“ትዊተር ሳይከፍለን አባሮን ፊቱን አዞረብን”፡ አፍሪካውያን ሠራተኞች

የፎቶው ባለመብት, TWITTER/@OLUWAMAYOWATJ
ከሥራቸው የተቀነሱ የቀድሞ የትዊተር (ኤክስ) የአፍሪካ ሠራተኞች ድርጅቱን እንደሚከሱ ገለጹ።
ከሥራ ሲቀነሱ ድርጅቱ እንደሚከፍላቸው ቃል የገባውን ገንዘብ ባለመክፈሉ ነው ወደ ክስ ሊያመሩ እንደሚችሉ የተናገሩት።
ያለፈው ጥቅምት ኤክስ የአፍሪካ ሠራተኞቹን ከሥራ አስወጥቷል። አብዛኞቹ የወጡት ሠራተኞች በተቋሙ ለወራት ብቻ ነው የሠሩት።
የቀድሞ ሠራተኞቹ ለቢቢሲ “የዓለም ቁጥር አንድ ሃብታም ሰው ገንዘብ ሳይከፍል ሲቀር ያሳዝናል” ብለዋል።
ቢቢሲ ከኤክስ ምላሽ ለማግኘት በተደጋጋሚ ጥያቄ ቢያቀርብም ፈገግ ያለ ኢሞጂ ከመላክ በዘለለ ድርጅቱ መልስ አልሰጠም።
በቅርቡ “አሁን ሥራ በዝቶብናል። ኋላ ላይ ሞክሩ” የሚል ምላሽ ኤክስ ለቢቢሲ ሰጥቷል።
ከዚህ ቀደም ሠራተኞቹን ሙሉ በሙሉ እንደከፈላቸው ድርጅቱ ገልጿል።
ኤሎን መስክ አምና ትዊተርን ከገዛ በኋላ በመላው ዓለም ሠራተኞች ተባረዋል። እነዚህም ከ6,000 በላይ ይሆናሉ።
መስክ በቀን 4 ሚሊዮን ዶላር እያጣ እንደሆነ ገልጿል።
ኤክስ በጋና፣ አክራ በከፈተው ቢሮ የተቀጠሩት ከ20 ያንሳሉ።
በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ወቅት ከቤት ሲሠሩ ቆይተው ነው ወደ ቢሮ የተመለሱት።
ኤክስ ከሥራ ካባረራቸው በኋላ የአእምሮ ጤና ቀውስ እንደገጠማቸውና የቤተሰቦቻቸው ገቢ እንደተቋረጠም ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ኮንትራታቸው የተቋረጠ ቢሆንም የአንድ ወር ደመወዝ እንደሚሰጣቸው ተነግሯቸው ነበር።
ሆኖም ግን ከድርጅቱ የኢሜል ዝርዝር እንዲወጡ ተደርጎ ደሞቸውም አልተከፈላቸውም።
ለአንድ ዓመት ያህል ኤክስ ገንዘባቸውን እንዲሰጣቸው ሲከራከሩ እንደቆዩ ይናገራሉ።
ለሠራተኞቹ የሕግ ከለላ የሰጠው ሰቨን ሰቨን የተባለ ተቋም ነው። የተቋሙ ሠራተኛ ክላራ ኦሎምፒዮ “ነገሩ መሻሻል እያሳየ ነው ብለን ተስፋ ማድረግ ስንጀምር ለሳምንታት ምላሽ ሳይሰጡን ይቆያሉ” ትላለች።
“ከተባረሩ አንድ ዓመት ይሆናቸዋል። ገንዘባቸው አልተሰጣቸውም። ይህ መርህ የጣሰ ነው።”
ከሁለት ወር በፊት ሁለቱም ወገኖች ለመነጋገር ተስማምተው ነበር።
ሆኖም ግን ኤክስ ቀነ ገደቡን ሳያከብር ቀርቷል።
ሐምሌ ላይ ቢቢሲ በሠራው ዘገባ የኤክስ የቀድሞ የአፍሪካ ሠራተኞች በድርጅቱ ችላ መባላቸውን እንደገለጹ ተነግሯል።
ሠራተኞቹ ያለ ክፍያ፣ የጤና መድኅን፣ የእረፍት ወቅት ክፍያ እንዲሁም የድርሻ ገበያ አማራጮች ነው ከሥራ መባረራቸውን የገለጹት።
የተወሰኑት የተቀጠሩት ከናይጄሪያ ነው። ስለዚህም ቤተሰቦቻቸውን ወደ ጋና ካዘዋወሩ በኋላ ያለ አማራጭ ተቀምጠዋል።
ቢቢሲ ዘገባውን በሠራበት ወቅት ነበር ከኤክስ የሳቅ ኢሞጂ ምላሽ የተሰጠው።
መስክ በዚህ ወቅት በጻፈው ትዊት ለድርጅቱ የመገናኛ ብዙኃን ክፍል የሚላክ ጥያቄ በኢሞጂ ምላሽ እንደሚሰጠው ገልጿል።
ከቢቢሲ ጋር ባደረገው ቆይታ ድርጅቱ አሁን 1,500 ሠራተኞች እንዳሉት ገልጿል። ቀድሞ 8,000 የሚጠጉ ሠራተኞች ነበሩት።
ስለ ሠራተኞች መባረር ቅሬታዎች ሲሰሙ የሦስት ወራት ክፍያ ተሰጥቷቸው እንደወጡ ገልጾ ነበር።
ሆኖም ግን የአፍሪካ ቢሮ ሠራተኞች ይህ እንዳልተሰጣቸው ገልጸዋል።
ቢቢሲ ዘገባውን ከሠራ በኋላ ኤክስ ከሠራተኞቹ ጋር መደራደር መጀመሩን ሰቨን ሰቨን አስታውቋል። ሆኖም ግን ምንም ውጤት አልተገኘም።
“አሁን ከዓለም አቀፍ ጠበቆች ጋር እየተነጋገርን ነው። በሌላ ግዛት ትዊተርን እንከሳለን። በስተመጨረሻ ትክክለኛውን ነገር ያደርጉ ይሆናል” ብላለች የሕግ ወኪሏ።
“የውጭ ምንዛሬ ዋጋ ወድቋል። 12 ወራት ሳይፈላቸው ቆይተዋል። በጣም አሳዛኝ ነው። ኤክስ በመስክ ከተገዛ በኋላ በትንሹ የአፍሪካ ቢሮ ትክክለኛውን ነገር ማድረግ ተስኖታል” ስትልም አክላለች።
ለሎችም የቀድሞ የኤክስ ሠራተኞች ክስ ከፍተዋል።
ተቋሙ 500 ሚሊዮን ዶላር አልከፈለም በሚል በካሊፎርኒያም ክስ ተመሥርቶበታል።
ሲኤንቢሲ እንደዘገበው ከነሐሴ ወዲህ ኤክስ ላይ የተከፈቱ ክሶች በአጠቃላይ ከ 2,200 ይበልጣሉ።












