ተስፋ የተጣለበት አዲስ የኤችአይቪ መከላከያ መድኃኒት በእንግሊዝ እና በዌልስ ፈቃድ አገኘ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የኤችአይቪ መከላከያ መድኃኒት በእንግሊዝ እና በዌልስ ፈቃድ አገኘ። በመርፌ የሚሰጠው መድኃኒቱ በዓመት ስድስት ጊዜ የሚወሰድ ነው።
ከዚህ ቀደም የነበረው መድኃኒት በየቀኑ የሚወሰድ ነበር። በዩናይትድ ኪንግደም፣ በስኮትራልድ ግዛት መድኃኒቱ ይቀርብ የነበረ ሲሆን፣ በእንግሊዝ እና በዌልስም መሰጠት መጀመሩ "ታሪክ ይቀይራል" ተብሏል።
ካቦተግራቨር (cabotegravir ወይም CAB-LA) የተባለው መድኃኒት፤ ዩኬ በ2030 ኤችአይቪን ለማስወገድ የያዘቸው ዕቅድ አካል ነው።
ለናካፕቪር (lenacapavir) በተባለው መድኃኒት ላይ የተሠሩ ጥናቶች የመጀመሪያ ደረጃ ውጤት እንደሚያሳው፤ ሕሙማን በዓመት አንዴ ብቻ መድኃኒቱን ሊወስዱ ይችላሉ።
የጤና እና ማኅበራዊ ደኅንነት ጸሐፊ ዌስ ስተሪንግ "ይሄ ታሪክ ቀያሪ መድኃኒት ፈቃድ ማግኘቱ መንግሥት ዘመናዊ መድኃኒት በማቅረብ የሰዎችን ሕይወት ለመታደግ ቁርጠኛ መሆኑን ያሳያል" ብለዋል።
"የኤችአይቪ መድኃኒት ማግኘት ለማይችሉ ሰዎች ተስፋ የሚሰጥ ነው" ሲሉም አክለዋል።
PrEP ወይም pre-exposure prophylaxis በኤችአይቪ ያልተያዙ ሰዎች ለቅድመ ጥንቃቄ የሚወስዱት ሕክምና ነው።
ለዓመታት የኤችአይቪ መድኃኒት ጥቅም ላይ ሲውል ቆይቷል። የበሽታውን ስርጭት ለመቆጣጠር የሚውለው መድኃኒቱ በየቀኑ የሚወሰድ ስለሆነ ለሕሙማን ምቹ አይደለም።
መድኃኒቱን በየቀኑ መውሰድ ፈታኝ ከመሆኑ ባሻገር ሕሙማን መገለል እንዲደርስባቸውም ሲያደርግ ቆይቷል።
የጎዳና ተዳዳሪዎች፣ የቤት ውስጥ ጥቃት ሰለባ የሆኑ ሰዎች እንዲሁም ሌሎችም ሕሙማን መድኃኒቱን ለመውሰድ እንደሚቸገሩ ይናገራሉ።
ለወራት የሚቆየው በመርፌ የሚሰጠው መድኃኒት ለሕሙማን ተስፋ ሰጥቷል።
በግብረ ሥጋ ግንኙነት፣ ከእናት ወደ ልጅ ወይም ደም በነካ መርፌ የሚተላለፈው ኤችአይቪ የሰውነትን በሽታ የመከላከል አቅም ያዳክማል።
የዩኬ ብሔራዊ የጤና አገልግሎት አዲስ ከተሠራው መድኃኒት አምራች የዋጋ ቅናሽ አግኝቷል።
አንድ ታካሚ መድኃኒቱን ለመውሰድ በዓመት 7,000 ፓውንድ ያወጣል።
መድኃኒቱ ለአዋቂዎች እና ጤናማ የሰውነት ክብደት ላላቸው ታዳጊዎች ይሰጣል። እነዚህ ታዳጊዎች ለኤችአይቪ ተጋላጭ ከሆኑ እና እንክብል መውሰድ ካልቻሉ አዲሱን መድኃኒት ይወስዳሉ።
መጀመሪያ ላይ ለ1,000 ሰዎች መድኃኒቱ ይቀርባል። አብዛኞቹ ሕሙማን እንክብል መውሰድ ይቀጥላሉ።
የኤችአይቪ እንክብል መድኃኒት የሚወስደው ዶም ባልደዊን "በመርፌ የሚሰጥ አዲስ መድኃኒት መምጣቱ በጣም አስደስቶኛል" ይላል።
"አሁንም የኤችአይቪ መድኃኒት ላይ የሚሠራው ምርምር ብዙ ሥራ ይቀረዋል። ሆኖም ኤችአይቪን ለመከላከል የሚደረገው ጥረት አበረታች ሆኗል" ሲልም አክሏል።
በ1980ዎቹ ኤችአይቪ ወረርሽኝ ከነበረበት ወቅት አንስቶ ባለፉት ዓመታት በግንዛቤ እጥረት፣ በመገለል እና ሕክምና ተደራሽ ባለመሆኑ ምክንያት ብዙዎች ሕይወታቸውን ማጣታቸውን ዶም ያስታውሳል።
"በኤችአይቪ መያዝ የሞት ፍርድ መሆኑ አብቅቷል" ሲልም የታየውን ለውጥ ይገልጻል።
የዩኬ ብሔራዊ የጤና አገልግሎት እንዳለው በቀጣይ ወራት መድኃኒቱ በሕክምና ተቋማት ይቀርባል።
'ቴራንስ ሂግንስ ትረስት' በተባለው የፀረ ኤችአይቪ ድርጅት የሚሠሩት ሪቻርድ አንገል እንደሚሉት፤ ሕሙማን መድኃኒት ለማግኘት ረዥም ሰዓት መጠበቅ አለባቸው።
መድኃኒቱን በተለያዩ የሕክምና መስጫ ተቋማት ተደራሽ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ያስረዳሉ።
"መድኃኒቱን ማግኘት ለማይችሉ ሰዎች ማዳረስ ያስፈጋል። እኩልነትን ማረጋገጥ የሚቻለው በዚህ መንገድ ነው" ይላሉ።
በዩኬ የኤችአይቪ ቅድመ መከላከያ ሕክምና የሚወስዱ ሰዎች ቁጥር ጨምሯል። አምና 146,098 ሰዎች ሕክምናውን አግኝተዋል።
የሕክምናው ተደራሽነት ሲታይ፤ ነጮች 79.4% እንዲሁም ጥቁሮች 77.8% ሲሆን፤ በተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪ ሴቶች እና ወንዶች ያለው ተደራሽነት ውስን ነው።
በዩኬ ብሔራዊ የጤና አገልግሎት የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪዎች አማካሪ ዶ/ር ማይክል ብራዲ፤ በመርፌ የሚሰጠው አዲሱ መድኃኒት "ለኤችአይቪ ተጋላጭ ለሆኑ ሰዎች ሁነኛ አማራጭ ነው" ብለዋል።















