ኢትዮጵያ ከ50 ሺህ በላይ ተሳታፊዎች የሚታደሙበትን ጉባኤ እንድታስተናግድ ተመረጠች

ኢትዮጵያ ከሁለት ዓመት በኋላ የሚካሄደውን የዓለማችን ዋነኛውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአየር ፀባይ ለውጥ ጉባኤን እንድታስተናግድ ብራዚል ውስጥ እየተካሄደ ባለው የዘንድሮ ስብሰባ ላይ ተመረጠች።

ኮፕ በመባል የሚታወቀውን እና በየዓመቱ ከሚካሄደውን የአየር ፀባይ ለውጥ ጉባኤ በአውሮፓውያኑ 2027 የሚደረገውን "ኮፕ32" ኢትዮጵያ እንድታስተናግድ የተመረጠችው ናይጄሪያን በመብለጥ ነው።

ኮፕ የሚለው ስያሜ 'ኮንፈረንስ ኦፍ ፓርቲስ' የሚሉት ቃላት ምህጻረ ቃል ሲሆን በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአየር ፀባይ ለውጥ ስምምነት ማዕቀፍ ስር የሚካሄድ የዓላማችን ዋነኛው የአካባቢ ጥበቃ ጉባኤ ነው።

በጉባኤው ከአሜሪካ በስተቀር መላው የዓለም አገራት እና ሌሎችም በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ተሳታፊዎች የሚታደሙ ሲሆን፣ ወሳኝ ድርድሮች እና ስምምነቶች የሚደረሱበት ነው።

ይህ ዓመታዊ ጉባኤ መካሄድ የጀመረው በአውሮፓውያኑ 1992 የአየር ፀባይ ለውጥ የዓለማችን ስጋት መሆኑ በመንግሥታቱ ድርጅት ተቀባይነት አግኝቶ ከስምምነት ከተደረሰ በኋላ ነው።

ኢትዮጵያ ይህንን ጉባኤ ለማዘጋጀት መመረጧ በጉባኤው አጀንዳ ላይ እና በማብቂያው ላይ በሚተላለፉ ውሳኔዎች ላይ ከፍተኛ ሚና እንዲኖራት እንደሚያደርግ የሮይተርስ ዘገባ ያመለክታል።

ሰላሳኛው የኮፕ ጉባኤ በብራዚሏ ቤሌም ከተማ ውስጥ እየተካሄደ ሲሆን፣ የቀጣዩን ዓመት ጉባኤ አውስትራሊያ እና ቱርክ ለማስተናገድ እየተፎካከሩ ነው። 31ኛውን የኮፕ ጉባኤ አስተናጋጅ በቀጣዮቹ ቀናት ይታወቃል ተብሎ ይጠበቃል።

ባለፉት ዓመታት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የዛፍ ችግኞችን እየተከለች የምትገኘው እና ግዙፍ ታዳሽ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫዎችን እየገነባች ያለቸው ኢትዮጵያ በአካባቢ ጥበቃ በኩል የምትጠቀስ ናት።

የኮፕ ጉባኤ አስተናጋጅ አገራት በስብሰባው የፕሬዝዳንትነት ሚና ስለሚኖራቸው የጉባኤውን ግቦች ለመቅረጽ ከመቻላቸው በተጨማሪ፣ የራሳቸውን የአየር ፀባይ ለውጥን የተመለከቱ ሥራዎችን ለማስተዋወቅ ይችላሉ።

በተጨማሪም በጉባኤው ላይ በሚደረጉ ድርድሮች ወቅት የሚከሰቱ አለመግባባቶችን ለመሸምገል እና መፍትሄ ለማስቀመጥ ሥልጣን ያገኛሉ።

ኢትዮጵያ በአውሮፓውያኑ 2027 የሚካሄደውን ጉባኤ በአዲስ አበባ እንድታስተናግድ የአፍሪካ አገራትን ድጋፍ አግኝታለች።

በብራዚል የኢትዮጵያ አምባሳደር ሉልሰገድ ታደሰ በስብሰባው ላይ ባደረጉት ንግግር አገራቸው ጉባኤውን እንድታስተናግድ በመመረጧ "በኢትዮጵያ ሕዝብ እና መንግሥት ላይ እምነት ስለተጣለ" ምስጋና አቅርበዋል።

ይህ የአየር ፀባይ ለውጥ ጉባኤ ኮፕ በየዓመቱ በዙር በተለያዩ አህጉራት ውስጥ የሚካሄድ ሲሆን፣ አስተናጋጁ አገር ሲመረጥም በአህጉሩ ያሉ አገራት ሙሉ ድጋፍ መገኘት አለበት።

ኢትዮጵያ ከሁለት ዓመት በኋላ እንድታካሂደው የተመረጠችበትን ጉባኤ ከኢህ ቀደም አራት የአፍሪካ አገራት አስተናግደውታል። እነሱም ኬንያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ሞሮኮ እና ግብፅ ነበሩ።

ኮፕ ጉባኤዎች ከዓለም ዙሪያ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ከተለያዩ የሙያ ዘርፎች የተውጣጡ የአየር ፀባይ ለውጥ የሚመለከታቸው ተሳታፊዎች የሚታደሙበት ከዓለማችን ታላቅ ስብሰባዎች አንዱ ነው።

አሁን ብራዚል ውስጥ እየተካሄደ በሚገኘው ኮፕ 30 ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ ከዓለም ዙሪያ 50 ሺህ በላይ ሰዎች ለመሳተፍ ተመዝግበዋል።

በጉባኤው ላይ ጋዜጠኞችን፣ የአየር ፀባይ ሳይንቲስቶች፣ የቀደምት ማኅበረሰብ መሪዎች እና የ195 አገራት ተወካዮችን ጨምሮ ሌሎች በአካባቢ ጥበቃ ላይ ተሳትፎ ያላቸው አካላት ይገኛሉ።

የዓለማችን ኃያል አገር አሜሪካ በዶናልድ ትራምፕ የሥልጣን ዘመን ከጉባኤው አግልላለች። ባለፈው መስከረም በተካሄደው የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ ላይም ፕሬዝዳንቱ የአየር ፀባይ ለውጥ የሚባለው ሐሰት መሆኑን እና አጭበርባሪዎች የፈጠሩት ሃሳብ ነው ሲሉ አጣጥለውታል።