ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የአብን አባሉ አቶ ጣሂር ሙሐመድ “በግል ምክንያት” ከአማራ ክልል የመንግሥት ኃላፊነት መልቀቃቸውን አስታወቁ
ላለፈው ሁለት ዓመት ከስምንት ወር ገደማ የአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ሆነው ሲሰሩ የነበሩት የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ አብን (አባሉ) አቶ ጣሂር ሙሐመድ “በግል ምክንያት” ከኃላፊነት መልቀቃቸውን ለቢቢሲ ተናገሩ።
በአቶ ጣሂር ቦታ ሌላኛው የአብን አባል አቶ መልካሙ ፀጋዬ በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር መሾማቸውን የአማራ ክልል ኮሚዩኒኬሽን አስታውቋል።
አዲሱ ተሿሚ አቶ መልካሙ፣ በፓርቲያቸው ጥቆማ ወደ ኃላፊነቱ እንደመጡ ተናግረዋል።
“በሥራ አስፈጻሚና ማዕከላዊ ኮሚቴ እያገለገልኩ ስለሆነ ሊሆን ይችላል” ሲሉ ለቢቢሲ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
ስድስተኛው አገር አቀፍ ምርጫን ያሸነፈው ገዢው ብልፅግና ፓርቲ መንግስት ሲመሰረት በተከተለው የተቃዋሚ ፓርቲ አባላትን በመንግስት ኃላፊነት ላይ የማካተት ውሳኔ መሰረት ወደ ኃላፊነት የመጡት አቶ ጣሂር፤ የተሾሙት መስከረም 2014 ዓ.ም. ነበር።
በወቅቱ የክልሉ ፕሬዝዳንት የነበሩት ዶ/ር ይልቃል ከፋለ ለኃላፊነት ያቀረቧቸው ሌላኛው የተቃዋሚ ፓርቲ አባል የአማራ ዴሞክራሲያዊ ኃይል ንቅናቄ (አዴኃን) ሊቀመንበር አቶ ተስፋሁን አለምነህ ነበሩ። አቶ ተስፋሁን የተሾሙት የክልሉ የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ኃላፊ ሆነው ነበር።
ከሹመቱ በኋላ ሶስት ዓመት ለሚጠጋ ጊዜ በቢሮ ኃላፊነት የቆዩት አቶ ጣሂር፤ ከኃላፊነት ለመልቀቅ ጥያቄ ያቀረቡት ከስድስት ወር በፊት እንደነበር ለቢቢሲ ገልፀዋል። ይሁንና “በክልሉ ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ ተከትሎ አመራሩ በተለያዩ ሁኔታዎች በመያዙ (busy በመሆኑ)” ጥያቄያቸው መልስ ሳያገኝ መቆየቱን አስረድተዋል።
ባለፉት “ሶስት፣ አራት ወራት” ወዲህ አንስቶ ከኃላፊነት የመልቀቅ ጉዳይ ላይ ከክልሉ አመራሮች ጋር “በዝርዝር” ንግግር ማድረጋቸውን ያስታወሱት አቶ ጣሂር፤ የክልሉ መንግሥት ጥያቄውን እንደተቀበለው ተናግረዋል። የቀድሞው የአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ፤ “ትንሽ የቤተሰብ ጉዳይ ስለነበረብኝ በቤተሰብ እና በራሴ ጉዳይ ነው የለቀቅሁት” ሲሉ ከኃላፊነት የለቀቁበትን ምክንያት አስረድተዋል።
አቶ ጣሂር፤ “[ከክልሉ አመራሮች ጋር[ በመነጋገር ከፓርቲያችን ሰው ተክተን ነው የወጣሁት” ሲሉም ከኃላፊነት ሲለቅቁ በእሳቸው ቦታ የሚሾም ሌላ የፓርቲው አባል እንዲተካ መደረጉን ለቢቢሲ ገልጸዋል።
የአማራ ክልል ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ዛሬ ማክሰኞ ሚያዝያ 22፤ 2016 ዓ.ም. በፌስቡክ ገጹ ባወጣው መረጃ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አረጋ ከበደ አቶ መልካሙ ፀጋዬን ባህል እና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አድርገው መሾማቸውን አስታውቋል።
አዲሱ ተሿሚ አቶ መልካሙ፤ የአብን ስራ አስፈጻሚ አባል ሲሆኑ የፓርቲው የፅህፈት ቤት ኃላፊም ሆነው ሲሰሩ ነበር።
አቶ መልካሙን ለቢሮ ኃላፊነት እንዲሾሙ በፓርቲው የተመረጡት ያላቸውን “የተሻለ የአመራር ሂደት” እና “የመንግስት ቢሮክራሲ ልምድ” ከግምት ውስጥ በማስገባት እንደሆነ አቶ ጣሂር ገልጸዋል።
አቶ ጣሂር በቀጣይ መዳረሻቸው የት ሊሆን እንደሚችል ከቢቢሲ ለቀረበላቸው ጥያቄ “እሱን አሁን መናገር አልችልም” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
የቀድሞው የክልሉ ባህል እና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ ጣሂር፤ በትግራይ ተቀስቅሶ ወደ አማራ እና አፋር ክልሎች ተስፋፍቶ የነበረውን ጦርነት ያስቆመው የፕሪቶሪያ ግጭትን በዘላቂነት የማስቆም ስምምነት ከተፈረመ በኋላ በጥር 2015 ዓ.ም. የተከበረው የጥምቀት በዓል በጎንደር ከተማ በድምቀት ለመካሄዱ የነበራቸው ሚና ስማቸው ይነሳል።
አሁን በክልሉ ባለው ግጭት ምክንያት ግን “በባህልና ቱሪዝም ዘርፍ በታቀደው እና በሚፈለገው ልክ ተግባራትን መፈፀም እንዳልተቻለ” ቢሮው ማስታወቁን የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ባለፈው ሳምንት ዘግቦ ነበር።
አዲሱ ተሿሚ ምን ይላሉ?
አሁን በአማራ ክልል ካለው አለመረጋጋት ጋር በተያያዘ ምን ፈተናዎች ሊገጥሟቸው እንደሚችሉ አቶ መልካሙ ተጠይቀው “ክልሉ ያለበት ሁኔታ ይታወቃል። ቱሪዝም ደግሞ ሰላም ይፈልጋል። የሰላሙ ጉዳይ ፈተና ሊሆን ይችላል። ፈተናዎቹ ከባድ ናቸው። በክልሉ ካለው አመራር ጋር እየተናበብን ሥራዎችን ለመሥራት ጥረት አደርጋለሁ” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት በፌደራልም ይሁን በክልል የኃላፊነት ቦታዎች ሲቀመጡ ከተቃውሞ ፖለቲካቸው ጋር ይጋጭ እንደሆነ ከቢቢሲ የተጠየቁት አቶ መልካሙ፣ እንደ ፓርቲ ከብልጽግና ፓርቲ ጋር “ልዩነቶች አሉን” ብለው እነዚህን ልዩነቶች “አስምረን ነው ሥራዎች እየሠራን ያለነው” ብለዋል።
“ከተመረጠ መንግሥት” ጋር አብሮ መሥራት ከፓርቲያቸው አሠራር ጋር የሚጣረስ እንዳልሆነም አክለዋል።
አሁን በክልሉ ካለው ሁኔታ አንጻር በመንግሥታዊ ኃላፊነት መቀመጥ ከፓርቲያቸው ደጋፊዎች ሊያስነሳ ስለሚችል ቅራኔ ለቀረበላቸው ጥያቄ “እንዲያውም አሁን ተናበን መሥራት አለብን። ሰላም እንዲመጣ” ሲሉ መልሰዋል።
ከአብን አባላት መካከል በአቋም ልዩነት ፓርቲውን የለቀቁ እንዲሁም በእስር ላይ የሚገኙም እንዳሉ በመጥቀስ ከመንግሥት ጋር አብሮ መሥራት ጫናዎች ይኖሩት እንደሆነ ተጠይቀው “ጫናዎች ይኖራሉ። ሌሎች አብረውን ሲታገሉ የነበሩ የሚያነሱት ሐሳብ እንደተጠበቀ ሆኖ ፓርቲው ያሳለፈውን ውሳኔ ተቀብዬዋለሁ” በማለት አቋማቸውን ገልጸዋል።