ሳካ ላይ ጥፋት ተሰርቷል? በአስደናቂ ጎሎች የታጀበው የማድሪድ እና ሲቲ ጨዋታ

ትናንት ማክሰኞ ሚያዚያ 2/2016 ዓ.ም. ምሽት የተካሄዱት የቻምፒየንስ ሊግ የሩብ ፍጻሜ ግጥሚያዎች በአስደናቂ ጎሎች ታጅበው እና ብዙ ባነጋገሩ የዳኞች ውሳኔዎች ተጠናቀዋል።

የባለፈው ዓመት የውድድሩ አሸናፊ ማንቸስተር ሲቲ ወደ ቤርናቤዩ አቀንቶ ከማድሪድ ጋር ሦስት አቻ ተለያይቷል።

አርሰናል ደግሞ የጀርመኑን ኃያል አሜሬትስ ላይ አስተናግዶ ሁለት አቻ ተለያይቷል።

ኢሜሬትስ ላይ በተደረገው ጨዋታ በፍጻሜው ሰዓት ላይ ዳኛው ያስተላለፉት ውሳኔ የብዙዎች መከራከሪያ ሆኗል።

ሁለቱ ቡድኖች 2 አቻ ሆነው በተጨማሪ ሰዓት ቡካዮ ሳካ ከሙኒኩ ግብ ጠባቂ ኑዬር ጋር ፊት ለፊት ሲገናኝ አርሰናል ባለቀ ሰዓት ጨዋታውን የሚያሸንፍ መስሎ ነበር። ሳካ ከግብ ጠባቂው ጋር ተጋጭቶ ሲወድቅ ያለ ጥርጥር ፍጹም ቅጣት ምት መስሎ ነበር።

ዳኛው ግን ጨዋታው ይቀጥል አሉ።

ሳካ ፍጹም ቅጣት ምት ውስጥ የወደቀው ሆነ ብሎ እግሩን ከግብ ጠባቂው እግር ጋር በማጋጨቱ ነው የሚሉ እንዳሉ ሁሉ፤ ግብ ጠባቂው ሁለቱንም እግር በመክፈቱ በፍጥነት ላይ የነበረውን ሳካ አደናቅፎ ጥሏል በማለት ፍጹም ቅጣት ምት ለአርሰናል ይገባው ነበር የሚሉም አሉ።

የቀድሞ የዩናይትድ ተከላካይ ሪዮ ፈርዱናንድ፤ “ይህ እንዴት ፍጹም ቅጣት አይደለም። . . . የኑዬር እንቅስቃሴን በመመልከት ብቻ ፍጹም ቅጣት ምት መሰጠት ነበረበት” ብሏል።

በሌላ በኩል የቀድሞ የአርሰናል ተከላካይ ማቲው አፕሰን ደግሞ ከፈርዲናንድ በተለየ፤ “መጀመሪያ ስመለከተው ፍጹም ቅጣት ምት መስሎኝ ነበር። ደግሜ ስመለከተው ግን ግጭቱን የፈጠረው ቡካዮ ሳካ ነው። ዳኛው በከባድ ጫና ውስጥ ሆነው ትክክለኛ ውሳኔ ወስነዋል” ብሏል።

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ በክስተቱ ላይ ቫር ጣልቃ አለመግባቱ መገለጹ ደግሞ አርሰናልን ያበሳጨ ነገር ሆኗል። የቫር ዳኞች የመሃል ዳኛው ክስተቱን እንዲመለከቱ እድል ቢሰጣቸው ኖሮ ውሳኔያቸውን ይቀይራሉ የሚል አስተያየት ማይክል ብራዎን ለቲኤንቲ ተናግሯል።

በትናንት ምሽቱ ጨዋታ አርሰናል የኳስ የበላይነትን ይዞ ቢያመሽም፤ ሙኒክ ነጥብ ታጋርቶ ከሳምንት በኋላ መድፈኞቹን ሙኒክ ላይ ይጠብቃል።

አርሰናል በቡካዮ ሳካ አማካይነት ቀዳሚ የምታደርገውን ጎሎ ቢያገኝም የጀርመኑ ቡድን የተከላካይ ስህተቶችን ተጠቅሞ ሁለት ጎሎችን አከታትሎ ማግባት ችሏል።

ግብ ጠባቂው ዴቪድ ራያ እና ተከላካዩ ገብርኤል ማጋሌሽ ሳይናበቡ ቀርተው ኳስ ለተጋጣሚ ተጫዋች መድረሷን ተከትሎ የቀድሞ የመድፈኞቹ ተጫዋች ገናብሪ በግሩም ሁኔታ ቡድኑን አቻ ማድረግ ችሏል።

ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ ዊሊያም ሳሊባ በሊዮር ሳኔ ላይ የፈጸመውን ጥፋት ተከትሎ ሃሪ ኬን ቡድኑ ያገኘውን ፍጹም ቅጣት ምት በቀላሉ ወደ ጎል ቀይሯል።

ተቀይረው የገቡት ገብርኤል ጄሱስ እና ትሮሳርድ ጥምረት አርሰናልን ከመሸነፍ የታደገችውን ጎል አስቆጥረዋል። ትሮሳርድ ከጄሱስ የተቀበለውን ኳስ ከሳጥኑ ውስጥ አክርሮ በመምታት ኳስን ከመረብ ማገናኘት ችሏል።

በሁለተኛው ጨዋታ ሲቲ ከሜዳው ውጪ 3 ጎል አግብቶ ከማድሪድ አቻ ተለያይቶ የመልስ ጨዋታውን በሜዳው ያደርጋል።

ሲቲ የኳስ ቁጥጥር ይዞ ቢቆይም የሚያገኛቸውን እድሎች ወደ ግብ መቀየር ሲሳነው ነበር። ሲቲ በበርናርዶ ሲልቫ ቀዳሚ ቢሆንም ማድሪድ ሩበን ዲያስ እራሱ ላይ አስቆጥሮ እንዲሁም ሮድሪጎ ኳስን ከመረብ አገናኝቶ መሪነቱን ተረክቦ ነበር።

ከእረፍት በኋላ ፎደን እና ጋርዲዮል ቡድናቸውን ወደ መሪነት ቢመልሱም የማድሪዱ ቫልቨርዴ ቡድኑን አቻ አድርጓል።

ባየርን ከ አርሰናል እንዲሁም ሲቲ ከማድሪድ የሚያደርጉት የመልስ ጨዋታ የዛሬ ሳምንት ሚያዚያ 9 ይደረጋል።