብለዋል።
አካባቢው በጎብኚዎች የሚዘወተር እንደሆነ ተገልጿል። ክስተቱም የተፈጠረው በአገሬው አቆጣጠር ለሊት 9:15 አካባቢ ነው።
የአሜሪካ የምርመራ ተቋም ኤፍቢአይ ጉዳዩን እየመረመረ ይገኛል።
የከተማው የአደጋ ጊዜ ክፍል 'ኖላ ሬዲ' እንዳለው ነዋሪዎች ከአካባቢው እንዲርቁ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷል።
የአደጋ ጊዜ ክፍሉ በኤክስ ገጹ "በካናልና በርበን ጎዳናዎች ሰዎች ተገድለዋል፤ ከአካባቢው ራቁ" ብሏል።
ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የወጡ ተንቀሳቃሽ ምሥሎች እንደሚያሳዩት ብዙ ሰዎች ተጎድተዋል። ከጀርባ የሚመጣ የተኩስ ድምጽም ይሰማል።
አንድ የዓይን እማኝ ለሲቢኤስ እንዳሉት አሽከርካሪው መኪናውን ሰው በተሰበሰበበት ከነዳ በኋላ ከመኪናው ወጥቶ ተኩስ ከፍቷል።
የሉዊዝያና አገረ ገዢ ጄፍ ላንድሪ በኤክስ ገጻቸው "ለተጎዱትና ድጋፍ እየሰጡ ላሉትም እፀልያለሁ። ይህ የጭካኔ ድርጊት ነው" ብለዋል።
አንድ የዓይን እማኝ እንዳሉት መኪናው ሰዎቹ በተሰበሰቡበት አካባቢ በቀጥታ ተነድቷል። አካባቢው የጎርጎሮሳውያኑን አዲስ ዓመት በሚያከብሩ ሰዎች የተሞላ ነበር።
የሉዊዝያና ነዋሪ ለቢቢሲ "መጠጥ ቤት ሳለን ነው ተኩስ የሰማነው። ሙዚቃው ይጮህ ነበር። ሰዎች ጠረጴዛ ሥር መደበቅ ጀመሩ። ፖሊስ ከአካባቢው እንድንወጣ ሲያደርግ የተገደሉ ሰዎች በየመንገዱ አየን" ብለዋል።
የኒው ኦርሊያንስ ከንቲባ ላቶያ ካንትሪል ምርመራ እየተደረገ እንደሆነና ከዋይት ሀውስ ጋር እንደተነጋገሩ ገልጸዋል።
አንድ ግለሰብ መኪናውን "በፍጥነት በቦታው እንደነዳና" ይህም "ብዙ ሰዎችን ለመጉዳት ሆነ ተብሎ የተረደገ" እንደሆነ የፖሊስ ባልደረባ አን ክሪክፓትሪክ ገልጸዋል።
ከተጎዱት መካከል ምን ያህሉ የከተማው ነዋሪዎችና ምን ያህሉ ቱሪስቶች እንደሆኑ በግልጽ አልታወቀም።
የፖሊስ ባልደረባዋ እንዳሉት በአካባቢው ከ300 በላይ ፖሊሶች ቢኖሩም ግለሰቡ "ሆነ ብሎ" ጥቃቱን ፈጽሟል።
"የተቻለውን ያህል ጉዳት ለማድረስ ቆርጦ እንደተነሳ ማወቅ ይቻላል" ብለዋል። አያይዘውም "የሽብር ጥቃት አይደለም" ሲሉ ተናግረዋል።
በአካባቢው ሦስት ተቀጣጣይ ፈንጂዎች እንደተገኙና ጉዳዩ እስከሚጣራ ነዋሪዎች ከቦታው እንዲርቁ አሳስበዋል።